ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በማዕከል ደረጃ ለ11 የግል ጤና ተቋማት ዕውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በማደስ በ2017 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ (ስታንዳርድ) መሠረት የተሻለ የአፈጻጸም ውጤት ላስመዘገቡ 11 ጤና ተቋማት ዕውቅና መስጠቱን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ የዋንጫ እና የእውቅና ሰርተፍኬት ለተበረከተላቸው የጤና ተቋማት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት እንተናገሩት፤ ባለስልጣኑ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አድሰው በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው የጤና ተቋማት ስታንዳርድ መሠረት ተግባራዊ ያላደረጉትን በመቆጣጠር የተለያዩ አስተዳደራዊ ቅጣቶች ሲያከናውን ቆይቷል። ዘንድሮ ተገቢውን ስታንደርድ አሟልተው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ጤና ተቋማት ዕውቅና መስጠት መጀመሩ ሌሎቹንም የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለጤና ተቋማት ዕውቅና መስጠት የተጀመረው በማዕከል ብቻ ሳይሆን በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ደረጃም በሁሉም ክፍለ ከተማ መሆኑን አንስተው፤ ይህም በቅርንጫፍ ደረጃ ጤና ተቋማቱ ስታንዳርዱን እንዲያሟሉ የሚደረገውን ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር የሚያመላክት ነው ብለዋል።

አያይዘውም ዕውቅና የመስጫው መመዘኛው መስፈርት ከፍተኛ መሆኑንና አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማት ተቀራራቢ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን አመልክተው፤ ዕውቅና መስጠቱ በቀጣይ ዓመታትም የሚከናወን ስለሆነ እያንዳንዱ የጤና ተቋም ስታንዳርዱን በከፍተኛ ሁኔታ አሟልቶ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ተግቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

ባለስልጣኑ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በኔክሰስ ሆቴል በስታንደርዱ መሠረት ዕውቅና የሰጣቸው ተቋማት በግሉ ዘርፍ እየሠሩ ለሚገኙ አስራ አንድ ተቋማት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሶስት መድኃኒት ቤቶች፣ ሶስት ሆስፒታሎች እንዲሁም አምስት የህክምና ማዕከላት ይገኙበታል።

ከሶስቱ መድኃኒት ቤቶች ከተቀመጠው መቶ ነጥብ ውስጥ 93 ነጥብ በማምጣት አንደኛ በመሆን የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሁም የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ሰሎዳ መድኃኒት ቤት ቁጥር 10 ነው። 79 ነጥብ 8 በማምጣት ሁለተኛ የወጣው ድሮጋ መድኃኒት ቤት ቁጥር 6 ሲሆን 78 ነጥብ 3 በማምጣት ሶስተኛ በመውጣት እውቅና ያገኘው ደግሞ ድሮጋ መድኃኒት ቤት ቁጥር 7 ነው።

ከሶስቱ ሆስፒታል ከተቀመጠላቸው መቶ ነጥብ ውስጥ 95 ነጥብ 46 ነጥብ በማምጣት አንደኛ በመሆን የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሁም የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተክለ ሃይማኖት አጠቃላይ ሆስፒታል እንደሆነ ታውቋል። 91 ነጥብ 86 ነጥብ በማምጣት ሁለተኛ የወጣው ስልኪሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል ሲሆን 91 ነጥብ 81 በማምጣት ሶስተኛ የወጣው ደግሞ አዲስ ህይወት አጠቃላይ ሆስፒታል መሆኑ ተገልጿል።

ከአምስቱ የህክምና ማዕከላት ከመቶ 92 ነጥብ 98 በማምጣት አንደኛ በመሆን የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሁም የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ስጦታው የሥነ አዕምሮ እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል እንደሆነ ተጠቁሞ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ በመውጣት የእውቅና ምስክር ወረቀት የተቀበሉት ደግሞ አይሲኤል አድቫንስድ ላቦራቶሪ፣ ዶክተር ሸምሴ ኤምሲኤች ማዕከል፣ ዩኮ ኤምሲኤች ማዕከል እንዲሁም ኖር ዲክ ኢንተርናሽናልና ሰርጂካል ማዕከል እንደሆኑ ተጠቁሟል።

በስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You