
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በደን ውጤቶች አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩን የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስታወቀ፡፡
በኦሮሚያ የደን ልማትና እንጨት ማቀነባበር ኢንዱስትሪ ላይ ባሉ ፈተናዎችና መፍትሄዎች ዙሪያ ትናንት በኢሊሌ ሆቴል ውይይት ተካሂዷል፡ ፡ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር ኃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቲ በኢትዮጵያ የደን ውጤቶች አቅርቦት አነስተኛ በመሆኑ ካለው ፍላጎት ጋር ሊጣጣም እንዳልቻለ ገልፀዋል፡፡
‹‹በደን ውጤቶች አቅርቦትና ፍላጎት በኩል ሰፊ ክፍተት ቢኖርም አሁንም መልካም አድሎች አሉ›› ያሉት ኃላፊው፤ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የደን ውጤቶችን ለማስቆም በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች የፋይናንስ ድጋፍና የረጅም ጊዜ ብድር በአነስተኛ ወለድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የግሉ ሴክተር በደን ልማት ዘርፉ እንዲሰማራ ማበርታት፣ ለደን ልማት አመቺ መሬቶችን ማቅረብና ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍም እንደሚገባ ኃላፊ አሳስበዋል፡፡
በደንና በደን ውጤቶች ዙሪያ የሚሰራ ራሱን የቻለ ሴክተር ሊኖር እንደሚገባም ኃላፊው አያይዘው የጠቆሙ ሲሆን፤ በተለይ በደን ችግሮች ዙሪያ ውይይቶችን የሚያካሂድ፣ ችግሮችን በመለየት ለመንግሥት የሚያቀርብና ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ አጀንዳ የሚቀርፅ የተደራጀ ሴክተር መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል። ለዚህም ከመንግሥት፣ ከግልና ከአጋር ድርጅቶች የተውጣጣ ግብረኃይል ማቋቋም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
አስናቀ ፀጋዬ