
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሙሉ ቃል የመጀመሪያ ክፍል ዛሬ ይዘን ቀርበናል
ኢቲቪ፦ ቃለ መጠይቄን የምጀምረው ከአንድ ንግግርዎ ነው፤ አሁንም ድረስ በበርካቶች ዘንድ የሚጠቀሰው አንድ ንግግር አለ። “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” የምትለው ንግግር በርካቶች አሁንም ድረስ የሚጠቅሷት ናት እና፤ ትልቅ የሆነ ኃያል የሆነ ትርጉም እንዳለውም ጭምር እረዳለሁ እና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያዊነት ለእርስዎ ምንድነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ እጅግ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያዊነት ምንነት ላይ ሳንግባባ ከዚያ ቀጥሎ በሚመጡ ሃሳቦች ላይ መነጋገሩ ያስቸግራል። ኢትዮጵያዊነት ማን ነው? ኢትዮጵያ ማን ነው? ለምንድነው ኢትዮጵያዊነት የሁላችንም አሰባሳቢ ጥላ አድርገን የምንወስደው? የሚለውን ነገር ሁሉም ሰው በእኩል ትርጉም ይገነዘበው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ለእኔ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕጣ ፋንታ ነው። እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ሕዝብ የምንደርስበትን ማንኛውም ትልሞቻችን ልናሳካ የምንችለው በዚህ ትልቅ ማንነት ውስጥ እንደሆነ ነው የማምነው።
ኢትዮጵያዊነት ሲባል ብሔራዊ ጥቅም፣ የግለሰብ ጥቅም፣ የቤተሰብ ጥቅም፣ የማኅበረሰብ ጥቅም፣ ከዚያ ደግሞ አልፎ ብሔራዊ ጥቅም። ብሔራዊ ጥቅም ልክ እንደ ግለሰብ ጥቅም ጠዋት ከፍለን ወዲያው የምናገኘው ላይሆን ይችላል። እኛ ከፍለን ልጆቻችን የሚያገኙት ሊሆን ይችላል።
አሰባሳቢ ትርክት፤ እኛ ሲፈጥረን ባለ ብዙ መልክ፣ ባለብዙ ቋንቋ፣ ባለብዙ ባህል ስለሆንን፤ እነዚያ የሚለያዩን ማንነቶች ዋናውን ማንነት እንዳይሸረሽሩት የሚሰበስበን፣ እንደቤተሰብ እንድንታይ የሚያደርገን ትርክት ያስፈልጋል። ከዚያም ባሻገር ያ ብሔራዊ ጥቅም ያልነውን ነገር ሊያሳካ፣ ሊያበለፅግ የሚችል ትውልድ መሥራት ይጠይቃል።
ብሔራዊ ጥቅም ከግል ጥቅም የሚለየው ነገር በሰሞኑ በፈረንሳይ ሀገር አንድ የካቶሊክ ካቴድራል የመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር፤ ኖተርዳም ካቴድራል ይባላል። እዚያ ሲነግሩን ይሄ ካቴድራል ተጀምሮ እስከሚያልቅ 200 ዓመት ፈጀባቸው። 200 ዓመት ማን መኖር ይችላል? 200 ዓመት ማንስ ጀምሮ ሊጨርስ ይችላል? 200 ዓመት የሚሠራ ሥራስ ጀማሪውስ ምን ሊሆን ጀመረው? በግል ጥቅም ቢሆን አያየውም! ብሔራዊ ጥቅም ማለት ያ የጀመረው ከዚያ ከጀመረው ሥራ ተጠቃሚ ባይሆን እንኳን በትውልድ ቅብብሎሽ መካከል የሚጸና እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቆይ ሥራ ማለት ነው።
አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ለመጨረስ 200 ዓመት የፈጀው የጋራ የሆነ ፈረንሳዊ ጥቅም እንጂ የግለሰቦች ወይም የኩባንያ ጥቅም ሊሆን አይችልም። ብሔራዊ ጥቅም ስንል ከእኛ ከግል ፍላጎትና መሻት የተሻገረ ማለት ነው። በእርግጥ አንድ ከግምት ሊገባ የሚገባው በርከት ባሉ ሰዎች እንደ ችግር የሚታየው ኢትዮጵያ ውስጥ የማንነት አረዳድ ነው።
የሰው ልጅ በአንድ ማንነት ብቻ አይታወቅም። እኔ በስሜ እታወቃለሁ፤ ዐቢይ ስባል መለያዬ ነው ማንነቴ ነው። የአባቴ ልጅ መሆኔ የአባቴ ስም ማንነቴ ነው። የልጄ ስም ማንነቴ ነው፤ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በተማርኩት ሥራ፣ በተለያዬ ነገር ልታወቅ እችላለሁ። እኔ ማንነቴ የሚገለጸው በአንድ ነገር ብቻ አድርጌ ወይም አንደኛውን አጉልቼ ሌላውን ሳኮስስ በአንድ ጉዳይ ብቻ አንደኛውን አጉልቼ ሌላውን ሳኮስስ የኢትዮጵያዊነት ምንነትና የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ትክክለኛውን ሚዛን ይስታል።
ለምሳሌ እዚህ ቤት ውስጥ 100 ኢትዮጵያውያን ብንኖር፤ 100 የምንሞላው ኢትዮጵያዊ ስንሆን ነው። እዚህ ካላችሁ ሰዎች ወንዶች ተለዩ ከተባለ 60 ልንሆን እንችላለን። ከወንዶች መካከል የብልፅግና ፓርቲ አባላት ተለዩ ቢባል ደግሞ 20 ልንሆን እንችላለን። ከብልፅግና ፓርቲ አባላት መካከል የሲቪል ኢንጅነር ተማሪዎች ተለዩ ብንባል ደግሞ ሦስት ልንሆን እንችላለን።
ሲቪል ኢንጂነርም ማንነታችን ነው፣ ብልፅግናም ማንነታችን ነው፣ ወንድም ማንነታችን ነው፣ የምንለይበት፣ የምንገለጽበት ነገር ነው። ሁሉም ተሰካክቶ ግን ኢትዮጵያዊነት ሥር ነው የሚወድቀው ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነት ሲሆን ሰብሰብ፣ ተለቅ ይላል። ከኢትዮጵያዊነት በታች የሆኑ ማንነቶች አሉ፤ ነገር ግን እያነሱ ይሄዳሉ፤ ነገር ግን ወደ ትልቁ ማንነት፣ ወደሚሰበስበን፣ ወደሚያፀናን፣ ወደሚያዘልቀን ማንነት መሰብሰብ ማለት ነው።
‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ›› የተባለው ሃሳብ እኔም የሚገዛኝ ሀሳብ ነው፤ ስኖር ኢትዮጵያዊ ሆኜ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሠርቼ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቆሜ ሳልፍም ኢትዮጵያ መሆን እመኛለሁ። ነገር ግን አንድ ወዳጄ ይሄን አባባል የሚወድና ነገር ግን የሚተች ‹‹አግላይ ነው!›› አለኝ። ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ›› አግላይ ነው፤ ስንኖር ዲያስፖራ ስንሞት ኢትዮጵያም ስላለን አለኝ።
ምን ማለቱ ነው? ሰዎች በተለያየ ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው በተለያየ ሀገር ይኖራሉ፤ ፓስፖርት ይቀይራሉ፣ ይወልዳሉ፣ ይኖራሉ። መጨረሻ ግን ብዙዎቹ፤ ሁሉም ባይሆኑም ብዙዎቹ ሲሞቱ ገንዘቡን መክፈል እንኳን ባይችሉ ኢትዮጵያውያን አዋጥተው፣ ለምነው፣ ተለቅተው አስከሬናቸውን ወደዚህ ልከው እዚህ ይቀበራሉ።
ያ ሰው ለምንድነው ኢትዮጵያ ሄደህ የምትቀበረው ተብሎ ከመሞቱ በፊት ቢጠየቅ፤ ብርድ እንዳይመታኝ፣ እንዳይርበኝ፣ ከጎረቤት ጋር ቡና ልጠጣ ሊል አይችልም። በሆነ ሎጂካል በሆነ መንገድ ሊያሳምነን አይችልም። ነገር ግን ሰው ሞቶ እንኳን የመጨረሻ ማረፊያው ሀገሩ እንድትሆን ይመኛል።
ብርድ እንዳይመታኝ፣ እንዳይርበኝ፣ ከጎረቤት ጋር ቡና ልጠጣ ሊል አይችልም። በሆነ አመክንዮ ምክንያት ሊያሳምነን አይችልም። ነገር ግን ሰው ሞቶ እንኳን የመጨረሻ ማረፊያው ሀገሩ እንድትሆን ይመኛል። ያ በዚያ ልክ የሚወዳት፣ በዚያ ልክ የሚመኛትን ሀገር ማፅናት፣ መጠበቅና ማስቀጠል ላይ ግን በዛ ልክ አይተጋም።
ለዚህ ነው ብሔራዊ ጥቅም የሚያስፈልገው። ስንሞት እንኳን ልናርፍበት የምንፈልገውን ምድር የማፅናትና የማቆየት ጉዳይ የየዕለት ንግግራችን፣ የየዕለት ሥራችን ውጤት ካልሆነ በእኛ እንዝህላልነት ሊፈርስ ይችላል። ከፈረሰ ደግሞ ስንኖር ካናዳዊ ሆነን ስንሞት ኢትዮጵያዊ የምንሆንበት ዕድል ያንሳል።
እና በጣም ጥልቅ ሃሳብ በውስጡ የያዘ ነው። ይህ በውስጡ የያዘው ሃሳብ ግን ለመጪው ትውልድ እንዴት አድርገን የፀና የለማ የማይለምን ሀገር እናቆያለን ከሚል ፍሬ ሃሳብ ጋር መሰናሰል አለበት። ምክንያቱም የጀመርነው ትውልድ ካልቀጠለ፣ የምናስበውን ትውልድ ካልቀጠለ በስተቀር በአንድ ትውልድ፣ በአንድ ቤተሰብ፣ በአንድ ግሩፕ ሀገር ተሠርቶ አያልቅም።
ሀገር የቅብብሎሽ ውጤት ነው። ያን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ መሥራት የሚቻለው ትውልድን እያሰብን ስንሠራ ነው። ነገን እያሰብን ስንሠራ ነው። ነገን የምናስብ ሰዎች ግን ዞር ብለን ትናንትናን መመልከት የማንችል ከሆነ፣ ትናንትናችንን የዘነጋን እንደሆነ፣ ከትናንትናችን መማር የማንፈቅድ ከሆነ ነገ አይሠራም። ለዚህ ነው እኛ ትናንትን ከዛሬ ዛሬን ከነገ አስተሳስረን፣ ሚዛን ጠብቀን ሀገር እንገነባለን ብለን የተነሳነው።
እንግዲህ ሁሉም ሰው እንደሚገነዘበው ትናንትን ባለው ልክ ማክበር፣ አፅንቶ ማቆየት የእኛ ንግግር አይደለም፤ ተግባር ነው። በዚህ ዕድሜሽ ወይም ከዚያ በፊት ወላጆችሽን ብትጠይቂ የትኛውም መንግሥት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ሊጠግን ሲሞክር አልሰማሽም። በዚህ ዕድሜሽ ወይም በአባትሽ ዕድሜ የትኛውም መንግሥት የፋሲል ቤተ መንግሥትን ሊጠግን ሲሞክር አልሰማንም።
በእኔም በአባቴም ዕድሜ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥትን ሰዎች ለመጠገን ሲሞክሩ አልሰማንም። እዚህ ያለንበትን የምኒልክ ቤተ መንግሥት፣ የኃይለ ሥላሴን ቤተ መንግሥት ሁሉ ቀርቶ የሉሲ መገኛ የሆነው የኢትዮጵያ ሙዚየም የሚባለው አንድ ለእናቱ ከተሠራ በኋላ ዞር ብሎ የሚያየው ባለመገኘቱ በውስጡ የያዘው ሀብት በጣም ብርቅና ውድም ቢሆን ሰው ገብቶ ለመጎብኘት የሚያስችል ብቃት አልነበረውም፤ አልተጠገነም። በተሠራበት ልክ አልተያዘም። ወይም አላደገም።
እነዚህን ትናንት አባቶቻችን የሠሯቸውን፣ የጀመሯቸውን ነገሮች ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ይሁን ብለን አስበን የምንጠግንበት ምክንያት እንዲቆይ የምንፈልግበት ምክንያት ትናንትናችንን ማየት ካልቻልን ነገ የሚባል ነገር የለም። ትናንትናን በመጠገን ብቻ ነገ አይሠራም። ለምሳሌ ዩኒቲን በመሥራት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን በመሥራት ብቻ ነገ ሊሠራ አይችልም።
መሐል ላይ ችግር አለ። መንገድ የሚያገናኝ የለም። ሳይንስ ሙዚየም የለም፣ ፍሬንድሺፕ የለም፤ ለዛሬ ደግሞ ያ ክፍተት መሞላት አለበት ማለት ነው። ዛሬ ላይ ሊሟላ የሚገባው ክፍተት ሲሟላ፣ ትናንት መቆየት ሲችል ነገ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ምን ዓይነት ነገር ላይ መድረስ እንደምንችል ማንም ሰው በቀላሉ ሊገምት ይችላልና ትናንትናን በወጉ ተገንዝበንና ተረድተን እሱን ጠግነን ለልጆቻችን መሻገር እንዲችል ስናደርግና በትናንትና ውስጥ የጎደሉትን ደግሞ ዛሬ ስንሞላ ነጋቸው ብሩህ የሆኑ ልጆች ይፈጠራሉ።
ይህን ያሰበ ነው ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት ማሕቀፍ ነው። ኢትዮጵያዊነት ከትናንት እስከ ነገ ነው። ኢትዮጵያዊነት ከሀ እስከ ፐ ነው እንጂ ሲመቸን፣ ሲደላን፣ ጥቅም ስናገኝበት የምናዜመው፣ የምናወድሰው፣ ሲከፋን፣ ሳይመቸን ሲቀር፣ ሕልሞቻችን ሲጨነጋገፉ የምንተወው የወረት ጉዳይ አይደለም። የሁልጊዜ ነው።
በከፍታም በዝቅታም፤ ሲመችም ሳይመችም የምንኖረው ጉዳይ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ሲደላንና ለእኛ ሲመች ለምሳሌ ሥልጣን ስንይዝ ኢትዮጵያዊ ብለን ኖረን ሥልጣኑ ሲቀር ደግሞ የለም ኢትዮጵያዊነት አያስፈልግም የምንል ከሆነ ይህ ትክክለኛ መስፈርት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የምንሰዋለት ዓላማ፣ ነገ ውጤቱን የምናየው (ሀርቨስት የምናደርገው) ብቻ ሳይሆን አንዳንዱ በልጆቻችን የሚታይ ሊሆን ይችላል።
ለዛም ቢሆን ዋጋ የሚከፈልለት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ታይቷል። ሰዎች ዓድዋ ላይ፣ ማይጨው ላይ፣ ባድመ ላይ የሞቱት ትውልድና ሀገር እንዲቀጥል እንጂ ከሞቱ በኋላ ሌላ የሚያገኙት ወረት፣ ክፍያ ስላለ አይደለም። ሰዎች ሕይወታቸውን ከፍለው ሀገር የሚያፀኑት ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ ባለ ደርዝ የሚለካና የሚታይ ስለሆነ ነው።
በአጭሩ ኢትዮጵያዊነት ኩልል ብሎ የሚፈስ ጅረት ነው። ክረምት ከበጋ የማይቋረጥ በድምፀቱ፣ ለተጠሙ በመድረሱ፣ ለእርሻ በመሆኑ ፈጥኖ በመጠበቁ እጅግ እርካታን የሚሰጥ በሰፈር ውስጥ የሚያልፍ ኩልል ያለ ጅረት ካለ ኢትዮጵያዊነት እንደሱ ነው። አንዳንዴ ዘንቦ ሊደፈርስ ይችላል። ነገር ግን ሰክኖ ይጠራል። ኢትዮጵያዊነት የማይቆም በቀጣይነት የሚፈስ፣ በሙላት የሚመለስ፤ በልጆች የሚገለጥ የኖረ፣ ያለና የሚኖር ነው ብዬ ነው የማስበው።
ኢቲቪ፦ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ስለትናንትናችን ሲያነሱ አያይዤ ማንሳት የፈለኩት ነገር ስላለ ነው፤ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትናችንን የምናይበት መነፅርስ የተስተካከለ ነው? በምን መልኩ ልናየው ይገባል ትናንታችንን ስንገነዘበው ይላሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ሁልጊዜ ሰዎች ትናንትን ሲመለከቱ ዛሬ ባሉበት የእውቀት ልክ፣ ዛሬ ባሉበት ዓለማዊ ሁኔታ፣ ዛሬ ባሉበት የሀብት ልክ ካዩት ሚዛን ይስታሉ። ትናንትን ማየት ያለብን በዚያን ጊዜ በነበረ ዓውድ ነው። የከፋም የለማም ነገር እንደሆነ ትናንትን ማየት ያለብን በዚያን ግዜ በነበረ ዓውድ ነው።
ትናንትን ማየት የሚያስፈልገው ለፍርድ አይደለም። ትናንትን ማየት የሚያስፈልገው ለመማር ነው። ትናንትና ውስጥ ልንማራቸው የሚገቡ በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ። እነሱን ካልተማርን ስህተት እንደግማለን። እነሱን ካልተማርን ጥፋት እንደግማለን። ጥፋት ከደገምን ደግሞ ይያያዝና ለትውልድ ይሻገራል።
ትናንትናን ስናይ ለመፍረድ ከሆነ፣ ትናንትናን ስናይ ያ መደረግ ነበረበት፣ ያ መደረግ አልነበረበትም ብለን ለመወሰን ከሆነ በዚያ ትውልድ መገኘት አለብን። በትውልዶች መካከል የሀሳብ፣ የዕውቀት፣ የሀብት ልዩነት አለ። እና ትናንትን ማየት ያለብን ቢበዛ ለመማር መሆን አለበት። ከእነችግሩም ቢሆን ብዙ ትምህርት ስለሚገኝበት፤ ከዚያ ውጪ ያለ እይታ የተንሸዋረረ ይሆንና የተሟላ ግንዛቤ እንዳንይዝ ያደርገናል። ትናንትን አብዝተን እንጠላለን ወይንም አብዝተን እንወዳለን።
አብዝተን ስንጠላ ልንማር የሚገባንን ነገር እንስታለን። አብዝተን ስንወድ ደግሞ ዛሬን መኖር፣ ዛሬን መሥራት ሲገባን ካለጊዜያችን ትናንትና ውስጥ እንኖራለን፤ ሁለቱም ትክክል አይሆኑም ማለት ነው።
ኢቲቪ፦ ወደ ኋላ ልመልስዎ፤ ወደ ለውጡ ማግስት እንሂድ እና በለውጡ ማግስት የተለያዩ በተለይም አስገራሚ የማይረሱ ከሚባሉ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው እንደሆነ ይታወቃል። እርስዎም የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉም እንዲገቡ እና በፖለቲካ ዓውድ ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ ማድረግዎ እንደዚሁ የሚታወቅ ነው። ከዚያ በኋላ ከተፈጠሩ አንዳንድ ጉዳዮች አንፃር ግን ዛሬ ላይ ሆነው ይህ ርምጃ ትክክል ነው የሚል ሃሳብ አለዎት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ይሄ ጥያቄ በብዙ ሰዎች ይነሳል። ነገር ግን አንድን አጋጣሚና ሁነት ራሱን ብቻ ወስዶ በማየት የተሟላ ግንዛቤ መያዝ አይቻልም። ማንኛውም “ትሪገሪ ፖይንት” “ፕሮክሲሚቲ” አለው፤ በአቅራቢያው ለዚያ ግብዓት የሚሆን ነገር አለው። ከዚያ ዝቅ ስንል መዋቅራዊ (ስትራክቸራል) ጉዳይም አለው። ሙሉውን ካላየን በቀር፣ ውሳኔን ብቻ ከወሰድን የተሟላ ግንዛቤ አንይዝም።
ፈላስፎች እውነት ሦስት ንጣፍ አላት ይላሉ፤ ልክ እንደሽንኩርት ናት ይላሉ። ሽንኩርት የመጀመሪያው ልጣጭ በሙቀት፣ በቅዝቃዜ፣ በአየር ፀባይ ምክንያት ቀለሙም፣ ድርቀቱም ውስጥ ካለው ሽንኩርት ጋር አንድ ዓይነት አይደለም። የመጀመሪያውን ስንልጥ ሁለተኛውን ስንልጥ ከውስጥ የሚወጣው ሽንኩርት የበለጠ የለሰለሰ፣ ከለሩም ከቀደመው የተሻለ፣ ለመበላት ዝግጁ የሆነ ነው። ወላጆቻችን ሽንኩርት እንዳገኙ አጥበው አይልጡም፤ የመጀመሪያውን ልጠው ጥለው ውስጥ ያለውን ነው የሚከትፉት። ልክ እንደዚሁ እውነትንም በሌየሩ ነጥለን ማየት ካልቻልን ትክክለኛውን ትርጉም አናገኝም።
ፈላስፎቹ እውነት ሦስት ክፍል አላት ካሉ በኋላ የመጀመሪያውን ‹ኢምፔሪካል› ነው ይላሉ፤ የምናየው፣ የምንነካው የምንሰማው ነገር ነው። ሁለተኛውን ልጣጭ ግን አክቹዋል ነው ይላሉ፤ አክቹዋል ማለት ደግሞ ኤቨንቱን ነው ይሉታል። ሦስተኛው ብዙ ሰው የማያየው ሪል ነው ይላሉ። እሱም መካኒዝም ወይንም ስትራክቸር ነው ይላሉ።
ሜካኒዝሙን ያልተገነዘበ ሰው ስለጉዳዩ እውቀት አይኖረውም። በቀላል ምሳሌ ላስረዳ፤ ቲያትር ቤት እንሄዳለን። ቲያትር ቤት ተቀምጠን የሚተውኑ ወንድና ሴት ሲጫወቱ አንዳንዴ እንስቃለን፣ አንዳንዴ እናጨበጭባለን ምናልባት አንዳንዴ እናለቅሳለን፣ እንቆማለን እንጮሃለን፣ ብዙ ስሜቶች ይገላበጣሉ። እዚያ ያለው ኦዲየንስ ሪአክት የሚያደርገው ስቴጁ ላይ የሚያየውን ብቻ ነው፤ እሱ ኢምፔሪካል ነው።
እሱ ኤክስፒሪያንስ የምናደርገው ነገር ነው። ነገር ግን ከዚያ መድረክ በስተጀርባ መብራት ላይ የሚሠሩ፣ ሜካፕ ላይ የሚሠሩ ድምፀት ላይ ወጣ ወረደ ብለው የሚሠሩ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ ቡድን አለ። በእያንዳንዷ የቲያትር ሾው ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ለእያንዳንዱ ተዋንያን ይህን ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ። እነርሱ ናቸው አክቹዋል የሚባሉት። የእነርሱ ሥራ ከፍና ዝቅ ቢል፣ የእነርሱ ሥራ በወጉ ባይከወን ያ የምንሰቀው፣ ያ የምንጮኸው ነገር ሊበላሽ ይችላል።
ውጤቱ ከእነርሱ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሰው ግን ከመጋረጃው ጀርባ ያለውን ማንም አያስብም። ከእነርሱ ጀርባ ደግሞ ሌላ ቁልፍ ስትራክቸራል የምንለው ጉዳይ አለ። ስክሪፕት ፀሐፊውና ዳይሬክተሩ ናቸው። ስክሪፕት ጸሐፊውና ዳይሬክተሩ የነገሩ መሠረት ናቸው። አንድ ሰው ስክሪፕት ሲጽፍ ዝም ብሎ አይጽፍም።
የቀሰቀሰው ነገር አለ፤ ወይ ያየው ነገር አለ፣ ወይ የሰማው ነገር አለ ወይ ከተፈጥሮ የተማረው ነገር አለው። ያንን ሲጽፍ እርሱ በጻፈውና ባየው ልክ የሚረዳው ዳይሬክተር ይፈልጋል። አስተውለሽ ከሆነ ዳይሬክተሮች ቲያትር ሲያለማምዱ አለባበስህን እንደዚህ ይሁን፣ ቁመና እንደዚህ ይሁን ፣ ድምፀትህን ከፍ አድርግ ዝቅ አድርግ ይላሉ፤ ከየት አመጡት ሰዎቹ? ያንን ቲያትር አላዩት፣ በጭንቅላታቸው ውስጥ የሙሉ ቲያትሩን ስክሪፕቱን አስቀምጠው ቲያትሩ ስለውን ለሰዎች ለመግለጥ የሚያደርጉት ጥረት ነው።
እነዚያን ስክሪፕት ጸሐፊዎችንና ዳይሬክተሮችን ስትራክቸራል ደረጃ ካየን፣ ከመጋረጃ ጀርባ ያሉትን ሰዎች ደግሞ በአክቹዋል ሌቭል ካየን የምናገኘው ውጤት አሳዛኝም፣ አስከፊም፣ የሚያዝናናም ቢሆን ሙሉ እይታ አለን ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ቲያትር እናይና ማን ጻፈው? ሎሬት ፀጋዬ ነው እንዴ፤ ማን ዳይሬክት አደረገው፤ እነ ማን ተጫወቱት እንልና በሙሉ ግንዛቤ ይኖረናል ማለት ነው። የእኛንም ጉዳይ ብዙ ጊዜ ያለው ችግር ሙሉ ግንዛቤ ማጣት ነው። ግንዛቤ ማጣት የተሳሳተ ፍርድ ለመፍረድ ይዳዳል፣ ይዳርጋል።
በመጀመሪያ እስረኞች ሳንፈታ፣ እንታገላለን የሚሉ ሰዎችን ሳንመልስ፣ ለውጡ ሲመጣ ምን ዓይነት ኢትዮጵያ፤ ምን ዓይነት መንግሥት ነበር እኛ የተቀበልነው? እኛ እኔም፣ አንቺም እሷም፣ ሁላችንም። የጋራ ዕዳ ስለሆነ፤ የተቀበልናት ኢትዮጵያ 59 ፐርሰንት ጂዲፒዋ ዕዳ የሆነ። ዕዳ መሆኑ አይደለም፤ ስትበደር ኖራ አሁን ጊዜው ደርሷልና ካልከፈልሽ ልትበደሪም አትችይም፣ ካልከፈልሽ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት አናደርግም የሚባለት ጊዜ ማለት ነው።
አንዳንዴ ዕዳም እያለ የመበደር ዕድል ካለ ችግር የለውም፤ እየተበደረም ሥራ ሊሠራ ይችላል። በፍጹም አናበድርም፣ ቀይ ናችሁ፣ እስከዛሬ የሰጠናችሁን ልትከፍሉ አልቻላችሁም የተባለች ሀገር ናት። ደመወዝ ለመክፈል እኔ ቢሮ ገብቼ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያው ጥያቄ ደመወዝ መክፈል አንችልም የሚል ነበር። የመጀመሪያው ጥያቄ! ዕዳ የነበረባት ብቻ ሳይሆን በዕዳ የተዘፈቀች ኢትዮጵያ መሆኗን በደንብ ማስተዋል ያስፈልጋል፤ በስትራክቸራል ደረጃ።
ሁለተኛው በጣም በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ቆመዋል። በየቦታው ድንጋይ ተዘርቷል። በየቦታው ሰው ድንጋዬን ልቀሙልኝ ይላል። ሌላውን እንተወውና ህዳሴን ብቻ እንውሰድ። ህዳሴ ኮንትራት የተሰጠው ኩባንያ በቃ ለውጥ መጥቷል ከዛሬ ጀምሮ ሥራህን ቀጥል በሚል አማርኛ የሚጀመር ስላልነበር ሥራውን ለመጀመር ብቻ ከኮንትራቱ ውጪ አንድ ቢሊዮን ዩሮ ጠይቆናል።
የነበረው ኮንትራት አይደለም አዘገያችሁኝ፤ በጊዜ እንዳልሠራ በጊዜ አልከፈላችሁኝም ኪሳራ አደረሳችሁብኝ ያንን ካልከፈላችሁኝ በቀር ሥራ አልጀምርም የሚል ኩባንያ ነው የነበረው። በነበረው ኮንትራት ሳይሆን በደረሰበት ኪሳራ የሚካካሰው ማለት ነው። እዚህ ጋር ዕዳ ነው እዚህ ጋ ደግሞ ፕሮጀክቶች ቁጭ ብለዋል። በመንገዱም በሁሉም መንገድ ጥያቄዎች አሉ ከሁሉም በላይ ግን ህዳሴ ላይ እንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ የሆነ ሀብት ይጠይቅ ነበር።
ሦስተኛ የተረከብናት ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ የታሰረች ናት፤ እስረኛ ናት። እኛ መሰለን እንጂ ስንንቀሳቀስባት፤ ኢትዮጵያን የሚያክል 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው፣ ከፍተኛ የቆዳ ስፋት ያለው፣ ብዙ ምርት ማምረት የሚችል፣ ለብዙ ጎረቤቶቹ በብዙ መንገድ ሽጦ በረከሰ መንገድ ምርቱን አቅርቦ ብዙ ነገር ማግኘት የሚገባው ሀገር እስረኛ ነው የነበረው።
የጂኦግራፊ እስረኛ መሆን ዛሬ ብቻ ሳይሆን በልጆቻችን በእነሱም ልጆች ጭምር አደጋው እያደገና እየጎላ የሚመጣ ጉዳይ ነው። የተረከብናት ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ነበረች። ይህንን መዘንጋት አይገባም። የጂኦግራፊ እስረኛ መሆን ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች በሙሉ በኋላ ምላሽ እየሆነ ስለሚሄድ።
የተቋም ድቀት ነበረ። ያሉን ተቋማት በወጉ ስላልተሰሩ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም የማይ ችሉ መንግሥት፣ ፓርቲ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ሰፈር መለየት የሚቸገሩ፤ መንግሥት እያለ ሌላ መንግሥት እንዲያዛቸው የሚጠብቁ ተቋማት ነበሩ። ድቀት ያለበት ነው። ያ ማለት ሃሳብ እንኳን ቢኖር ያን ሃሳብ ለመፈጸም አያስችልም ማለት ነው።
ከተቋም ሻገር ስንል በርካታ አሳሪ ሕጎች ነበሩ። ሕጎቻችን በንግድም በሰብዓዊ መብቱም መፈተሽ ይጠይቁ ነበር። ሕጎቻችን ሲሠሩ ሥሪታቸው አሳሪ ስለነበረ። ከዚህ ሁሉ ብሶ ደግሞ ትርክታችን፤ አንተ ቀይ ነህ አንተ ጥቁር ነህ አንተ እንደዚህ ነህ የሚል ከፋፋይ፤ በታኝ ትርክት ነበር ለዓመታት የተሠራበት። እና ሰው ቁጭ ብሎ በጋራ ለማውጋት እንኳን በዚያ የተሰጠው ክፉ ዘር የራሱን ቢጤ ካላገኘ በስተቀር ለመነጋገር የሚቸገር ነበር።
የሚዲያ፣ የፖለቲካ ዓውዱ የተሳከረ ዓለም ነው የነበረው። እነዚያን መዋቅራዊ ጉዳዮች ሰው ዘንግቶ ለምን ተመለሰ፤ ለምን ተወሰነ፤ ለምን ተቀመጠ ቢል ትክክለኛውን ምላሽ አያገኝም። ምን ዓይነት ኢትዮጵያ ነው የተቀበልነው፣ ምን ትመስል ነበር ኢትዮጵያ ያኔ? ታስታውሳላችሁ እንፈርሳለን አንፈርስም ነውኮ ጥያቄው የነበረው። አሁን ተቀይሮ ሌላ ጥያቄ መጣ እንጂ ያኔ የነበረው ጉዳይ እሱ አልነበረም። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለን ሀገር የሚመራ መንግሥት ጠንከር ያሉ፣ ፈታኝ ውሳኔዎችን ይወስናል። ያለው ዓውድ በራሱ መጨከን መወሰን ይጠይቃል።
ውሳኔዎች ግን ሙሉ ለሙሉ በፈለግነው መንገድ ግብረመልስ ያላቸው፣ መቶ ፐርሰንት አወንታዊ (ፖዘቲቭ) ነገር የሚያስችሉ ናቸው ማለት አይደለም። ውሳኔዎች ሁልጊዜም ቢሆን የራሳቸው ደካማ ጎን አላቸው። ማንኛውም ውሳኔ ጠቀሜታ አለው፤ ጉዳትም አለው። ወሳኙ ሰው ማድረግ ያለበት ጥቅሙን ማጉላት ጉዳቱን መቀነስ ነው።
አልያም ደግሞ ጉዳት ፈርቶ አለመወሰን ነው። ጉዳት ፈርቶ ካልወሰነ በነበረበት ዓውድ ውስጥ ይኖራል ማለት ነው። ደፍሮ ከወሰነ ጥቅም አለ፣ ያጎላዋል፤ ጉዳቱን እንዲቀንስ ይገራዋል፣ ይመራዋል። ይሄ ማንኛውም ኃላፊነት ያለበት ሰው እንዲያደርግ የሚጠበቀው ጉዳይ ነው።
ከዚህ ተነስተን ነው እንግዲህ በነበረው ዓውድ፤ ሚዲያው፣ የፖለቲካ ዓውዱ እና ተቋማት ችግር ስለነበረባቸው፤ ፓርቲዎች ተቃዋሚ ኃይሎች እንዲገቡ ብንፈቅድ፤ እስረኞች እንዲፈቱ ብንወስን፤ ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ብንቀይር ያልነው። የተፈታው እስረኛ ሁሉ ለሀገር ጠቃሚ ነው ፤ የተፈታው እስረኛ ሁሉ ጥፋት ሳያጠፋ ነው የታሰረው ብለን አይደለም። እንደዛ ብለን አይደለም። ግን ሳንፈታ እንለይ ብንል ምን ይፈልጋል ተቋም ይፈልጋል። የተቋም ስብራት አለ ብዬሻለሁ። ተቋም በሌለበት አንድ ሺህ፣ አስር ሺህ፣ ሃያ ሺህ እስረኛ በትክክሉ እየመዘነ አንተ ወንጀለኛ ነህ፤ አንተ አይደለህም ለማለት ሌላ አስር፣ አስራ አምስት ዓመት ሊያቆየን ይችላል። ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ስላልነበረ፣ የተቋም ስብራት እዚህ ጋ ይመጣል።
ከተቃዋሚዎች መካከል አቶ እከሌ ቢገቡ አይከፋም፤ አቶ እከሌ ግን ችግር አለባቸው ለማለትም ኢትዮጵያ ያን ልየታ ማስኬድ የሚያስችል ተቋም አልነበራትም። ጊዜም አልነበራትም፤ አቅምም አልነበራትም። በዚያ ምክንያት መልካሙን ከጉድፉ ደምሮ ጥቅምም ጉዳትም ያለው ነገር ቢሆንም በጊዜ ሂደት እየጠራ እንዲሄድ መወሰን አለበት።
ለምንድን ነው እንደዚህ አይነት ውሳኔ መወሰን የሚያስፈልገው ዴሞክራሲን እንለማመድ ስንል፤ ዴሞክራሲ በተፈጥሮ ምቹ ጎዳና አይደለም። አንድ ነገር ለመሥራት ግራ ቀኝ ማየት ማማተር ማማከር የሚፈልግ ሥርዓት ነው። እንደ እኛ ላሉ ሀገራት ተመራጭ ቢሆንም ንፁሕ የሆነ መንገድ /ሃይ ዌይ/ አይደለም። በየመሐሉ የሚጎረብጡ ነገሮች አሉት። ያ የሚጎረብጠን ነገር እየፈቱ መሄድ ግድ ነው።
ያ የማይመችን ነገር እየፈቱ መሄድ ግድ ነው። ያ በመሆኑ ምክንያት ይሄ ውሳኔ ያመጣው ጥቅም ባለው ልክ በለውጡ አጠቃላይ ዑደት ውስጥ የፈጠራቸው ደግሞ ውስብስብ ችግሮች አሉ። ችግር አልባ ውሳኔ ስላልነበረ ችግሩን እናሳንሳለን፤ ጠቀሜታውን ደግሞ እናጎላለን። እኛ ስንመጣ አንዱ ቃል የገባነው ምንድን ነው? ቃል የገባነው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለማምጣት እንሠራለን ነው።
ዴሞክራሲን ለማምጣት እንሠራለን ብለን ወንጀል ሠርተውም በግፍ የታሰሩ ሰዎች፣ በትክክለኛ መንገድ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሚታገሉም፣ ሌላ ፍላጎት ያላቸውም ሰዎች ከሀገር ተሰደው ባሉበት ሁኔታ የመለየት አቅም ሳይኖረን ሁለቱንም ብንከለክል ያን የምናስበውን ዴሞክራሲ ልናመጣ አንችልም። ልክ አስፋልት ሠርቶ አስፋልቱ ስለሚያምር መኪና አይሄድበትም ብሎ እንደመከልከል ነው። አስፋልቱን ከሠራን በኋላ ጥንካሬው ምን ያህል እንደሚዘልቅ ማወቅ የምንችለው መኪኖች ከሄዱበት ነው።
በመንገድ ሥራ ኮንትራት ውስጥ አንድ ኮንትራክተር አስፋልቱን የጨረሰ ቀን አያስረክበንም። በኮንትራት ሕጉ ተጨማሪ አንድ ዓመት ሁለት ዓመት ይሰጣል። ለምንድን ነው ያ የተሠራው ስናየው ያማረ ግን ስንሄድበት አስር ሜትር ጠንካራ አንድ ሜትር ጎድጓዳ፣ አንድ ኪሎ ሜትር ጠንካራ ሌላ ደግሞ መቶ ሜትር የተበላሸ ሊሆን ይችላል።
ያንን ፈተና ማለፍ የሚችለው መኪኖች ሲመላለሱበት ነው። መኪኖች ከሄዱበት ከታየ በኋላ የተበላሸ ክፍሉ ተጠግኖ ሲሟላ ነው ኮንትራት ሰጪው የሚረከበው። እኛ ዴምክራሲ ያልነውን መንገድ ከሠራነው በኋላ ፓርቲዎች አይንቀሳቀሱበትም ብለን ከዘጋን የዴሞክራሲውን ውሃ ልክ ማወቅ አይቻለም። እና የኛ ውሳኔ የነበረው ሁሉም መድረክ ማግኘት አለበት። ሁሉም ጆሮ ማግኘት አለበት። ሃሳብ ያለውና ሃሳብ የሌለው፤ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ምክር የሚያመጣና የማያመጣ ጊዜ ይለየዋል።
አሁን እኛ ተቋም ሳንይዝ እንለይ ብንለው ሪፎርሙን ሳንጀምረው ይጨናገፋል። ግን ለሁሉም መድረክ እንስጥ፤ ሁሉም ይደመጥ፤ ይታይ፣ ሃሳቡ ይደመጥና የተሻለው ይቀጥላል። ያልተሻለው ደግሞ በጊዜ ብዛት የሚሆነውን ይሆናል። እና የመጀመሪያው ነገር መድረክ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ራሱን ለገበያ እንዲያቀርብ፤ ራሱን ለሚሸጥለት ሕዝብ ለማቅረብ እንዳይከለከል ማድረግ ነው።
ከዚያ በኋላ በሕዝብ ተመዝኖ መክበድ አልያም መቅለል የሚወሰነው በእኔ፣ በአንቺ ሳይሆን በእዛ ሰው ሳይሆን በሕዝብ ነው። ሕዝብ ሁሉን ይሰማል፤ ሁሉን ያያል፤ ከዚያ መካከል የተሻለና የከበደለትን አክብዶ ይወስዳል። የቀለለውን ደግሞ ይተዋል ማለት ነው። ሕዝብ እንዲወስን ዕድል ሳንሰጥ ከሆነ ግን ውሳኔ የምንወስነው ጥፋት ያመጣል።
በቅርቡ አውሮፓ ጉዞ ነበረኝ እና በዚህ ቆይታዬ አንድ የሚገርም ነገር አስተዋልኩ። እዚህ በንጽጽር በጣም ብዙ አምቡላንስ ስለማይጮህ መሰለኝ አውሮፓ በጣም ይረብሽ ነበር። ከአንድ ቦታ አንድ ቦታ ሲኬድ አምቡላንስ ብቻውን አይደለም። የእሳት አደጋ መኪና አለው፤ ሞተር ሳይክሎች አሉ፤ ጩኸት ነው። ወደዚያ ጩኸት ወደዚህም ጩኸት ነውና ይረብሻል።
ተደጋጋሚ አጋጠመኝ፣ ዝም ልል ሞከርኩ፤ ግን እየበዛ ሲሄድ ጎኔ ለነበረው ሰው የአምቡላንሱ ጩኸት በጣም ይረብሻል፤ ያውካል፤ ራስ ያማል ፤ ያስመርራል። አይነት ቅሬታ አዘል አስተያየት ሰነዘርኩ። አዎ ልክ ነህ ይጮሀል፤ ግን ለመውለድ የምታጣጥር እናት ሕይወት ይታደጋል።
በመኪና አደጋ ወድቀው ሕይወታቸው ሊያልፍ ያሉ ሰዎች አምቡላንሱ ደርሶ ሕይወታቸውን ይታደጋል። ወላጅ ልጆቻቸው አጠገባቸው ሳይኖሩ በስትሮክ ምክንያት ወድቀው፣ በካንሰር ምክንያት ታመው በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሲሆኑ ደርሶ ይታደጋቸዋል አለኝ። ለእሱ የአምቡላንሱ ጩኸት ሳይሆን አምቡላንሱ የሚሠራው ቁምነገር ነው የሚታየው፤ እኔ ደግሞ እንደመጤ እንደ አዲስ ሰው ለዚያ ሀገር የነበረኝ ምቾት ጩኸቱ አልተመቸኝም።
እኔ ያየሁት ጩኸቱን ነው። እሱ የሚያየው ደግሞ ማዳኑን ነው። ልክ እንደዚሁ ወደሀገር ውስጥ ያስገባናቸው ሰዎች ኪሳራ ብቻ ናቸው ብሎ የሚያስብ ሰው ልክ እንደዚሁ ነው። ብዙ አትርፈንበታል፣ ብዙ የከበዱ ሀገራቸውን እያገለገሉ ያሉ ሰዎች አሉ። በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ፣ በክልል አመራር ውስጥ ያሉ አሉ። ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ አሉ፣ ገብተው የሚነግዱ አሉ። ለረዥም ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ተለያይተው ከቤተሰብ ጋር የተገናኙ አሉ።
አባትና ልጅ መገናኘት ተስኗቸው አብረው የሚኖሩ አሉ። ወይም አብረው ኖረው ወጥቶ መግባት ያልተከለከሉ አሉ። እና በዚያ ውሳኔ ብዙ ያተረፉ፣ ብዙ የተጠቀሙ ሰዎች አሉ፡፤ በርግጥ ጉዳትም አለው። ኢትዮጵያም እንደዛው ናት። በሩቅ የምናቃቸው ቢያገለግሉ ብለን የምንመኛቸው እያገለገሉ እየተጠቀሙ ያሉ ሰዎች አሉ። ያን ደግሞ ስተው ያጡ ሰዎች አሉ።
ውሳኔውን ማየት ያለብን ሙሉ በሙሉ አክሳሪ፣ ሙሉ በሙሉ ጥፋት ሳይሆን እንደማንኛውም ውሳኔ የራሱ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው። ደካማ ጎኑን እያረቅን፣ እያረምን፤ እያስተካከልን ጠንካራ ጎኑን ደግሞ አጉልተን እየተጠቀምን ለመሄድ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፤ በዚያ ዓውድ ነው መታየት ያለበት እና መሠረቱን (ፋውንዴሽኑን) ካልተረዳን፣ ውሳኔውን ብቻ ከወሰድን እንስታለን።
ያኔ ‹ምን አለ እዚያው በቀሩ ኖሮ› ብሎ የሚያስብ ሰው እንደሚኖር ይገባኛል። ግን በየትኛው ኢትዮጵያ ነው የምትወስነው ይሄንን፣ ለነገሩስ አይግቡ ብለን ብንወስን ያን ለመከላከል የሚስችል ተቋምስ ነበረን ወይ? የሚለውም ጥያቄ ያስነሳልና በደንብ ከመሠረቱ መገንዘብ አስፈላጊ ይመስለኛል ይህ ጉዳይ። በድምሩ ግን አትርፈንበታል፤ የከበዱ አሉ፣ የተጎዳንባቸው አካባቢዎች አሉ፣ የከሰርንባቸው አካባቢዎች አሉ። እነሱን እየተማርን እየቀነስን ጥቅሙን እያጎላን እንቀጥላለን። /ክፍል ሁለት በነገው እትማችን ይቀጥላል /
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም