. በአምስት ክፍለ ከተሞች 121 ሚሊዮን 365ሺ 398 ብር ጉድለት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት የሂሳብ ጉድለት ከነበረባቸው 59 ተቋማት ውስጥ 32ቱ 66 ነጥብ 7ሚሊዮን ብር ለአስተዳደሩ ተመላሽ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር አስታወቀ። በ2011 በጀት ዓመት በሁለተኛው ግማሽ ዓመት በተሰራው ልዩ ኦዲት በአምስት ክፍለ ከተሞች በድምሩ 121 ሚሊዮን 365 ሺ 398 ብር ጉድለት መመዝገቡ ተገለጸ ።
የአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፅጌወይን ካሳ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያው ስድስት ወራት በተከናወነው የኦዲት ሥራ በ59 ተቋማት ላይ የሂሳብ ጉድለት ተገኝቷል። ዋና ኦዲተሩ ያገኘውን ግኝት መሰረት በማድረግ የከተማዋ ዓቃቢ ህግ ተቋማቱን ተጠያቂ ለማድረግ አቅጣጫ የተላለፈ ቢሆንም በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት 32ቱ ተቋማት 66 ሚሊዮን 774 ሺ 741 ብር ከ75 ሳንቲም ተመላሽ ተደርገዋል።
እንደ ዋና ኦዲተሯ ማብራሪያ፤ ተቋማቱ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ውዝፍ ሂሳብ፣ ተመላሽ ያልተደረገ ቅድመ ክፍያ፣ የተሰብሳቢ ክፍያ፣ ከመመሪያ ውጭ የተከፈለ፣ አበልና ደመወዝ በብልጫ የተከፈለ፣ ያለአግባብ ግዥ ፈፅመው ተመላሽ የተደረጉ መሆናቸው በተደረገው ምርመራ ለማወቅ ተችሏል። በዚህ መሰረትም አስተዳደሩ የተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋት ጥብቅ አቅጣጫ በማስተላለፉ አብዛኞቹ ተቋማት ስህተቶቻቸውን በማረም የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግበዋል።
ይሁንና ቀሪዎቹ 27 ተቋማት ዋና ኦዲተሩ ላቀረበው ጥሪ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለመስጠታቸውን ወይዘሮ ፅጌወይን አመልክተው፣ ከእነዚህ ተቋማት መካከልም 40/60 የቤቶች ኢንተርፕራይዝ፣ መንገዶች ባለስልጣን፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ዘውዲቱ ሪፈራል ሆስፒታልን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ተቋማቱ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ያቀረበላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል። «በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ እንዳለ ሆኖ ተቋማቱ በዋናነት ወደ ህጋዊና ዘመናዊ ስርዓት እንዲገቡ ማድረግ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው» በማለትም አክለዋል።
እንደ ዋና ኦዲተሯ ማብራሪያ፤ በ2011 በጀት ዓመት በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ልዩ ኦዲት የተሰራ ሲሆን በተለይም በአምስት ክፍለ ከተሞች ላይ የክዋኔ ኦዲት ሥራ በማከናወን በድምሩ 121 ሚሊዮን 365ሺ 398 ብር ጉድለት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል። ከእነዚህም መካከል ኮልፎ ቀራኒዮ ክፍለከተማ ያልተከፈለ የቅድመ ክፍያ 69ሺ563 ብር ከ35 ሳንቲም ጉድለት እንዲሁም ያልተከፈለ የሊዝ እዳ የወቅቱን የወለድ ምጣኔ ጨምሮ ወደ 40 ሚሊዮን 115ሺ 610 ብር ከ58 ሳንቲም ተገኝቶበታል። በተመሳሳይም በቦሌ ክፍለ ከተማ ያልተከፈለ ቅድመ ክፍያ 17 ሚሊዮን 110ሺ23 ብር ከ91 ሳንቲም ሲገኝበት ያልተከፈለ የሊዝ ክፍያ ደግሞ የወቅቱን ወለድ ጨምሮ ወደ 26 ሚሊዮን 806ሺ ብር ከ95 ሳንቲም የሚጠጋ ገንዘብ ጉድለት ታይቷል። ከአምስቱ ክፍለ ከተሞች ውስጥ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተሻለ አፈፃፀም የታየበት ሲሆን፣ የተገኘበትም ያልተከፈለ የሊዝ እዳ 40ሺ 342 ብር ከ50 ሳንቲም ብቻ ነው።
በክዋኔ ኦዲቱ ዝርዝር ኦዲት መሰራቱን ያመለከቱት ወይዘሮ ፅጌ፣ በተለይም በአምስቱ ክፍለ ከተሞች ታጥረው የተቀመጡ፥ የግንባታ አፈፃፀማቸው ከ30 በመቶ በታች የሆነ ተቋማት ላይም የአፈፃፀም ምርመራ መካሄዱን አስገንዝበዋል። ለአብነት ያህልም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 57 ባለይዞታዎች ግንባታቸው ያልተጀመረና ከ30 በመቶ በታች ሆነው የተገኙ መሆኑን በኦዲቱ ማጣራት መቻሉን አመልክተዋል። በተመሳሳይም በቦሌ ክፍለ ከተማ 60፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ 106 ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወደ 15፣ አዲስ ከተማ ክፍለከተማ 24 የሚሆኑ ባለይዞታዎች ግንባታቸው ሳይጀመርና አፈፃፀማቸው ከ30 በመቶ በታች መሆኑን እንደታወቀ አስረድተዋል።
በመሆኑም አጠቃላይ የኦዲት ግኝቱን ለአስተዳደሩም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት የተላከ መሆኑን ወይዘሮ ፅጌ ወይን አመልክተው፣ ጉድለት የታየባቸው ተቋማትና ክፍለከተሞች ሪፖርቱን መሰረት አድርገው አጭር ጊዜ ውስጥ አሰራራቸውን ያስተካክላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ጎን ለጎንም በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ የሚቀጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
ማህሌት አብዱል