የመጽሐፉ ርእስ ተወልደ ብርሃን የምድራችን ጀግና የሕይወት ታሪክ
አዘጋጅ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ
የገጽ ብዛት 520
የመጽሐፉ ዋጋ ሁለት መቶ ብር
ኅትመት ማንኵሳ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤
መጠኑ ትልቅ መጽሐፍ ነው።
ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ቀደም ሲል በምጽዋ የባሕር ኃይል ባልደረባ ሆኖ ሀገሩን ያገለገለ፤ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ በርካታ ጽሑፎችን ያስነበበና በግሉም ከፀሐይ በታች በሚል የቴሌቪዥን ፕሮግራም (የአንድ ሰው ቶክ ሾው) ወቅታዊነት፤ አስተማሪነት፤ አስገራሚነትና አዝናኝነት ያላቸውን ሥራዎች በቴሌቪዥን ተመልካቾች ዘንድ ይታወቃል።
በድርሰት ረገድ ቀደም ሲል ሕይወት በባሕር ውስጥ (1985)፤ማስታወሻ በደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር (የዶክተር ተወልደ ብርሃን ወንድም) የሕይወት ታሪክ ላይ ያተኮረ (1983፤2006)፤ ልጅነት (2000)፤ መልኅቅ (2010) የተሰኙ ሥራዎቹን ያስነበበ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ለዕፀዋት ህልውና ጥብቅና በቆሙት ተመራማሪ በዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ሥራውን ይዞልን ቀርቧል።ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ በሀገራችን የሁለት ወንድማማቾችን የሕይወት ታሪክና ሥራ ተከታትሎ በመጻፍ የመጀመሪያው ሰው ነው ለማለት ይቻላል።
ዶክተር ተወልደ ብርሃን በአካባቢ ጥናት ጉዳይ፤ በሥነ ሕይወት፤ በብዝኀ ሕይወትና በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፤ በዕፀዋት ስያሜ ፕሮጀክት (ኢትዮጵያን ፍሎራ ፕሮጀክት) ላይ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር አድርገው ዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኙና የምድራችን ጀግና የሚል የክብር ስም የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ጀግና ናቸው።
ዶክተር ተወልደ የዕፀዋት ዘረመል እንዲቀጥል፤ የተስተካከለ ሥነ ኑረትና ሚዛናዊ የአየር ንብረት እንዲኖር፤ የምድሪቱ የተፈጥሮ ጸጋ በድርቅና በፀሐይ ሙቀት ምክንያት እንዳይገፈፍ፤ ዕፀዋት በጎርፍ ምክንያት ከለም ዐፈር ጋር ተጠራርገው እንዳይሄዱና ምድራችን ምድረ በዳ እንዳትሆን ከልጅነታቸው ጊዜ አንሥቶ በዕፀዋት ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ሲመራመሩ የኖሩና ለውጤትም የበቁ ሳይንቲስት ናቸው።
የዕፀዋት ስያሜ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲሆን ካላቸው ቀናዒነትና ተቆርቋሪነት የተነሣም የኢትዮጵያ ወጣት ተመራማሪዎችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ሕይወት ዲፓርትመንት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ስዊድን ልከው እንዲማሩ አድርገዋል።በፕሮጀክቱ ከተማሩት ውስጥ ዶክተር መስፍን ታደሰ፤ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው፤ ዶክተር ዘመዴ አስፋውና ሌሎች መሆናቸውን ዘነበ በጻፈው የዶክተር ተወልደብርሃን ታሪክ ላይ ያስነብበናል።
ዕፀዋትና ደኖች የሕይወት እስትንፋሶች፤ የደስታ ምንጮችና የተፈጥሮ ውበት መናኸሪያዎች፤ የብልጽግና ምልክቶችና የሕልውና መሠረቶች ስለሆኑ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዶክተር አብይ አህመድ አሳሳቢነት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም «የአረንጓዴ አሻራ ቀን» በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀገራችን አረንጓዴ ካባ እንድትለብስና የድርቅን መቅሰፍት እስከመጨረሻው ተቋቁማ እንድታስወግድ በሚሊዮን የሚገመቱ ችግኞች በየተራራውና በየጋራው፤ በየሜዳውና በየጥጋጥጉ እንዲተከሉ መደረጉና እንክብካቤም ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑ ዶክተር ተወልደ ብርሃንን ጨምሮ በዘርፉ የተሰለፉ ባለሙያዎችንና ቅን ዜጎችን ሁሉ የሚያስደስት ነው።ለምሳሌ ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች በኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ስለሚያደርጉ ነው።
ቻይናውያን ከከተማ እስከ ገጠር የተፈጥሮ ሀብታቸውን ጠብቀው ይኖራሉ።በዚህም በቻይና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፤ እንክብካቤ አያያዝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ይታያል።የቻይና ተራራ በደን ፤ ሜዳና ረባዳው በአዝርዕት ፤ በአትክልትና በፍራፍሬ የተሸፈነ በመሆኑ ሁልጊዜ አረንጓዴ ነው።
በአብዛኛው የቻይና ሜዳ ውሃ ገብ በመሆኑ በሩዝ ሰብልና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጨናንቆ ሲታይ ለመንፈስ ፍስሐን ይሰጣል።በቻይና ያፈጠጠና ያገጠጠ ተራራ ፤ ጦም ያደረ፤ የተራቆተ መሬት አይታይም።በልምላሜ የተዋቡ ተራሮችና ዳገታማ አካባቢዎች በፀሐይ ቃጠሎ እንዳይጠወልጉ ፤ ዐፈራቸው በዝናብና በነፋስ፤ በጎርፍና በማእበል እንዳይጠራረግ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ ያደርጋሉ።
ከዚህም የተነሣ ፤የተናደና የተንሸራተተ መሬት፤ያፈጠጠና ያገጠጠ ተራራ፤የተራቆተ ዳገትና በወራጅ ውሃ የተፈጠረ ዐፈር ገደልና ቁልቁለት አይታይም።ይልቁንም እያንዳንዱ ለም ዐፈር እንዳይጠረግ በእርከን ሥራ ጋራውና ሸንተረሩ፤ ተራራው፤ ሜዳውና ረባዳው በሽቦና በብረት ሰንሰለት እንደ እሥረኛ ተተብትቦና ተያይዞ አሸዋ ግርፍ ተገርፏል።
ከላይና ከሥር ደግሞ ሐረግና አበባ ተተክሎበት ፤ በላዩም ላይ እንደ ሐረግ ዘምቶበት የተለየ የተፈጥሮ ውበት ይታያል።የለመለመውን ሣር፤ የተለያየ ኅብረ ቀለም ያለውን አበባ በየዛፉና በየመንገዱ ዳር ግራና ቀኝ ያስተዋለ ሰው ወደማያውቃትና ልዩ ፕላኔት ወደ ሆነች ምድራዊት ገነት የገባ ያህል ስለሚቆጥረው የተለየ ደስታ ይሰማዋል።ማንም ሕዝብ የሥነ ኑረትን ሕግና ሥርዓትን አክብሮ ያለ ስንፍናና ያለ ሌብነት በቅንነት ከሠራ ዓለምን በቀላሉ ሊለውጣት እንደሚችል በ40 ዓመት ውስጥ ተምዘግዝጋ ያደገችው ቻይና እንደ ምሳሌ ልትሆነን ትችላለች።
በዚህ ረገድ ሌት ተቀን የሚታክቱ ወገኖቻችንን ፈር ተከትለን ለሀገር መሥራት ደግሞ የእያንዳንዳችን አቢይ ጉዳይ ሊሆን ይገባል።የዘነበ ወላ መጽሐፍ ዋነኛ መልእክትም ይኸው ይመስለኛል።
ዘነበ በብዝኃ ሕይወት ሀብት አጠባበቅ ላይ በጥልቀት በመሥራታቸውና በተለይም በዓለም አቀፍ ብዝኃ ሕይወት ድርድር ወቅት አፍሪካን ወክለው በጥንካሬና በአንድነት በመቆማቸውና በአእምሮ ንብረት ጥበቃ ላይ ምርምርና አስተዋጽኦ በማድረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ መርሐ ግብር (ዩኔፕ) እኤአ አፕሪል 21 /2006 «የምድራችን ጀግና »በሚል የሸለማቸውንና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራትም በርካታ ሽልማቶችን ያገኙትን የዶክተር ተወልደብርሃንን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ እነሆ ያለን በስድስት ክፍሎችና በ59 ምዕራፎች ከፋፍሎ ነው።ስድስተኛው ምዕራፍ በማውጫው ላይ ሳይገለጽ በገጽ 499 ላይ እናገኘዋለን።
የመጽሐፉ አወራረድ በባለጉዳዩ አንደበት በአንደኛ መደብ እንዲህ አደረግሁ፤ እንዲህ ሆነ -ይላል እንጂ ዘነበ በሁለተኛ መደብ የአተራረክ ስልት ጣልቃ ገብቶ እንዲህ ናቸው፤እንዲህ ዓይነት ሥራ ሠሩ አይለንም።የጻፈውም በአንቱታ ሳይሆን በአንተታ መሆኑ ከባለታሪኩ ጋር ያለውን ቅርርብ፤ ወዳጅነትና ቤተሰባዊነት ያመለክታል።በማውጫው ላይ እንደተጠቆመው «የብዝኃ ሕይወቱ ብርሃን ተወልደ» እና «ቅድመ ግለ ታሪክ » በሚሉት የመግቢያ ርእሶች ላይ ዘነበ ስለ ዶክተር ተወልደ ያቀረበውን ትንታኔ እናገኛለን።መጽሐፉ ጠቅለል ባለመልኩ ሲዳሰስ በክፍል አንድ በ23 ንዑሳን ርእሶች ስለዶክተር ተወልደ ብርሃን ግለታሪክ ማለት ስለልጅነት ፤ ስለትምህርት፤ ስለ ትዳርና የሥራ ሕይወታቸው፤ በክፍል ሁለት በሰባት ንዑሳን ርእሶች ስለ ትምህርት፤ ምርምራቸውና ምርምር የብዝኃ ሕይወት መሥሪያ ቤትን ስለመፍጠሩ፤ ስለኢትዮጵያና የብዝኃ ሕይወት ሀብቷ- ያሳያል።
በክፍል ሦስት በ14 ርእሰ ነገሮች ስለፕላኔታችን የአካባቢ ገጽታ፤ ስለዓለም አቀፍ ድርድርና ዝግጅት፤ ስለአዝርእት ባንክ፤ስለ ኮፐንሀገን፤ ስለፓሪስ ጉባኤና ሌሎች፤ በክፍል ዐራት በአምስት ርእሰ ጉዳዮች ስለአማራጭ ኖቤል ሽልማታቸው፤የክብር ዶክትሬት ስለማግኘታቸውና ስለሕይወት ዘመን ሽልማታቸው፤ በክፍል አምስት መጽሐፉ ይዘት በዝርዝር ሲታይ ደግሞ ምዕራፍ አንድ ተመራማሪው በእንባ ገረድ ትግራ ስለመውለዱና ልጅነት ጊዜውን፤
ከገጽ 288 ጀምሮ እስከ ገጽ 102 ድረስ ስለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ፤ ስለ ሽልማታቸው የሚያመለክቱ ታሪካዊነትና ማስታወሻነት ያላቸው ፎቶግራፎችን እናገኛለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)