በተፈጥሮ ፍቅር የነጎዱ፣ ለተፈጥሮ የተፈጠሩ ጥቂቶች አሉ ከተባለ ተፈጥሮን ከማጥናት አልፈው እየኖሩት ካሉት መካከል የዛሬው «የህይወት እንዲህ ናት» አምድ እንግዳችን አቶ ደቻሳ ጅሩ ተጠቃሽ ናቸው።
አቶ ደቻሳ ከልጅነት ጀምሮ ለተፈጥሮ ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ የመጠሪያቸው መሰረት ደን የሆነ፣ በዚህም የደን ዘርፍ ላይ ብዙ ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉ ናቸው። “በገርቢ ዛፍ” ላይም በሰሩት ጥናት አለምዓቀፍ ሽልማት ተችሯቸዋል። እናም በዓለም ላይ የተለያዩ ፍጥረታት አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ተለይተው ስለማይኖሩ የሰውም ልጅ መሰረቱን ደን ማድረግ እንዳለበት ካላቸው ተሞክሮ ተነስተው ይናገራሉ። ይህ የዘወትር ንግግራቸው ከምን መነጨ፣ በዚህ የሕይወት ዑደት ውስጥ እንዴት አለፉና ተጠቀሙ የሚሉትን እያነሳን ተወያየን። ለእናንተ አንባብያን ልምድ ይሆን ዘንድም እንዲህ አቀረብነው። መልካም ንባብ።
ደቻሳ
በኦሮሞ ባህል ለህጻናት ስም የሚወጣው በታቅፎ ስም ነው፤ በባህሉ አምስት የእምነቱ አባቶች ልጁ ሲጫወት ትኩረት የሚያደርግበትን ነገር በመከታተልና በማየት ወዴት እንደሚያዘነብል ይረዳሉ። በተጨማሪም በቅርበት ያለው ቤተሰብ ነውና እነርሱን ጠይቀው ምን አይነት ስም ማውጣት እንዳለባቸው ይወስናሉ። እናም አቶ ደቻሳ በዚህ መስመር ውስጥ በማለፋቸው ስም ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
“ደቻሳ” የሚለው ስም “ደቼ” ከሚለው ኦሮምኛ ቃል ትርጉም ጋር የሚያያዝ ሲሆን “ደቼ” ማለት መሬት እና መመለስ የሚሉ ትርጉሞችን ይይዛል። አቶ ደቻሳም መሬት ሁሉን ቻይ ፣ታጋሽ። ቢረግጡት የማይቆረቁረው። ደግሞም እንደ መሬት የሰጡትን ሁሉ የሚያበቅልና ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅሙ እንዲሆኑላቸው በመመኘት ነው ይሄንን ስም ያወጡላቸው። እርሳቸውም ታዲያ ስምን መላክ ያወጣዋል እንደሚባለው ሆነና ስምና ምግባራቸው ተስማምቶላቸዋል።
ሌላው “ደቼ” ማለት መመለስ ማለት ሲሆን፤ ወደሌላ አቅጣጫ መዘርጋት ያመለክታል። ምክንያቱም የዛፍ ቅርንጫፍ መዘርጋቱ አንድም ጥላ ለመሆን አንድም ጸሀይ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው። ስለዚህ ከለላ ነህ ለማለት ስለፈለጉም በዚህ ምክንያት ስያሜ እንደተሰጣቸው ይገልጻሉ።
በዚህ ሁኔታ ስማቸውን ያገኙት አቶ ደቻሳ፤ በደን ፍቅር እንዲያዝ ያደረገኝ ቤተሰባቸውና የአካባቢያቸው ማህበረሰብ መሆኑን ይናገራሉ። በትውልድ ቀያቸው አርሲ አካባቢ ክርስቲያን ሙስሊሙ ዛፍን እንደባህል በቤተ እምነቱ መትከል ያዘወትራል። “የእኔ ቤተሰብ ደግሞ በሁለቱም እምነት ውስጥ ያለፈ ነው። ስለዚህም ቤተሰቤ ለዛፍ ልዩ ፍቅር እንዲኖረኝ ብዙ ጥሯል። ተሳክቶለታልም” ይላሉ።
እንግዳችንን ከሁሉም የአካባቢው ልጆች ለየት የሚያደርጋቸው ዛፍ ወዳድ፣ ፈረስ ጋላቢና የሚያዩትን ሁሉ በስዕል መግለጽ የሚወዱ መሆናቸው ነው። የዋህና የተባሉትን በቅንነት የሚፈጽሙ መሆናቸው ደግሞ ምርቃት አዝንቦላቸዋል።
ከየዋህነታቸው ጋር ተያይዞ «ማሞ ቂሉ» የሚል ቅጽል ወጥቶላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የዚህ ቅጽል ስም መውጣት ምክንያት በርከት ያለውን የጤፍ ማሳ አርመህ ከጨረስክ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ትገባለህ በመባላቸው ይሄንኑ ለማሳካት ብለው፤ ምሽት ሳይቀር በመስራት የታዘዙትን አጠናቀቁ። ሆኖም ቃል የተገባላቸው አልተፈጸመላቸውም። ይባስ ብሎ ዳግም የማይ ችሉት ተግባር ተሰጥቷቸው እንደነበርም ይናገራሉ። የቤተሰቡ አቋም ወደ ትምህርት ማስገባት አይደለምና ሌላ ሌላ አይቻላቸውም ብለው የሚያስቡትን ምክንያት እየደረደሩ ያታልሏቸው ነበር። “ ቂል” የመባላቸው መነሻም ይሄው ነው።
አቶ ደቻሳ የመጨረሻ ልጅ በመሆናቸው ቅጣት ባይኖርባቸውም የሰው ገንዘብ ከነኩ ግን ክፉኛ ይገረፉ እንደነበር ይናገራሉ። እንዳውም በአንድ ወቅት ያደረጉትን ሲያነሱ “ዶሮ ገዝተው ለማርባት ይፈልጋሉ። ይሁንና የገዟት ዶሮ ያረጀች ነበረች። እናም እቤት ሲገቡ እናታቸው በጣም ተናደው ይቆጧቸዋል። አቶ ደቻሳም ዶሮዋን ይዘው ወደ ገዙበት ቦታ ይሄዳሉ። የሸጡላቸውን ሰው ባያገኝዋትም ለሌላ ሰው እርሳቸውም ይሸጣሉ። ይሄ ድርጊታቸው ደግሞ ሲመለሱ ዱላ አቆያቸው። ተደበደቡ። የሰው ልጅ ከሁለት ነገር ትምህርት ይወስዳል። አንዱ ከሰው፤ ሌላው ከራሱ። ይሄ ለእርሳቸው ከራሳቸው ትምህርት ያገኙበት ነበርና የእናታቸው ቁጣና ግርፋት የወደቀ ሳንቲም እንኳን እንዳያነሱ እንዳገዛቸው ይመሰክራሉ።
ከብት መጠበቅ የሚወዱት ባለታሪኩ፤ ብዙ ጊዜ ግን ከብቶቹ አምልጠዋቸው ማሳ ውስጥ ይገቡባቸው ነበርና ይደበደባሉ። ስለዚህም በልጅነታቸው የሚያስደስታቸው ከአባታቸው ጋር ቤት መዋል ነው። አባታቸው ማንም እንዳይነካቸው ስለሚከላከሉላቸው እንደ ጠበቃቸው ይቆጥሯቸዋል። ይህ ግን በአንድ በኩል እንደጎዳቸው ይገልጻሉ። ከስራቸው እንዳይርቁ ስለሚፈልጉ እድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ እንኳን ትምህርት ቤት አላስገቧቸውም።
በአፈር ውስጥ ያለውን ምስጢራዊ ነገር ማወቅ የልጅነት ፍላጎታቸው እንደነበር የሚናገሩት እንግዳችን፤ ዛፍ ለውሃ፣ ለጥላ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለሀይል ምንጭነት ያለውን ፋይዳ ስመለከት እመሰጥበት ነበር። እናም ሁሌ በዚህ ዙሪያ መመራመርን እሻለሁ ይላሉ። በጣም ሀብታም መሆን። መርቸዲስ መኪና ገዝተው እናታቸውን ማንሸራሸር ምኞታቸው እንደነበር ያስረዳሉ። ከምኞታቸው አንዱ ተሳክቶ አንዱ ባለመሆኑ በጣም እንደሚያዝኑም አጫውተውናል።
ትምህርት
ቤተሰቦች አንድም እንዳይርቋቸው፤ በሌላም በኩል ከብት እንዲያግዱላቸው በመፈለጋቸው የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ ትምህርት ቤት ያስገቧቸው እድሜያቸው ከፍ ካለ በኋላ ነው። ይህ ደግሞ በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳርፎባቸው እንደነበር አይረሱትም። ለዚያውም ለትምህርት የበቁት ወንድማቸው ጋር ትምህርትን ፍለጋ በመጓዛቸው እንደነበር ያነሳሉ። እርሱ ሰብዓዊነት የሚሰማውና የችግረኛ ልጆችን ሰብስቦ የሚያስተምር በመሆኑ በእንቢታ ቢሸኛቸውም ለርዕሰ መምህሩ ነግሮላቸው ግን ያለተያዥ መግባት ችለዋል።
የልጅነት ምርጫቸው ምን ያህል ከተፈጥሮ ጋር እንዳቆራኛቸው የሚያነሱት አቶ ደቻሳ፤ ትምህርት ቤት እስኪርብቶ እንዲገዙ ሲታዘዙ ከሰማያዊ ይልቅ አረንጓዴ ቀለም ምርጫቸው እንዳደረጉና ሁልጊዜ አረንጓዴ እያዩ እንደተማሩ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ለዛሬው የደን ምርምር እንዳበቃቸውም ይገልጻሉ።
አቶ ደቻሳ፤ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በዚያው በትውልድ ቀያቸው አርሲ ሲሆን፤ ራስዳርጌ ትምህርት ቤት ተማሩ። ይሁንና በዚህ ጉዟቸው ወቅት ብዙ ችግሮችን አስተናግደዋል። የመጀመሪያውና የማይረሳቸው ግን የአማርኛ ትምህርት ውጤታቸው ዝቅ ማለት ነው። መሸነፍን የማይ ወዱት አቶ ደቻሳ፤ በአንድም ትምህርት ሌላ ሰው እንዲበልጣቸው አይፈልጉም። ሆኖም አንድ ቀን ግን ይህንን የሚያስቀር ችግር ገጠማቸው። በአማርኛ ትምህርት ወደቁ። በወቅቱ አማርኛ ትምህርት ቅኔ ስለነበር እጅግ ከበዳቸው። በዚህም አስበውት የማያውቁትን ውጤት አመጡ።
በሌሎቹ ትምህርቶች ውጤታማና የደረጃ ተማሪ የሆኑት አቶ ደቻሳ ይህንን ለመበቀል በሚገባ አጠኑ። በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥም 350 የአማርኛ መጽሀፍትን አነበቡ። ይህ ደግሞ መምህሩን የሚያስንቅ ተማሪ እንዲሆኑ አስቻላቸው። በተለያየ መልኩም ቅኔ መዝረፍን ቻሉ። ቅኔን ሲዘርፉ ከዛፍ ጋር ያገናኙ እንደነበር የሚናገሩት እንግዳችን፤ ሥር፣ ግንድ፣ ቅጠል፣ ልብ፣ አይንና ቅርፊት እያሉም ይሰይሙትና ይቀኙ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አቶ ደቻሳ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ በቀጥታ ወደ ጅማ ግብርና ኮሌጅ ነበር የገቡት። ከዚያ በፊት ግን የተለያዩ ቦታዎችን ረግጠው ነበር። ምክንያቱም በወቅቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በዲግሪ የሚማሩበትን ውጤት ማምጣት አልቻሉም ነበር። በአገር አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ፈተና ሲወስዱ ሂሳብ የተለየ ትምህርት ስለነበር “ኤፍ” አምጥተዋል። ሂሳብ ደግሞ ዋነኛ መፈተኛ ነጥብ ነው። በዚህም ዓመቱን ያለምንም ትምህርት ላለማሳለፍ ሲሉ በዲፕሎማ ተወዳደሩና ወደ ጅማ አቀኑ።
በወቅቱ ግን አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ አልፈው እንደነበር ያስታውሳሉ። ኮሌጁ ምንም እንኳን በዲግሪ ቢያስመርቅም የእርሳቸው ምርጫ ደን በመሆኑ ይህንን ማድረግ አልፈለጉም። በዚህም ከዲግሪ ይልቅ ዲፕሎማን መርጠው ጀነራል አግሪካልቸርን ለመማር ጅማ ኮሌጅ ሄዱ። ለዓመት ያህልም በዚያ ቆይተው ውጤታቸውን በማሻሻል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። ፊዚካል ሳይንስ ትምህርትን መርጠው መከታተል ጀመሩ። ሆኖም ሊገፉበት አልቻሉም። የሂሳብ ትምህርት ዳግም ፈተናቸው። “ኤፍ” አመጡና ዓመቱን መቀጠል ተሳናቸው።
ይህም ቢሆን ተስፋ አልቆረጡም። እንደውም አሻሽለው እንደሚመለሱበት ያውቃሉ። እናም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለቀው ጅማን ግን እንዳይ ለቁት የሚያደርጋቸውን ምክንያት ፈጠሩ። አሳማኝ ምክንያት አቅርበው ከዓመት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ ዕድል ተመቻቸላቸው። በአድቫንስ ዲፕሎማም በከፍተኛ ማዕረግ በእርሻ ትምህርት ተመረቁ።
በወቅቱ ደን ተብሎ ለብቻው ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳልነበር የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማርና ዲግሪ ለመያዝ ሲሉ ዓመታትን በደን ልማት ላይ በሥራ አሳለፉ። ብቁ ነኝ ብለው ካመኑ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቆዩበትን የዓመት የፊዚካል ሳይንስ ውጤታቸውን ይዘው የባይሎጂን ትምህርት በማከል ዓመት ያህል ከተማሩ በኋላ ትምህርቱ በስፋት ወደሚሰጥበት ሀሮማያ የቀድሞ አለማያ ኮሌጅ ተዘዋወሩ። ከእዛም በእጽዋት ሳይንስ ባችለር ዲግሪያቸውን ይዘው ተመረቁ።
ለሁለተኛ ዲግሪ የሚያበቃቸውን ትምህርት መማር ቢችሉም በተለያየ ምክንያት ማስረጃዎቹ በእጃቸው የሉም። በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በማስትሬት ዲግሪ ተምረው በመመረቂያ ጽሁፍ ተጣልተው ወረቀቱን ያልተቀበሉት አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።
«ምርምሮቼ መሰረታቸው ማህበራዊ ነገሮች ናቸው። በዘመናዊ እውቀት እንዲታገዙ አደርጋለሁ እንጂ መነሻዬ ከእነርሱ ውጪ አይደለም። ከተፈለገ በምርምር የሰራሁት በሶሾሎጂ የተሰራ ሥራ አለኝ እርሱን አይታችሁ ወረቀቱን ስጡኝ ብልም ማንም ሊሰማኝ አልፈለገምና ትቸዋለሁ። እኔ የምፈልገው እውቀት እንጂ ወረቀት አይደለም።» ሲሉ አጫውተውናል።
አቶ ደቻሳ፤ ሲውዲን አገር ሄደው እንዲሰለጥኑ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች ቢፈጠርላቸውም አሻፈረኝ ብለው አውስትራሊያ የትምህርት እድል አግኝተውም ተምረዋል። በወቅቱ የሲውዲኑን እንቢ ያሉት ከአገሪቱ ተወስዶ ሲውዲን ውስጥ የበቀል ዛፍም ሆነ ችግኝ አለመኖሩ፣ ከሲውዲንም መጥቶ አገር ውስጥ የበቀለ አንድም ችግኝ ባለመፈጠሩ ነው። እናም ሥልጠናውን እዚያ ሄደው ቢወስዱ ለአገራቸው ሆነ ለራሳቸው የሚያተርፉት ነገር ስለሌለ ትተውታል። በዚህም ከአውስትራሊያ በደንና እርሻ ጥምር ልማት የትምህርት መስክ ሜልበርን ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ ሆነዋል።
በጆግራፊ ትምህርት የተሻለ እውቀት እንዳላቸው የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ በአፈር ምርምር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማስተሳሰር ብዙ ሥራዎችን እንዲሰሩ የረዳቸው የተለያዩ ሥልጠናዎች ከተለያዩ አካላት በማግኘታቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። በተለያየ መልኩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት በሲውዲን፣ በታንዛንያና ኬንያ እንዲሁም በጣሊያን የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንደወሰዱም ነግረውናል።
«ትምህርት ለእኔ ለዘመናት የተከማቸ በመስኩ ውጤታማ የሆነ ሰው በተግባር ተፈትሾ ውጤት ያመጣ፣ ከእርሱ የምታገኘው እውቀት ነው። እውቀቱ ራሱ እውቀት ለመሆኑ ማረጋገጥ የሚችል መምህር የሚሰጠው ትምህርት ነው። አንድን ነገር አውቆ በዚያ እውቀት የሰውን ልጅ ከችግር ማላቀቅም ነው።»
47 ዓመትን በደን ልማት
ከሁለት ዓመት የጅማ ግብርና ኮሌጅ ቆይታ በኋላ ነበር ለሥራ ወደ አርሲ የሄዱት። በዚያም ጭላሎ የእርሻ ልማት ድርጅት ውስጥ ገብተው የደን ልማት ረዳት ተመራማሪ ተብለውም 11 ዓመታትን አሳለፉ። ይህ አጋጣሚ ብዙ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮላቸዋል። ምክንያቱም የልጅነት ህልማቸው ደን ላይ መመራመር ነው። እናም ፈልገውት ስለሚሰሩበት በሥራቸው ብዙዎች ይደሰቱበት ነበርና የሚፈልጉትን ያደርጉላቸዋል።
ጭላሎ ላይ የሚሰራው ሥራ መስክ የሚበዛበት ሲሆን፤ ከብዙ አገራት ከመጡ ባለሙያዎች ጋር እንዲተዋወቁም እድል ሰጣቸው። ልዩ ልዩ የምርምርም ሆነ የስልጠና እድሎችን እንዲያገኙም አስችሏቸዋል። ከዚያ አልፎም በተለይም በእጽዋት ሳይንስ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ረድቷቸዋል። በእንጨት ልማት ላይ በስፋት የሰሩትም ከየአገራቱ ከተውጣጡ ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀት በመቀመር ነው። በተለይ ከሲዊድኖች በርከት ያለ እውቀት እንደቀሰሙ ይገልጻሉ።
የአርሲው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ደግሞ በቀጥታ ግብርና ምርምር እንደመጡ የሚገልጹት አቶ ደቻሳ፤ በተለያዩ የእርከን ደረጃዎች አልፈዋል። የማህበራት ዘርፍ ሀላፊም በመሆን አገልግለዋል። በአግሮ ፎረስተሪ የተለያዩ ምርምሮችንም እየሰሩ ብዙዎችን አስተምረዋል። በተለይም ከውጪ አገር ሰዎችን በመምረጥ በየትኛው አካባቢ የተሻለ ሥራ ይሰራሉ በማለት ከእነርሱ ጋር ይሰሩ ስለነበር በግብርናው ዘርፍ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራትን እንደከወኑ ይናገራሉ።
ከእነዚህ ሁሉ ግን ከጀርመኖች ጋር በመሆን በሞሪንጋ ዙሪያ የሰሩት ምርምር እንደሚያስደስታቸውም ያነሳሉ። ደቡብ ክልል ውስጥ ሞሪንጋን፣ መሀል አገር ላይ አልቢዳንን፣ ሰሜን ላይ ደግሞ የጎጃምን ብሳና እያሉም የተለያዩ ምርምሮችን መስራታቸውም ለአገር የድርሻዬን ተወጥቻለሁ እንደሚያስብላቸውም ያስረዳሉ።
አሁን በጡረታ ቢገለሉም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እውቀታቸውን አካፍለው እውቀትም አግኝተው ለመኖር ዕድል አግኝተዋል። የሞሪንጋ ማህበር ኮሚቴ እና የ19 ማህበራት አባል በመሆንም የተለያዩ ሥራዎችን ይሰራሉ። የማማከር ስራም በሙያ ዘርፋቸው ከመጣ ወደ ኋላ አይሉም። ነገር ግን እዚህ ላይ ከሥራውና ከገንዘቡ ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጡት ፍላጎታቸው እንደሆነም አጫውተውናል።
የደን ፈውስ
የሞሪንጋ ዛፍን ለአለም ያስተዋወቁትና ከዓርባ ሰባት ዓመት በላይ ምርምር እንዳደረጉበት የሚናገሩት አቶ ደቻሳ፤ የገዳ ሥርዓት ያለ ዛፍ ህልውና የለውም። እንደ አካባቢያችን ባህል ዛፍ መሰረታዊ መለያችን ነው። በእምነትም ቢሆን ክርስቲያን ሙስሊሙ ቤተ እምነታቸውን በዛፍ ያሳምራሉ። ይህ ደግሞ ለአካባቢ ስነምህዳር ብቻ ሳይሆን ለእምነቱ ባለቤቶች ጭምር ባህል እንዲሆን አድርጎታል። እኔም ከዚያ በመውጣቴ ነው ባህሌን ደን ያደረኩት ይላሉ።
«ደን ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ የሚውል አይደለም። በመድሀኒትነትም ጭምር የሚያገለግል ነው። ይህንን የተረዳሁት ደግሞ ገና ተማሪ ሳለሁ ነበር።» የሚሉት እንግዳችን፤ በደርግ ዘመን የገጠማቸውንና የወሰዱትን መፍትሄ አብነት በማድረግ ያነሳሉ። ጊዜው ብዙ ሰዎች በሰፈራ ውሃና እርጥበት ባለበት ቦታ እንዲሰፍሩ የተደረገበት ነው። ቦታው ግን ምን አለበት የሚለው “በባለሙያ አልተጠናም”። እናም ነዋሪዎቹ ባሉበት አካባቢ ደምስር የሚዘጋና እግርን የሚያሳብጥ ትል ተፈጠረ። በዚህም ብዙ ሰዎች አለቁ። እንደውም ብዙ ሴቶች ሰው እንዳያያቸው ሰው ሲመጣ ቀሚሳቸውን ቡፍ አድርገው በመልበስ ይቀመጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ እነርሱ ተማሪዎች በመሆናቸው ጥናት እንዲያደርጉና ሰፋሪዎቹ ምን ላይ እንዳሉ እንዲመለከቱ ነበር በዘመቻ የተላኩት። በዚህም ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ ከተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን መፍትሄ ለመስጠት ይሯሯጡ ጀመር። እድል ቀናቸውናም ጊዜያዊ መፍትሄ ሰጡ። በቀጣይነት ችግሩ እንዳይቀጥል ደግሞ ቀይ ባህር ዛፍ ተከሉ። ቀይ ባህር ዛፍ እርጥበቱን ይመጠውና ደለል እንዳይፈጠር ያደርጋል። ደለል ከጠፋ ደግሞ ትሉ አይኖርም። ስለዚህ ዛፍ መድሃኒት መሆኑን በዚህ ማረጋገጥ ችለናልም ሲሉ አጫውተውናል።
ሽምግልናን ፍለጋ
ገና ወጣት ሳሉ ነበር ጺማቸውን ማሳደግ የጀመሩት። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ አንድ ነገር ነበር። ሰዎች እንዲያከብሯቸው፣ እንዲታረቁላቸው ማድረግ። ሰው መልክንና ቁመናን ያያል። ከሚናገረው ይልቅ አለባበሱና ያለው ተክለቁመና ለአክብሮት ያበቃዋል። ስለዚህም እርሳቸውም ጺማቸውን ከማሳደግ አልፈው ነጭ ቀለም ይቀቡት እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ለብዙዎች መፍትሄ ሰጪ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ልጆቻቸው ይህን ተግባራቸው አይወዱላቸውም።
አንደኛው ጺምህን አታሳድግ ሲል አንዱ ደግሞ አሳድግ ይላል። ይህ ያሳሰባቸው አባትም ሁለቱን ለመዳኘት አንድ ነገር ሰሩ። ለወራት ያህልም ጺማቸው እንዲወገድ ሆነ። ምክንያቱም ሁለቱን ለማስማማት ከአንድ ጎን ላጭተው አንዱን ባለበት ትተው «በሉ ሁለታችሁም እንዳትጣሉ። እንዲህ ሆኜ የፈለጋችሁት ቦታ እንሄዳለን» ሲሏቸው አንደኛው ተሸንፌ ያለሁ ስለዚህ ተላጨው ብሎ መረታቱን እንደገለጸላቸው ያስታውሳሉ። ከዚያም በኋላም ቢሆን እድሜያቸውም ባይደርስ እንደ አዛውንት ጺማቸውን አሳድገው ሰዎችን ያስታርቁ እንደነበርም አውግተውናል።
ቤተሰብ
አቶ ደቻሳ የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ አንዱ ሞቶባቸው ሴቷ ልጃቸው ውጪ አገር ትገኛለች።
«ህዝባዊ የሆነ ሰው ቤተሰብ የለውም። ለቤተሰቡ ሳይኖር ለህዝብ በሚል እሳቤ ቤተሰቡን ይጎዳል። ጥሩ ባልም መሆን አይችልም። በዚህም የእኔም ቤተሰብ እንደእኔው ተጨራምቶ በችግር ውስጥ አልፏል። የተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎችን እንድይዝ እድሎች ተመቻችቶልኝ ነበር። ሆኖም የምፈልገውን የምሰራው ከታች ስሆንነው ብዬ ስለማምን ይህንን ላደርግ አልፈለኩም። በዚህም እንደ ሥራ ልምዴና እውቀቴ ተጠቃሚ መሆን ተስኖኛል። ይህ ደግሞ ለቤተሰቤም የፈለኩትን እንዳላደርግ ገድቦኛል»ይላሉ።
ልጆቻቸውን ያሳደጉት በዲሞክራሲያዊና በውይይት እንዲያምኑ አድርገው መሆኑን ይናገራሉ። አርሲ ለሥራ በሄዱበት ወቅት የትዳር አጋራቸውን እንዳገኟት ይናገራሉ። ምርጫቸው በጣም ቀይ ወይም በጣም ጥቁር ነውና የዛሬዋ ባለቤታቸው ለእርሳቸው መልከመልካም ሆና ታየቻቸው። በዚያ ላይ የሚሰራ ሰው በጣሙን ይወዱ ነበርና ምንም እንኳን ምግብ ቤቱ የራሳቸው ቢሆንም በሥራ ተጠምዳ ስላዩዋት ይበልጡን ወደዷት።
በምግብ ቤቱ በቋሚነት ተመጋቢ በመሆናቸው ደግሞ የራሳቸው ለማድረግ የገደባቸው ነገር አልነበረም። ፈተና የሆነው የእርሷ እሺ አለማለት ብቻ ነው። ሆኖም እስኪያገኟት ድረስ ደጋግመው ጥያቄያቸውን በማቅረብና በመመላለስ አሳመኗት። የልጆቻቸው እናትም አደረጓት። ዛሬ በደስታ አብረው ለመኖርም በቁ።
እንደገና ተወለድ ብባል
«ከእንደገና በብሔር ተከፍሎ ተወለድ ብባል ኮንሶዎችን፣ ደራሼዎችንና ጌዲዮዎችን ሆኜ ብፈጠር ደስ ይለኛል።”ይላሉ። እነዚህ ብሄረሰቦች በደረቅ ምድር ውሀን ያመጡ። ታታሪ። የስራ ሰው ናቸውና ከእሳቸው ስሜት ጋር አንድ ሆነው ስላገኟቸው እነሱን ሆኖ ዳግም መፈጠርን ተመኙ። ጨዋማነትን ተዋግተው ያሸነፉና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ህዝቦች ናቸው ሲሉም ምስጋና ማበረታታቱን አከሉ።
ለምለም ምድር
አገሪቱ የምቹ አየር ንብረት ባለቤት ነች። ዝናብ ባይኖር እንኳን ብዙ የሚበቅሉ ችግኞች አሏት። በዚህም የትኛው ለየትኛው ይመቻል የሚለውን በማጥናትና በምርምሮች ላይ በመንተራስ ሥራዎችን ማከናወን ከቻለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝናብ ድርቋ አይሆንም። ለምለምነትም መለያዋ ይሆናል። የጥንት ማንነቷም በሚገባ ይመለሳል። ስለዚህ ደረቁን ወደ እርጥብ ለመቀየር እጃችን ላይ ያሉ ብዙ ችግኞች አሉንና እንጠቀምባቸው ይላሉ።
አላማው ዓሳን መያዝ ነው። ይሁንና መረቡ ሲደራ ወንፊት ከተደረገ አይሳካም። ሊይዝ የሚችልበትን ድር ማድራት ይገባል። መንግስትና ምሁራኑ ተናበው መስራት አለባቸው። መስሪያቤቶችም ለየብቻቸው ከመሮጥ ለአንዱ አንዱ መጋቢ መሆኑን ተረድተው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን ማንም ከማንም አይማርምና አገር ልትለወጥ አትችልም ሲሉ የመጨረሻ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እኛም ይህ ሀብታችንን ማየት ግዴታ መሆኑን እየጠቆምን ለዛሬ በዚህ አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011
ጽጌረዳ ጫንያለው