
አዲስ አበባ፡- ጃፓን ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ለምታደርገው የልማት እንቅስቃሴ የሚውል የ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ሰጠች።
የእርዳታ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ዴሱኬ ማሱናጋ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ትናንት በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈራርመዋል። በስምምነቱ ወቅት እንደተገለፀው፤ የእርዳታው ገንዘቡ ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ለምታደርገው የልማት እንቅስቃሴ አጋዥ እንዲሆን የታሰበ ሲሆን፣ በዋናነት በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሆስፒታሎች የህክምና ቁሳቁስ ለማቅረብ ይውላል።
አምባሳደር ዴሱኬ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የጃፓን መንግሥት የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። በተለይም ኢትዮጵያን ለመደገፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ይሰጣል። ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን ሕይወት ለማሻሻል በምታከናውነው ዘርፈ ብዙ የልማት ፕሮግራሞች ጃፓን የበኩሏን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ትገኛለች።
በጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ መሰረተ ልማት፣ ትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ጃፓን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥልበት አምባሳደሩ አብራርተዋል። ጃፓን አሁን የሰጠችው እርዳታም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ሲሆን፣ በተለይም በሆስፒታሎች የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ጥራትንና የወሊድ አገልግሎትን ለማሻሻል እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በሆስፒታሎች ያሉ የሕክምና ቁሶች እጥረት በጤና ሚኒስቴር ከተለዩ በኋላ እንደ አስፈላጊነታቸው እንደሚቀርቡ ታውቋል። የሕክምና ቁሶቹ ከሆስፒታሎች በተጨማሪ የሕክምና ትምህርት ለሚሰጡ የሕክምና ተቋማት ለማስተማሪያነት እንዲጠቀሙት ታስቦ እንደሚሰራጭም አምባሳደሩ አስረድተዋል።
የኢፌዴሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ፣ የድጋፉ አላማ መንግሥት የህክምና አገልግሎቱን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑ መግለጻቸው የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል።ድጋፉ በዩኒቨ ርሲቲዎችና የህክምና ስልጠና በሚሰጡ ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል መንግሥት እያደረገ የሚገኘውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ አገሪቱ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው የልማት ሥራዎች ጋር የተጣጣመ ነው።የሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ትብብርም ለበርካታ ዓመታት የዘለቀና የሚደረገው የልማት ድጋፍም እየተስፋፋ መጥቷል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጃፓን የሚያደርጉት ጉብኝት የአገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከሩ ረገድ ሚና እንደሚኖረውም አቶ አድማሱ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳህራላ አብዱላሂ በበኩላቸው ግዥ ከሚከናወንባቸው የህክ ምና መሳሪያዎች መካከል እንደ ማይክሮስኮፕ፣ ማሞግራፊ፣ ኢንዶስኮፒና ሌሎች እጥረት ያለባቸው መሳሪያዎች እንደሚገኙበት መግለጻቸውን ኢዜአ በዘገባው አመል ክቷል።
የሁለቱ አገራት የምጣኔ ሃብት ትብብር የጀመረው እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ነው። እ.ኤ.አ ከ1974ዓ.ም ወዲህ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር በተለያየ መልኩ ማሳደግ ችላለች።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
ቦጋለ አበበ