ሠላም ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ላለፉት ጥቂት ሳምንታት አልተገናኘንም ነበር። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። መቼም በእናንተ በኩል የትምህርት ወቅቱ ከወትሮው በተለየ መልኩ ጠንከር እንደሚል እና የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ፈተና እየተቃረበ እንደመጣ እገምታለሁ። የአያቴ ታሪኮችም እንደሚናፍቃችሁ አልጠራጠርም። ምክንያቱም እርሷ አስተማሪ እና አዝናኝ ታሪኮችን በየጊዜው ስለምትነግረን ነው።
አሁን ያለንበት ወር ታህሳስ ነው። ለመሆኑ ልጆች ታህሳስ በመጣ ጊዜ ምን የተለየ ነገር ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ? የአያቴ ጣፋጭ ታሪክ ለእናንተ ከመንገሬ በፊት በታህሳስ ወር ውስጥ ስለሚከናወኑ ተግባራት ልንገራችሁ። የመጀመሪያው በክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በዓል የሚከበርበት ወቅት ነው። ምዕራባውያን ደግሞ የገና ወቅት የዘመን መለወጫቸው በመሆኑ ወሩን በልዩ በዓል እና የደስታ ሥነ- ሥርዓት ያከብሩታል። ስለዚህ ይህ ወር በርካታ ዓለም አቀፋዊ ክብረ በዓላትን የሚያስተናግድ ነው።
እንደሁል ጊዜው እኔና አያቴ በግቢያችን ውስጥ ባለው የዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠናል። እሁድ ቀን ነው። እርሷ በጠዋት ተነስታ ቤተክርስቲያን ተሳልማ መጥታለች። በዕለቱ ያሳለፍኩትን የትምህርት ሳምንት እንዴት እንደነበር እየነገርኳት ነበር። «ልጄ ወደፊት ምን አይነት ሰው መሆን ነው የምትፈልገው?» በማለት ድንገት ጥያቄ አነሳችብኝ። እኔም «ትልቅ ስሆን ብዙ ገንዘብ እና ንብረት ያለው ሀብታም መሆን ነው» ስል መለስኩላት። ምክንያቱን ስትጠይቀኝ ግን ልመልስላት አልቻልኩም። በዚህ ምክንያት እራሴን እንዳውቅ ያደረገኝን አንድ አስተማሪ ታሪክ እንዲህ ስትል አጫወተችኝ።
ከብዙ ዓመታት በፊት በአንድ አነስተኛ መንደር ውስጥ ከሚወዳት ሚስቱ ጋር የሚኖር ሸማኔ ነበር። ይህ ሰው በመንደሩ ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች እጅግ ውብ የሆነ ልብስ እየሠራ በመሸጥ ይተዳደራል። ሆኖም በሚያገኘው ገቢ ደስተኛ አይደለም። በመንደሩ የሚኖሩ በርካታ ሸማኔዎች ከእርሱ የተሻለ ገቢ እና ሀብት ነበራቸው። ጥራት ያለው የሽመና ሥራ የሚሠራው ግን እርሱ ነበር። ይህ ሁኔታ እጅጉን ያሳስበው እና ያበሳጨው ነበር። ብዙ ገንዘብ ያለው ዝነኛ ሀብታም መሆንም ይፈልግ ነበር።
ከዕለታት በአንዱ ቀን የተለመደውን የቀን ሥራውን አከናውኖ ምሽት ላይ እቤቱ ይገባል። እጅግ በጣም ደክሞት እና ድብርት ውስጥ ገብቶ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በሥራው ደስተኛ ያለመሆኑ ነው። ጉዳዩን ለሚስቱ አማክሮ አንድ መፍትሄ ላይ መድረስ እንዳለበት ወሰነ። በዚያው ቀን ማታም «ውዴ ለብዙ ዓመታት በሽመና ሥራ ላይ ብቆይም እንደ ሌሎቹ ጓደኞቼ ባለፀጋ መሆን አልቻልኩም። ስለዚህ ይሄ ከተማ ለእኔ ስለማይሆን ወደ ሌላ አካባቢ ተጉዤ ገንዘብ ማጠራቀም ይኖርብኛል» በማለት ነገራት።
የሸማኔው ሚስት ግን በባሏ ሃሳብ አልተስማማችም። ምክንያቱም ለኑሯቸው በቂ የሆነ ገንዘብ ስላላቸው እና ከዛ አልፎ ባለፀጋ መሆን አስፈላጊነቱ ስላልታያት ነበር። በዚህም «ውዱ ባለቤቴ ሙያህን እወደዋለሁ። በምትሠራው ሥራም ደስተኛ ነኝ። ለኑሯችን በቂ ገንዘብ አለን። ስለዚህ ወደ ሌላ አገር መሄድህ ትክክል አይደለም» በማለት የባሏን ሀሳብ ተቃወመች። እርሱ ግን በሚስቱ ሀሳብ ሊስማማ አልቻለም። እንደጓደኞቹ ባለፀጋ መሆን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከተማውን ለቆ መውጣት ይኖርበታል። በመሆኑም በውሣኔው ፀንቶ እርሱ ከሚኖርበት መንደር ርቆ የተሻለ የገበያ አማራጭ ያለበት ከተማ ሄደ። በዚያም እርሱ እንደሚፈልገው ጥሩ ገበያ አገኘ።
ከሚስቱ እና ከሚወደው መንደር ርቆ የሽመና ሥራውን ለሦስት ዓመታት ሲሰራ ቆየ። በሥራውም ደስተኛ ሆነ። ባለፀጋ የሚያረገው እጅግ ብዙ ገንዘብ እና ወርቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት ቻለ። በዚህ ጊዜ «አሁን ወደ ባለቤቴ እና ወደ የምወደው ከተማ መመለስ ይኖርብኛል» ብሎ ጉዞውን ወደ ቀድሞ መኖሪያው አደረገ። መኖሪያ ስፍራው ለመድረስ ግን ብዙ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ይኖርበታል።
ሸማኔው ባለፀጋ ከብዙ ቀናት ጉዞ በኋላ ወደ ከተማው ለመግባት ተቃረበ። ጉዞው አድካሚ ስለነበር በአንድ በጫካ የተሞላ ስፍራ እረፍት አድርጎ በነጋታው ለመሄድ ወሰነ። በድንገት ግን ዕረፍት ባደረገበት ቦታ ላይ እንግዳ ድምፅ ሰማ። የሚታይ ባይሆንም ሁለት ሰዎች ይወያዩ ነበር። ድምፁ ግን ከሰው አንደበት የሚወጣ አይደለም። በንፋስ መልክ ነው የሚሰማው። ንግግሩ እንዲህ የሚል ነበር።
«ትሰማኛለህ ለዚህ ሰው ይሄን ሁሉ ሀብት እና ወርቅ እንዴት ሰጠኸው። ይሄ ለርሱ አይገባውም» ይላል ከወዲኛው የጫካው ጥግ የሚሰማው ድምፅ ደግሞ «እኔ ለዚህ ሰው ገንዘቡን የሰጠሁት በጠንካራ ሥራው እና ጥረቱ ነው። የሰውን ዕጣ ፈንታ ወሳኝ በመሆንህ የሚገባውን ልታደርግ ትችላለህ» በማለት ከወዲህኛው ጥግ ምላሽ ሰጠ። በዚህ መሃል ንግግሩን ሲያዳምጥ የቆየው ባለፀጋ ሸማኔ በድንጋጤ ገንዘቡን አጠራቅሞ የያዘበትን ቦርሳ በፍጥነት ተመለከተው። በሚያሳዝን ሁኔታ ያጠራቀመውን ወርቅ እና ገንዘብ ማግኘት አልቻለም። ዕጣ ፈንታ ሙሉ ገንዘቡን ሰወረበት።
ሸማኔው በሁኔታው እጅግ ተበሳጨ። የሦስት ዓመት ልፋቱ ከንቱ መሆኑ ሲገባው ወደ ሚስቱ እና መኖሪያ መንደሩ መመለሱ ተገቢ አለመሆኑ ገባው። በድጋሚ ሲሰራ የቆየበት ከተማ ለመመለስ እና ሀብት ለማጠራቀም ወሰነ። ወደ ቤተሰቦቹ ሲያደርግ የነበረውን ጉዞ አቋርጦ ተመለሰ። ለአንድ ተጨማሪ ዓመት የሽመና ሥራውን ሠራ። ቀድሞ ካገኘው ገንዘብ እና ወርቅ በላይ አጠራቀመ። ጥረቱ እና ልፋቱ በድጋሚ ከፈለው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ መሆኑ እያስደሰተው ወደ ትውልድ ስፍራው እና ባለቤቱ ለመመለስ ወስኖ ጓዙን ጠቅልሎ በድጋሜ ተጓዘ። ግን በመንገዱ ላይ ቀደም ሲል ያዳመጠውን ተመሳሳይ ድምፅ ሰማ። ውይይቱ በዕጣ ፈንታ እና በተግባር መካከል የሚደረግ ነበር። ዕጣ ፈንታ ሸማኔው በድጋሚ ባለፀጋ የሚያደርገውን ገንዘብ እና ወርቅ ማግኘት የለበትም በሚል አቋሙ ፀንቷል። ተግባር ደግሞ ልፋቱን እና ጥረቱን አይቼ ነው ሀብቱን የሰጠሁት ይላል። ተግባር ግን የመጨረሻ ውሳኔውን ለዕጣፈንታ ሰጥቶታል። በዚህ ምክንያት ዕጣ ፈንታ ከሸማኔው ላይ በድጋሚ ያፈራውን ሀብት ሰወረበት።
ሸማኔው በሁኔታው እጅጉን ተበሳጨ። በህይወቱ ሀብት ማፍራት እንደማይችል ሲያውቅ የእርሱ ወደ ሚስቱ እና ትውልድ መንደሩ መመለስ ትርጉም እንደሌለው በማመኑ እራሱን ለማጥፋት ወሰነ። በዚህ ጊዜ «ዕጣ ፈንታ» ሸማኔውን እንዲህ ሲል ተናገረው። «አንተ ሰው እራስህን ለማጥፋት ከመወሰንህ በፊት ሀብት ያፈራህበት ከተማ ተመልሰህ ሂድና ሁለቱ ሸማኔ ጓደኞችህ ጋር በየተራ ለሁለት ቀናት ቆይ። ያን ጊዜ አንድ ነገር ትማራለህ። እኔም ምን ያህል ትክክል እንደሆንኩ ትገነዘብና ታመሰግነኛለህ» አለው። እርሱም ሁኔታውን ለማወቅ ስለጓጓ ወደ ከተማው ተመለሰ።
ሁለቱ ጓደኞቹ አብረውት ሲሰሩ የነበሩ ሸማኔዎች ናቸው። አንደኛው በጣም ሀብታም ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ነገር የተረፈው ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአነስተኛ ገቢ ይተዳደራል። ከተማዋ ላይ እንደደረሰም የመጀመሪያውን ሁለት ቀናት በሀብታሙ ቤት አደረገ። ነገር ግን ይህ ባለፀጋ የሆነው ሰው ገንዘቡን ለሰዎች ማጋራት የማይወድ ከመሆኑም በላይ ሰዎችን በእንግድነት የማይቀበል ስግብግብ መሆኑን ተገነዘበ። ባለው የተትረፈረፈ ሀብት ከመደሰት ይልቅ የሚነጫነጭ ነበር።
ሁለቱን ቀናት ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሸማኔ ጓደኛው ጋር ቆየ። ያጋጠመው ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነበር። ደስተኛ፣ ሰው የሚወድ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ያለውን ተካፍሎ የሚበላ ነበር። ህይወት የሰጠችውን ዕጣ ፈንታም ሳይቃረን ተቀብሎ በሃሴት ይኖራል። ይህን በተመለከተ ጊዜ እስካሁን ሀብት ለማጠራቀም እና ባለፀጋ ለመሆን ሲለፋ እና ሲጥር የነበረበትን ጊዜያቶች መለስ ብሎ አስተዋለ።
ዕጣ ፈንታ ሊያሳየው የፈለገውን የህይወት መስመር በሚገባ ተገነዘበ። በሀብት ብቻ የሚገኝ ደስታ እንዲሁም የተደላደለ ህይወት እንደሌለ በአራቱ ቀናት ቆይታው ገባው። ባለቤቱም «ባለን ነገር በበቂ ሁኔታ ደስተኛ ኑሮ መምራት እንችላለን» ያለችው ትዝ አለው። በዚህም ወደ ቀድሞው ህይወቱ መመለስ እንዳለበት እና የእርሱ ዕጣ ፈንታም ይሄ እንደሆነ አምኖ ተቀበለ። ከዚያም ሁሉም ነገር ተገልፆለት ህይወቱን ከቤተሰቡ ጋር በድጋሚ ለማጣጣም ወደ ትውልድ ቦታውና ሚስቱ ተመለሰ። በደስታም መኖር ጀመረ።
አያቴ ጀምራ እስክትጨርስ በተመስጦ የሰማኋትን ታሪክ በዚህ መልኩ ጨረሰችልኝ። እኔም ከታሪኩ ብዙ ተማርኩ። ባለፀጋ ለመሆን ካልታደልኩ ባለኝ ነገር መደሰት መማር እንዳለብኝ፤ በተለይ ደግሞ የህይወት ትርጉሙ ሀብት ማሰባሰብ ብቻ አለመሆኑን ተገነዘብኩ። መቼም ልጆች እናንተም ይህን ታሪክ ስታነቡ ትልቅ ትምህርት ትወስዳላችሁ። መልካም ታሪኩንም እንደወደዳችሁት እገምታለሁ። የሳምንት ሰው ይበለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
ዳግም ከበደ