
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ያለውን ሰፊ የማዕድን ሀብት የወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ገለጸ፡፡
በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ለ81ሺ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ እና ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ይርዳው ነጋሽ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ የማዕድን ሃብት አላቸው ከሚባሉ የኢትዮጵያ ክልሎች የኦሮሚያ ክልል አንዱና ቀዳሚው ቢሆንም፤ ክልሉ ያለው ሃብት በውል አይታወቅም፡፡ በመሆኑም ባለስልጣኑ በክልሉ ያሉ የማዕድን አይነቶች፣ መጠንና የመገኛ ቦታ ጭምር በውል እንዲታወቅና እንዲለይ ጥናት እያደረገ ሲሆን፤ ዘርፉም የወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
እንደ ኢንጂነር ይርዳው ገለጻ፤ የክልሉን ማዕድን አይነት፣ መጠንና መገኛ ከመለየት አኳያ በክልሉ ያሉ 20 ዞኖች ተለይተው ባለስልጣኑ ከኩባንያዎች፣ ከማዕድን ሚኒስቴርና በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች ጋር እየሰራ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጋር በመሆን ወደስራ ገብቷል፡፡ በዚህም በክልሉ ያለው የማዕድን ሃብት እየተለየ ለወጣቶች መሰጠት ያለበት ለተደራጁ ወጣቶች እንዲሰጥ በማድረግ ለ81ሺ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ የሚፈልጉትም እየተለዩ ለባለሃብቶች እንዲተላለፉ ይደረጋል፡፡
በዚህ መልኩ እየተለዩ ለባለሃብት የሚሰጡ የማዕድን ልማት ስራዎችም ባለሃብቶቹ ወደስራ ሲገቡ የማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ ለአገር ማስገባት ያለባቸውን ገቢ በአግባቡ እንዲከፍሉ ለማስቻል የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ባለሃብቶቹ በተሰማሩ ባቸው አከባቢዎች በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ያሉ እንደመሆናቸው እነዚህ ባለሃብቶች ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማሳተፍና ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአካባቢው የሚሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ ሲወስዱ በምን መልኩ የአካባቢውን ህብረተሰብ እንደሚያሳትፉና የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ የስምምነት አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን በዚህም በማዕድን ልማት የተሰማሩ ወጣቶች ከእነዚህ ኩባንያዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በስራ እድልም ሆነ በገበያ ትስስር እየተከናወነ ባለው ተግባርም ወጣቶች በዘርፉ በቀላሉ ሊሰሯቸው በሚችሉ የማዕድን ልማት ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ በሩብ ዓመቱ ውጤታማ አፈጻጸም ታይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
በወንድወሰን ሽመልስ