
አዳማ፡- በኦሮሚያ ክልል አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አባወራዎች የጤና መድን ኢንሹራንስ አባል መሆናቸውንና ከአባላቱም 310 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። እያደገ ከመጣው የጤና መድን ኢንሹራንስ ጋር የሚጣጣም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ለማከናወን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በክልሉ ካሉት 333 ወረዳዎች በ247 ወረዳዎች የጤና መድን ኢንሹራንስ አገልግሎት የተጀመረባቸው ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከልም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ፣ሰሜንና ምዕራብ ሸዋ፣ቦረና አካባቢዎች ከ60 በመቶ በላይ አባላት ማፍራት የተቻለባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በፀጥታ ችግርና በተለያየ ምክንያት ደግሞ አፈጻጸማቸው ከ15 በመቶ በላይ ተደራሽ አለመሆኑ ተመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ ዓመት በከተሞች ላይ የተጀመረውም አበረታች እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ደረጃ አፈጻጸሙ እንዲህ በተለያየ ደረጃ ላይ ቢሆንም፣በህዝቡ በኩል አባል የመሆን ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በሰው 250 ብር በመክፈል ዓመቱን ሙሉ ከነቤተሰብ አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን በመጠቆም የጤና መድን ኢንሹራንስ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በተሟላ የህክምና መሳሪያና ተገቢውን አገልግሎት በሚሰጥ ባለሙያ ጠንካራ ሥራ ካልተሰራና በተገልጋዩ እርካታ ከሌለ አሁን የተፈጠረው ተነሳሽነትም ሆነ አባል የሆኑት ክፍያቸውን የሚያቋርጡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አስረድተዋል፡፡
በክልሉ አሁን ባለው ወደ 30 በመቶ የሚሆኑት የጤና ድርጅቶች ጥሩ በሚባል ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ከህብረተሰቡ ግብረ መልስ በመሰብሰብ ማረጋገጣቸውን የጠቆሙት ዶክተር ደረጀ የጤና መድን ኢንሹራንስ መድን ዓላማን ካለማወቅና ሙያዊ ግዴታን ባለመወጣት የሚስተዋሉ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚገባና በ2012 በጀት ዓመት እንደሚስተካከል አመልክ ተዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት በስፋት በመንቀሳቀስ የተጠቃሚውን ቁጥር ወደ 90 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ለህክምናው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንዲቀርቡ፣ባለሙያውም ሙያዊ ግዴታውን እንዲወጣ በትኩረት ቢሮው ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመው ፣ለበለጠ ስኬት በየደረጃው ያለው አመራርም ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሰንዳፋ፣ጫንጮ እንዲሁም አርሲ ነገሌ፣ሐረርጌ ውስጥ ሚጋቶዴና ጉርሱም የሚባሉ አካባቢዎችን ጨምሮ እያንዳንዳቸው እስከ ሁለት መቶ ሺ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ ከሶስት ዓመት በፊት ከተገነቡት 16 ሆስፒታሎች 10 ሆስፒታሎች በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ደረጀ በውጭ ምንዛሪ እጥረት አስፈላጊው ግብዓት ባለመሟላቱ አገልግሎቱ የተጓተተ መሆኑንና በአዲሱ በጀት ዓመት ችግሩ ተፈቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በውሃና በመብራት ችግሮች ሳቢያ 50 በመቶ የሚሆኑት የጤና አገልግሎት መስጫዎች የተሟላ የወሊድ አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው በፀሐይ ኃይል ለመጠቀም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
ለአደጋ እና ለወላዶች አገልግሎት የሚሰጡ ወደ ዘጠኝ መቶ የሚሆኑ አንቡላንሶች ቢኖሩም በተገቢው ለታለመለት ዓላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግና የወረዳ አመራሩ አገልግሎቱን እንዲገመግመው በማድረግ ጭምር ይሰራል ብለዋል፡፡በአዲሱ በጀት ዓመት ለግንባታ፣ለሥራ ማስኬጃ፣ሶስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በጀት ለዘርፉ መመደቡንም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011
ለምለም መንግሥቱ