
አዲስ አበባ፡- በርካታ ወታደር በመጠቀም እና ምሽግ ቆፍሮ ለረጅም ሰዓት ከመጠበቅ የተለየውን የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የውትድርና ስልት ለመከተል የዘመናዊ መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።
የኢፌዴሪ መከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ትናንትና አስመርቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የምኒሊክ ግብር አዳራሽ ትናንት በተከናወነው የምርቃት ስነስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት ሽልማት ለተመራቂዎች አበርክተዋል። በወቅቱም ዶክተር አብይ አህመድ እንደገለጹት፤ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ውትድርና ስልት ተለውጧል። አሁን ላይ ብዙ ወታደር ይዞ ምሽግ ቆፍሮ መቆየት ብቻ ተዋጊ እንጂ አሸናፊ አያደርግም። በመሆኑም ሰራዊቱን ለማዘመን በዕውቀትም ሆነ በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
እንደ ዶክተር አብይ ገለጻ፤ ዘመናዊነት ሲባል ከከብቃት፣ ከሰብዕና፤ ከምርምር እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ተጨማሪ ሰፊ ጉዳዮችን ያጠቃለለ ነው። ዘመናዊ ጀቶችን ከጎበዝ አብራሪዎች ጋር ማሰማራትና ጠላት ሲመጣ መትቶ መጣል ብቻ ሳይሆን፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማሰማራት እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ እስከመጣል የሚደርስ ብቃት ያስፈልጋል። በምርምሩም ዓለም ላይ በህዋ ሳይንስ እና በተለያዩ መስኮች ያሸነፉ ሰዎች ከውትድርና ሙያ የወጡ በመሆናቸው ሰራዊቱ እራሱን ለዕውቀት እና ለምርምር ማሳተፍ ይገባዋል። በዚህ ረገድ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ የዘመናዊነቱ አንዱ አካል ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ መከላከያውን ለማዘመን ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ይህን አላማ የሚደግፉ በርካታ አገራት በመኖራቸው በቀጣይም ወታደሩ የተለያዩ አዳዲስ ስልጠናዎች እንደሚኖሩ በማሰብ ራሱን ሊያዘጋጅ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። ለአላማው መሳካት ግን ከዘረኝነት እና ከወረደ አስተሳሰብ ጎን ባለመቆም በአንድ ሃሳብ ለአገሩ የቆመ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። ወታደሩ በትጋት የሚሰራ እና ማልዶ የተነሳ በመሆን ለወገን ተቆርቋሪነቱን ማሳደግ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሃመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ሰራዊቱን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች፣ በስልጠና እና በአቅም እንዲጠናከር የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሀገርን እና ወገንን በሚያኮራ መልኩ የሚፈጸሙ ግዳጆችን ለማበራከት በየጊዜው ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የአሁኑ የመከላከያ አዛዥነት ኮሌጅ ከፍተኛ መኮንኖች ኢትዮጵያውያን ተመራቂዎች ወደሰራዊቱ ተግባር ሲመለሱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ በሚያስችል ሁኔታ የሰለጠኑ በመሆኑ ለመከላከያ ተጨማሪ አቅምን መፍጠር ያስችላል።
እንደ የኢፌዴሪ መካላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ መረጃ መሰረት፣ ተመራቂዎቹ 100 መኮንኖች ለአንድ አመት ስልጠና ወስደዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ደግሞ 79ኙ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ አራቱ ሴቶች ናቸው። የተቀሩት 21ዱ ከፍተኛ መኮንኖች ደግሞ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን ዜግነት አላቸው።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 5/2011
ጌትነት ተስፋማርያም