በአገራችን አንዳንድ ጊዜ በተማሪዎቻችን ላይ የምንሰማቸው ድርጊቶች ያስከፉናል። በተለይ ከትምህርት ቤት እየቀሩ ቪዲዮ ቤት የሚውሉ ወይም በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ተማሪዎችን ጉዳይ ስንሰማ “እነዚህ ዱርዬዎች” ማለት ይቀናን ይሆናል።
በሌላ በኩል አሁን ካለው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አንጻር ህፃናትና ታዳጊዎች በቤት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው መንገዶች ሳያስጨንቀን አልቀረም። በተለይ ልዩ ልዩ የሞባይልና የኮምፒውተር ጨዋታዎችን የሚያዘወትሩ ህጻናትና ታዳጊዎች አብዛኛውን ወላጅ የሚያስጨንቅ ተግባር ነው። ካናዳዊው የ49 ዓመት ጎልማሳ ዴቭ ሄርዞግ ግን ከዚህ የወላጆች ጭንቀት በተለየ በልጁ ላይ የፈጸመው ተግባር ብዙዎችን አነጋግሯል።
እንደ ኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ይህ ሰው የልጁን የኤሌክትሮኒክስ ጨዋታዎች (ኢጌም) ችሎታ በመመልከት ልጁ ከትምህርት ቤት እንዲቀርና ሙሉ ትኩረቱን በጨዋታው ላይ እንዲያደርግ በማድረግ ትኩረት ስቧል።
መረጃው እንዳመለከተው ዴቭ ራሱ በልጅነቱ ጀምሮ የእንዲህ አይነት ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ጨዋታዎች ወዳጅና አፍቃሪ ነበር። በዚህ የተነሳ ለልጁ ጆርዳን ገና በሶስት ዓመቱ ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ መጫወጫዎችን በመግዛት እንዲለማመድ ማድረግ ችሏል። ልጁም ገና በሰባት ዓመቱ በአካባቢው ላይ የሚገኙ ልጆችን ብቻ ሳይሆን አዋቂዎችን በመብለጥ የጨዋታ ብቃቱን አስመስክሯል።
አስር ዓመት ሲሆነው ደግሞ በአካባቢው በተደረገ የኤሌክትሮኒክስ ጨዋታ ውድድር ላይ በማሸነፍ ሁለት ሺህ ዶላር ማሸነፍ ችሏል። እስካሁንም 60 ሺህ ዶላር ማግኘት የቻለ ሲሆን በቀጣይም የሚያገኘውን ገንዘብ በዚህ የኤሌክትሮኒክስ ጨዋታዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሃሳብ እንዳለው ተናግሯል።
ጆርዳን በየእለቱ ከ8 እስከ 10 ሰዓት በጨዋታ የሚያሳልፍ ሲሆን በዩቲዩብ አማካይነት ከሚያገኛቸው የጨዋታ ተወዳዳሪዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ይጫወታል። ከዚህም ባሻገር አሁን ጆርዳን 30 ሚሊዮን ዶላር ለሚያስገኘው የኤሌክትሮኒክስ የፑል ጨዋታ ለመወዳርና ለማሸነፍ ትልቅ ዝጅት እያደረገ እንደሆነም ታውቋል።
በዚህ የተነሳ ነው ታዲያ አባት ልጁ ሙሉ ትኩረቱን በዚህ ጨዋታ ላይ እንዲያደርግ በሚል ከትምህርት ቤት እንዲቀር የወሰነው። አንዳንድ ጊዜ የማይጠበቁ ነገሮች የሕይወትን አቅጣጫ ባልተጠበቀ መንገድ ይመራሉ። ጆርዳንም በዚህ ዘርፍ ዓለምን የሚያስጠራ ይሆን? ወይስ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ለችግር ያጋልጠው ይሆን? የሚለው ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2011
ወርቁ ማሩ