ለረዥም ዓመታት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ወጣቶች «በሥም እንጂ በተግባር ተጠቃሚዎች አይደለንም» ሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህም በማሳያነት የሚያነሱት የሥራ አጡ ቁጥር በሀገሪቱ በየጊዜው የሚያሻቅብ መሆኑን፣ ከስደትና ሞት አለመላቀቃቸውን እና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወትን እንዲኖሩ መገደዳቸውን ነው።
በመሆኑም በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች እንዲስተዋሉ እስከሕይወት የዘለቀ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በሀገራቸው ባይተዋርነታቸው እንዲያከትም ዘርፈ ብዙ ትግል አካሂደዋል። ለዚህም በተለያዩ አጋጣሚዎች እውቅናን ተችረዋል።
«ኢትዮጵያ ያለ እናንተ አስተዋጽኦ አንዳች ርምጃ ፈቀቅ አትልም። የሥራ ባለቤቶች እንድትሆኑ ቅድሚያ ሰጥተን ከእናንተው ጋር በቅንጅት ርብርብ እናደርጋለን» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ ይሄንኑ የሚያረጋግጡ እና የወጣቱን ተስፋ ይበልጥ የሚያለመልሙ እቅዶችን ይፋ አድርገዋል።
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች አሉ። በተጨማሪ በየዓመቱ ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ሥራ ፈላጊውን የዕድሜ ክልል ይቀላቀላሉ። ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ ያለውን አቅም አሟጣ ትጠቀማለች የሚለውን ቁርጠኛ አቋም በትኩረት የተለዩ መስሪያ ቤቶች እንዴት ያዩታል፤ ዝግጁነታቸውስ ምን ድረስ ነው? በተለዩ ዘርፎች የግል አልሚውንስ እያሳተፉ ናቸውን? በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ መረጃዎች ተጠናቅረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት «በ2012 ዓ.ም ለ3 ነጥብ 09 ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታልሞ እየተሰራ ነው። የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለማህበረሰቡ በተለይም ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር አንዱ የለውጡ አካል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ቅድሚያ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ መስሪያ ቤቶችና የሥራ ዘርፎች ተለይተው በእቅዱ የተመላከቱ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ማዕድን ልማት፣ ቱሪዝም፣ ግብርናና አይሲቲ ከፍተኛውን የሥራ አጥ ቁጥር ተቀብለው በማስተናገድ የሥራ ባለቤት ያደርጋሉም ነው ያሉት።
በሀገሪቱ የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደተመ ላከተው «የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግርን በመቅረፍ ሂደት ግብርናው ከሌሎች ዘርፎች የላቀ ሚና እንደሚያበረክት ተጠቁሟል። ግብርናው 80 ነጥብ 5 በመቶ የሀገሪቱ ሕዝብ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ 38 ነጥብ 5 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) የሚሸፍን፣ 85 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እና የኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃ መገኛ መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ ከሚገኘው ጠቅላላ 111 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ መታረስ የሚችል 74 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር፣ የታረሰ 13 ሚሊዮን ሄክታር፣ በመስኖ ሊለማ የሚችል 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር እና በመስኖ እስከአሁን ድረስ የለማው 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑ በሥነልቦና ለመስራት ዝግጁ ለሆነና በዘመናዊ መንገድ ሰርቶ ለመለወጥ ጉልበትና ወኔ ለሰነቀ ሥራ አጥ ወጣት ሰፊ ዕድል መኖሩ በፖሊሲው ተመላክቷል።
በዚህ መነሻነት በ2012 ዓ.ም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ አንድ ነጥብ 03 ሚሊዮን የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን የሥራ ባለቤት ያደርጋል» ያሉት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ «መስኖና የአበባ ልማት ከ568 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የተማሩ ወጣቶች ጭምር በመስኖ ላይ መሠረቱን ባደረገ የግብርና ሥራ ላይ ይሳተፋሉ» ብለዋል። አክለውም 414 ሺህ የሚሆኑ የሥራ ዕድሎች ለሥነ ምህዳር ተስማሚ በሆኑ የደን ልማቶች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።
«የኢንዱስትሪው ዘርፍ ዋና ትኩረቱ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን እና በማዕድን ልማት ሲሆን አንድ ነጥብ 11 ሚሊዮን የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመቀበል የማይተካ ድርሻ ያበረክታል» ሲሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በአገልግሎት ዘርፉ በሥራ ዕድል ፈጠራ ቀዳሚ ተደርጎ የሚወሰደው የአይሲቲ ቴክኖሎጂው ሲሆን 333 ሺህ ሥራ አጥ የተማሩ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽነር አበበ ይናገራሉ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርካቶ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት «የማዕድን ዘርፉ እጅግ ከፍተኛ ዕድል ለሥራ አጥ ወጣቶች ይዞ የመጣ ነው። በመላው ኢትዮጵያ የተለያዩ ማዕድናት በስፋት ይገኛሉ። ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን ለይቶ በተገቢው በማሰልጠን እሴት በሚጨምር መንገድ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል። ወጣቶቹም ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ማዕድናትን እስከአሁን ወደ ውጪ የምንልከው እሴት በሚጨምር መንገድ ባለመሆኑ ከዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚዎች መሆን አልተቻለም። ዘርፉ የውጪ ምንዛሪ ለሀገሪቱ ከሚያቀርቡ መስሪያ ቤቶች አንዱ ነው። ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናትን በቀጥታ ለአለም ገበያ ያቀርባል። በመጠንም፣ በጥራትም፣በዓይነትም ለማሳደግ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ አምስት የምርትና 19 የምርመራ ፈቃዶች የተሰጡ ሲሆን አራት ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ተመዝግቧል። ላለፉት ሃያ ዓመታት ግን በኩባንያ ደረጃ የነበሩት ሁለት ብቻ እንደነበሩ ተናግረዋል። አክለውም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል። «አሁን እየሰራን ያለነው ከሀገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እቅድ ጋር በሚጣጣም መንገድ ሲሆን በሰፊው አቅም ያላቸው ባለሀብቶች እንዲሰማሩ በቅንጅት መስራት ተገቢ ነው። ይህ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሥራ አጥ ወጣቶች እየተደራጁ ዘርፉን በማልማት የሚሳተፉ ይሆናል» ብለዋል።
ዘርፉ ባለፉት ጊዜያት ወጥ በሆኑ የአሠራር መመሪያዎች የተደገፈ ባለመሆኑ ተቀናጅቶ እየተመራ አልነበረም። ይሄን ለማስተካከልና ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የማዕድን ፖሊሲ፣ የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲ እንዲሁም የተለያዩ አዋጆችና ደንቦች ተሻሽለዋል። ተቋማዊ አሠራርን የሚያሻሽሉና የማዕድን ፈቃድ አስተዳደሩን የሚያዘምን የካዳስተር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል ዶክተር ሳሙኤል።
ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር የሚስተናገድበት ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ በባህላዊ መንገድ በየክልሎች የተሰማሩ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ዘጎች የሚሳተፉባቸው ወርቅ አምራቾች አሉ። እነዚህን አካላት በሥልጠና፣ በማሽን፣ በካፒታል አቅም እንዲሁም በሰለጠነ የሰው ኃይል ማደራጀት አስፈላጊ ነው። በመደበኛ መንገድ ሥራዬ ነው ብለው መስራት እንዲችሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ መሠረት የሚፈጥር መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የበጀት ዓመቱ የውጭ ምዛሪ ግኝቱ 48 ነጥብ 938 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ከሚጠበቀው አንጻር ዝቅተኛ ቢሆንም በኩባንያዎችና በባህላዊ ወርቅ አምራቾች 179 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፉ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ እንዲጨምር በማድረግ ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች ዕድል መፍጠር የግድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚቴውን በይፋ ባቋቋሙበት ወቅት ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የዓለም ባንክ፣ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ያስነበቧቸው ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ሀገራዊ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታዎች አስተማማኝ አለመሆን በየዘርፉ መሰማራት በሚፈልጉ የግል ባለሀብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሣርፋል። በዚህ ምክንያት የሥራ አጡን ቁጥር መንግሥት ብቻውን በዘላቂነት ሊቀርፍ ስለማይችል ለሌሎች ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋል። ለሙስናና ለሌሎች ብልሹ አሠራሮች በር ይከፍታል። የቱሪዝም ልማቱም ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይፈጥራል። በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት መስራት ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ዳር ለማድረስና ወጣቱን የሥራ ባለቤት ለማድረግ ይረዳል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011
ሙሐመድ ሁሴን