አዲስ አበባ:- በ2011 ዓ.ም ከመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለ90 ሺ ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ እድል መፈጠሩ ተገለጸ። ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢም ተገኝቷል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ትናንት አምስተኛ የምክክር መድረኩን ከተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራኖች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ በ2011 ዓ.ም 50 ሺ ቋሚ እና 40ሺ ጊዜያዊ የሥራ እድል ለዜጎች ተፈጥሯል።
አብዛኛውን ወጪና ገቢ ንግድ የሚደረገው በጅቡቲ በኩል ሲሆን፤ በዚህ መስመር በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች፣ በሠራተኞች ፍልሰት እና በአንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ በሚፈጠር ችግር ሠራተኞች ተረጋግተው ሥራቸ ውን መሥራት ባለመቻላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታማነታቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል። በመሆኑም ፓርኮቹ የሚያመርቱትን ምርት የሚፈለገውን ያህል ወደ ውጭ መላክ አልተቻለም። ይሁንና በ2011ዓ.ም የተገኘው ገቢ ከ2010 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የ35 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመንግሥት 12፣ በግል ኢንቨስተሮች ስምንት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት መቻሉን ጠቁመው፣ እንዲሁም ክልሎች ኃላፊነቱን ወስ ደው የሚያለሟቸው አራት አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መኖራቸውን አመልክተዋል።
በሚቀጥለው ዓመትም በመንግሥት አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገነባሉ ብለዋል። በመሆኑም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በመንግሥት ከሚገነቡ ፓርኮች ባሻገር የግል ኢንቨስተሮችን በማበረታታት በመጪው ሁለት ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር 30 ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከተሳታፊዎች የሚነሱ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የኮርፖሬሽኑን ዕቅዶች ሊያሳኩ የሚችሉ ሃሳቦችን አካቶ ተፈጻሚ በማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በውጤታማነት ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በባህር ዳር፣ በመቐለ፣ በድሬዳዋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከመንግሥት አካላትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን ማካሄዱ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011
ሶሎሞን በየነ