በክልሉ በዜግነት አገልግሎት 654 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ተሠርቷል

ባቱ፡– በኦሮሚያ ክልል ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በዜግነት አገልግሎት 654 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ መሠራቱ ተገለጸ። በኦሮሚያ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ አስተባባሪነት የሚከናወን የዘንድሮው የክረምት የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብር ትናንት በባቱ ከተማ ተጀምሯል።

የኦሮሚያ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የዜግነት አገልግሎት ኃላፊ መሐመድናስር አባጀማል (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ እንደ ክልል የዜግነት አገልግሎት ሥራ በ2012 ዓ.ም ሲጀመር በ10 የሥራ ዓይነቶች ሲሆን፤ በወቅቱም 13 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ተሠርቷል።

የሥራ ዘርፉም ሆነ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከዓመት ዓመት እያደገ በመምጣቱ፤ በ2017 በጀት ዓመት የሥራ ዘርፉ ወደ 58 ማደጉን የጠቆሙት መሐመድናስር (ዶ/ር)፤ በዓመቱ ወደ 30 ሚሊዮን ሰው የተሳተፈበት 329 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ መሥራት እና 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስረድተዋል። እንደ ክልል በዜግነት አገልግሎት ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት 654 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ በመሥራት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አብራርተዋል።

እንደ መሐመድናስር (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ለአብነትም፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መስክ በተደረገው ተሳትፎ እንደ ክልል አምስት ቢሊዮን ያህል ችግኞችን መትከል ተችሏል። ከእዚህ ባሻገር የአቅመ ደካሞችና ችግር ያለባቸውን ዜጎች ቤት በመሥራት እና በማደስ፤ ትምህርት ቤቶችን እና የጤና ተቋማትን በመገንባት፣ በማስፋፋትና ደረጃ በማሳደግ፣ እንዲሁም ግብዓት በማሟላት፣ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት እንዲሁም በትምህርት ቤት ምገባና ማዕድ የማጋራት ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።

በቀጣይም የዜጎችን ቤት በመሥራትና በማደስ፤ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን የመገንባት፣ የማስፋፋት፣ ደረጃ የማሳደግና ግብዓት የማሟላት፤ የሕጻናት መዋያዎችንና መጫወቻ ቦታዎችን የመገንባትና የማስፋፋት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ላይ የመሳተፍ፣ የደም ልገሳ እና ሌሎችም የነጻ አገልግሎቶችን የመስጠት ተግባራት ሕዝቡን በማሳተፍ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት መሐመድናስር(ዶ/ር)፤ ለእዚህም በ2018 በጀት ዓመት በ72 የሥራ መስኮች 360 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ለማከናወን እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ በበኩላቸው፤ ቢሮው የሴቶችን፣ የሕጻናትና የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በእዚህም በ2017 በጀት ዓመት 57 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ አከናውኗል። ይህንኑ ተግባር በማጠናከር በ2018 በጀት ዓመት ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሥራ በማከናወን፤ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞችና ሕጻናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ መብራት ማብራሪያ፤ በቢሮው አስተባባሪነት እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሊሠሩ ከታቀዱ ሥራዎች መካከል፤ 156 ሺህ 870 የአቅመ ደካሞችና ድሃ ወገኖችን ቤት መሥራትና ማደስ፤ ለአራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ፣ 107 የሕጻናት መዋያ እና አንድ ሺህ 370 የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ግንባታዎች ይገኙበታል።

በባቱ ከተማ የመርሃ ግብሩ ጅማሬ መበሰሩን የጠቆሙት ወይዘሮ መብራት፤ በቀጣይ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሥራዎቹ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። ለእዚህም እስካሁን ለነበረው የሕዝቡ ተሳትፎ በማመስገን፤ በቀጣይም ለሚኖረው ሥራ የተለመደ ተሳትፎውን እንዲያጠናክርና መደጋገፍ ሕዝባዊ እሴቱ መሆኑን እንዲገልጽ ጥሪ አቅርበዋል።

የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አሕመዲን ኡስማኤል በበኩላቸው እንደገለጹት፤ እንደ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ደረጃ ለማሳደግም ሆነ የነዋሪዎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚያግዙ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። እነዚህ ሥራዎች ከሚከናወኑባቸው መንገዶች አንዱ የዜግነት አገልግሎት ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 233 እናቶችን ከችግር ያወጣ የቤት ግንባታና እድሳት ተከናውኗል። ይህንኑ ተግባር ለማጠናከርም እንደ ከተማ አስተዳደር ከ30 በላይ አገልግሎቶች ተለይተው እየተሠራባቸው ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎት በ2011 ዓ.ም በጨፌ ኦሮሚያ አዋጅ ወጥቶለትና ወደ ሥራ እንዲገባ በጸደቀው መሠረት፤ በ2012 ዓ.ም በይፋ ወደ ሥራ የተገባበት መሆኑ ይታወሳል። ትናንት በባቱ ከተማ በተከናወነው መርሃ ግብር፤ የኦሮሚያ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ የአረጋውያን ቤቶችን የመገንባትና የማደስ፣ የሕጻናት መጫወቻ የመገንባት ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፤ የትምህርት ቁሳቁስ እና የሕጻናት የስፖርት ቁሳቁሶችንም ለከተማ አስተዳደሩ አስረክቧል።

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You