«ረቢሞ ነሙማ ከንሴራ ጀልሴ»
«ሃት ኬኛ ቶኮ ማልቱ አዳኑ ባሴ…»
ጆሮን በጥዑም ዜማ እየሰረሰረ ልብን የሚያረሰርሰው የአርቲስት አሊ ሙሃመድ ሙሳ፤ (በመድረክ ስሙ አሊ ቢራ) ዘፈን ላይ የተቀነጨበ ነው። ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ነበር አድማጭ ደጅ የደረሰው። ጥሬ መልዕክቱን ወደ አማርኛ ስንመልሰው እንዲህ የሚል ትርጉም ይሰጠናል።
«አምላክ ነው ወይስ ሰው?
ሕግን የጣሰው እናታችን አንድ ነች ምን አለያየን…?»
ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም ጥዑመ ዜማው ሰርክ አዲስ ሆኖ በድጋሚ ሊሞግተን፤ የማህበረሰባችንን እሳቤ እና ፅንፍ የወጣ ጎጠኝነት ምንጭ «ምን ይሆን?» ብሎ ሊጠይቀን ዳግም ቤታችንን እያንኳኳ ይገኛል። ከሃምሳ ዓመታት በላይ የሙዚቃ እና ኪነ ጥበብ አድናቂዎቹን አንጀት ሲያርስ የነበረው ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራም ህያው ከሆነው ዘፈኖቹ ጋር የወገኖቹ ህመም ለሆነው በሽታ ፈውስ ሊፈልግ አለሁ ብሏል።
ድሬዳዋ ነው የተወለደው። ከጎጠኝነት እና ፅንፍ ከወጣ ብሔርተኝነት ይልቅ አንድነት፣ አብሮ መኖር፣ መተሳሰብ እና ፍቅር ይገዛዋል። ከብሔሩ በላይ አገሩን፣ ከአገሩ በላይ ሰው መሆንን ያስቀድማል። ይህን ድንቅ ማንነት ያገኘው ታዲያ ከልቡ በሚወዳት የተወለደባት ከተማ ድሬዳዋ በመኖሩ ነው።
ዛሬ ግን ይህ እሴት ሊሸረሸር ጫፍ መድረሱን ያስተዋለው አርቲስቱ እና ሌሎች የሙያ አጋሮቹ ሳይቃጠል በቅጠል ብለው እኩያኖችን ቀልብ ግዙ ለማለት በድሬ ባህል በ «ሙከጀላት እና ጌድ ሆስት» የዛፍ ጥላ ስር ሽምግልና የኢትዮጵያውያንን የጋራ ከተማ እሴት ለመጠበቅ ኑ በጋራ ቤታችንን እናፅዳ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት።
ታዲያ ከቃል በላይ ሙዚቃዬ መልዕክቴን በሚገባ ያስተላልፍልኛል ሲል «እናታችን አንድ ሆና ማን ይሆን የለያየን?» አንድነታችንን ምን አደጋ ላይ ጣለው በማለት ኑ እንደ ባህላችን ዛፍ ጥላ ስር ሆነን እንመካከር ሲል ነው ጥሪውን የሚያስተላልፈው።
የድሬ ሕዝብ በጣም ተግባቢ፣ እንግዳን የራሱ ቤተሰብ አድርጎ የሚቀበል መሆኑ በተለያየ አጋጣሚ ይነገራል። በአካል ደጃቸውን የረገጠም እውነታውን በተግባር አረጋግጦ ለመመስከር ቸኩሎ ይመለሳል። ነገሮችን ሁሉ ቀለል አድርጎ የሚያይ፣ የማያጨናንቅና ፈታ ያለ ነዋሪ መሆኑን ላገኘው ሁሉ ያበስራል። «ለሥራም ሆነ ለመዝናናት ወደ ድሬዳዋ የመጣ ማንም ሰው ካለምንም ችግር ጉዳዩን ፈፅሞ
የሚመለስባት ተወዳጅ ከተማ ነች» ሲል ነጋሪት ይጎስማል። በምሥራቅ በኩል የፀሐይ መውጫ ከሆኑት ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ድሬ በበርካታ ከያኒያን ዘንድ ስትወደስ፣ ስሟ ሲጠራ ስትንቆለጳጰስም ኖራለች። ቋንቋ፣ቀለም ብሎም ዘር በድሬ ይብሱኑ የሚያግባባ እንጂ የሚያራርቅ የልዩነት ሽብልቅ አይደለም።
ተወዳጇ ከተማም “የእኔና የእኛ” በሚል ስሜት በተወጠሩ ግለሰቦች ሰላሟ ታውኮ፣ እንደቆዳ ተወጥራለች። ድሬ ቆንጥጣ ያሳደገቻቸው እና ከጉያዋ የወጡ እውቅ ልጆቿ ደግሞ «ፍፁም ይሄ የእኛ ባህል አይደለም» ችግር እንኳን ቢኖር የምንፈታበት ልዩ እሴት አለን ሲሉ የእናት ከተማቸው ህመም ሳይጠና ፈውስ ሊሹ ከወዲያ ወዲህ እያሉ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከል ዓለም አቀፍ ሞዴል ፈቲያ መሀመድ ትገኝበታለች። በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የሞዴሊንግ ውድድሮች ላይ ተሳትፋ አሸናፊ ሆናለች። አሁን ዓለም አቀፍ ሞዴል ነች። በ2018 በማሌዢያ ሚስ ንግስት ውድድር አሸናፊ፣ በቡልጋሪያ የሚስ ፕላኔት ውድድር ሁለተኛ የወጣች እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ዓለም አቀፍ የሞዴሊንግ ውድድር የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አሸናፊ ስትሆን፤ ድሬ ካፈራቻቸው ስኬታማ ግለሰቦች ውስጥ ትመደባለች። ዛሬ ላይ የወገኖቿ ሰላም መደፍረስ እና እዚህም እዚያም የሚፈጠር ስጋት አሳስቧት አርቲስት አሊ ቢራን ጨምሮ ከወዳጆቿ ጋር አብራ የችግሩን ማርከሻ እነሆ ለማለት መሰናዶዋን አጠናቃለች።
«ሙከጀላት እና ጌድ ሆስት» በድሬዳዋ ከተማ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል በዛፍ ጥላ ስር የሚደረግ የሽምግልና ሥነ ሥርዓት ነው። የተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲከሰቱ፤ በግለሰቦች መሃል አለመግባባት ሲፈጠር የአገር ሽማግሌዎች፣ኡጋዞች፣እናቶች እና ወጣቶች በዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበው ምክክር በማድረግ ችግሩን የሚፈቱበት እሴት ነው። በዚህ እውቅ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት ነው ዓለም አቀፍ ሞዴል ፈቲያ እና መሰል አጋሮቿ ያደጉት። ታዲያ አሁን ላይ ባህላዊ እሴቶች ፈር ሲለቁ ከመተሳሰብ እና ከአብሮነት በላይ ጎጠኝነት ሲነግስ እነዚህ የድሬ ፈርጦች ወደኋላ እንመልከት፣ ማንነታችንን አንዘንጋ፣ ባህላችንን አንርሳ «ኑና በዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበን ልዩነታችንን በምክክር እንፍታ» በማለት እሴቶቻቸውን ለማበልፀግ የተነሱት።
ዓለም አቀፍ ሞዴል ፈቲያ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ የድሬዳዋ ተወላጅ የሱማሌኛና ኦሮምኛ ዘፋኝ አቶ የኑስ አብዱላሂ፣ ስኬታማው የንግድ ሰው እና የናሁ ቴሌቪዥን ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው እንዲሁም ሌሎች እውቅ የከተማዋ ልጆች እና መላው የድሬዳዋ ማህበረሰብ የተጣላን በማስታረቅ፣ አብሮነትን በማበልፀግ፣ የተሰበረ ማህበራዊ ሕይወትን የሚጠግኑ ሳይንሳዊ ቤተ ሙከራዎች እና ምርምሮች የማይፈቷቸው ባህላዊ ሀብቶች አሉን ይላሉ። መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያስረዳውም የእነርሱን ቃል ነው።
አሁን አሁን እነዚህን ወርቆች እንደመዳብ የመቁጠሩ ነገር መፈጠሩን ተገንዝበዋል። የበይ ተመልካች ከመሆን ለመትረፍ ወደራሳችን እንመልከት የሚል ጥሪ የሚያስተላልፉትም ለዚሁ ነው። አብሮነት ሲደበዝዝ፣ መገፋፋት ሲበረታ «አንተም ተው/አንቺም ተይ» ከሚባባሉበት ባህላዊ ሀብቶች ውስጥ ደግሞ ግዙፉ ወርቃቸው «የሙከጀላት እና ጌድ ሆስት» የዛፍ ጥላ ስር ሽምግልና ነው።
ለተወዳጇ ከተማ የተቆረቆሩት እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች «ድሬዳዋን የምናውቃት በህብረ ብሔራዊነቷ፣በሰላሟ፣በፍቅሯ፣በእውነተኛ እንግዳ ተቀባይነቷ የምሥራቅ ፈርጥ በመሆኗ ነው» ይላሉ። የዛፍ ጥላ ስር የሚደረገው የሽምግልና ሥነ ሥርዓትም ቀደም ባለው ትውልድ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፈ ነበር። አሁን አሁን ማህበረሰቡ ከእነዚህ አገር በቀል ትሩፋቶች እየራቀ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ማሳያ የሆኑ እሴቶች እየተሸረሸሩ መለያየትን የሚሰብኩ አስተሳሰቦች እየጎሉ መምጣት መጀመራቸው አሳስቧቸዋል። ለዚህ ደግሞ ድሬ ያበቀለቻቸው ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንድ መላ ዘይደዋል።
የፊታችን ነሐሴ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድሬን ሰላም ለማናጋት ዳር ዳር የሚለውን እኩይ እሳቤ በእንጭጩ ለመቅጨት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ የመጣውን ባህላዊ እሴት ለመመለስ በድሬዳዋ ከተማ ሚሌኒየም ፓርክ የሙከጀላት እና ጌድ ሆስት የዛፍ ጥላ ስር ባህላዊ የሽምግልና ሥነ ሥርዓት አዘጋጅተዋል። በዚህ ዝግጅት ላይ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች የሚቀርቡ ሲሆን በከተማዋ ብቻ የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች ለእይታ የሚቀርቡ ይሆናል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ኡጋዞች፣ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች፣ በከተማዋ ተወልደው ያደጉ የውጭ አገር ሰዎች እና የተለያዩ የማህበረሰቡ ክፋዮች ይታደማሉ። አሁን ከጉያዋ የወጡ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የከተማዋ ነዋሪን በዛፍ ጥላ ስር ለማሰባሰብ ጫፍ ላይ ደርሰዋል። ሊታመም ዳር ዳር እያለ ስለሚገኘው ሰላማቸው እንዲመክሩ ዕድሉን ይፈጥራሉ። ይህ ሥነ ሥርዓት ታዳሚውን በተለይ ደግሞ ወጣቱን ከባህሉ እና ከማንነቱ ጋር ዳግም የማስታረቅ ዕድል እንደሚፈጠርም ነው የሚጠበቀው።
በዓለም አቀፍ ሞዴል ፈቲያ ሃሳብ አመንጪነት በክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች አጋፋሪነት ድሬዳዋ ልጆቿን ለመገሰፅ ተዘጋጅታለች። «መጀመሪያ ቤታችንን ጠርገን ነው ግቢያችንን የምናፀዳው» በማለት በቀጣይ በኢትዮጵያውያን ቱባ ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓት መላው አገሪቷ ላይ መሰል ሥነ ሥርዓቶችን እንደሚያሰናዱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
እኛም የፊታችን ነሐሴ 4 «መልካም አገልግል» ሰንቀው የሰላም አየር ለመዝራት ወደ ድሬ የሚያቀኑትን የድሬ አድባሮች መንገድ የስኬት እንዲሆን ተመኘን። እውቁ ዘፋኝ ፀጋዬ እሸቱ ደግሞ እንዲህ እያለ ትውስታን ይጭራል::
«እሄዳለሁ ድሬ ባቡር ተሳፍሬ፤ያችን ጉብል ወጣት አያታለሁ ድሬ…»
«መገን የድሬ ልጅ ፀባይ ምግባራቸው፣እንግዳ ያለምዳል አቀራረባቸው…»
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2011
ዳግም ከበደ