በጎ ፈቃድ – ድንበር አልባው መልካምነት

የሰው ልጆች ሕይወት አንድም በደስታ፣ አልያም በፈተና አጋጣሚዎች መዋዘቱ አይቀሬ ነው:: ብዙ ጊዜ ደስታን እንደራሳቸው ቆጥረው የሚጋሩ፣ በእኩል መንፈስ የሚካፈሉ ወገኖችን ማየት የተለመደ ነው:: እንዲህ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩ ላያስገርም፣ በአድናቆት ላያስደምም ይችላል::

የሰው ልጆች የማንነት ልክ የሚመዘነው ችግርና ፈተና ጓዛቸውን ይዘው ወደ ሕይወታችን በደረሱ ጊዜ ነው:: እንዲህ በሆነ አጋጣሚ ታዲያ ደስታን በዋዛ ቀርቦ እንደመካፈል ሆኖ ሁሉም ጉዳይ ቀላል ሆኖ አይገኝም:: ችግርን እንደራስ አድርጎ የመቀበሉ እውነታ ሳስቶ ይታያል:: ፈተናን በእኩል የመጋራቱ አጋጣሚም እየቀነሰ ይገኛል::

በአብዛኛው ይህ እውነታ በበርካቶች የሕይወት መንገድ ላይ የሚከሰት አጋጣሚ ነው:: እንዲህ አይነቱ ሐቅ ሁሌም በሰው ልጆች ማንነት ውስጥ ይኖራል፣ ያጋጥማል ቢባልም ይህን ግድግዳ ጥሰው ታሪክን የሚለውጡ፣ ኅዘንን በደስታ የሚተኩ፣ ትኩስ ዕንባን ከፊት የሚያብሱ በርካታ ልበ መልካሞች አይታጡም::

እንዲህ አይነቶቹ ብዙ ጊዜ በመልካምነት ጎራ ሲገኙ በራሳቸው በጎ ፈቃድ እንጂ በማንም ግፊትና አነሳሺነት አይሆንም:: እነሱ በተገኙበት አጋጣሚ ሁሉ ውስጣቸው ለበጎነት ይፈጥናል:: የየዕለት ድርጊታቸውም በጥሩ ምግባር ተገንብቶ ይገለጣል::

ዓለማችን በጦርነት፣ በበሽታ፣ በድንገተኛ አደጋዎችና መሠል ሁነቶች ስትታመስ መኖሯ አዲስ አይደለም:: አንዳንዴ ይህ አይነቱ ክስተት ኃይል አላቸው ከሚባሉ መንግሥታት አቅም በላይ ሆኖ ችግሩን ለመታደግ ፈታኝ የሚሆንበት አጋጣሚ ይበረክታል:: እንዲህ በሆነ ጊዜ ማንነታቸው በቅንነት የሚገለጽ በጎ ፈቃደኞች መልካምነታቸውን አውጥተው ሲመነዝሩት ይስተዋላል::

ይህ ዓይነቱን ልብ የተቸሩ ወገኖች ታዲያ ሁሌም የሚያስቀድሙት የውስጣቸውን በጎነት ብቻ ነው:: በእነሱ ዘንድ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቀለም ፆታና ዕድሜ ይሏቸው ልዩነቶች ትርጉም የላቸውም:: ሰዎች ናቸውና ቅድሚያውን ለሰው ልጆች ክብር ይሰጣሉ:: በጎነታቸውንም በጉልበት፣ በዕውቀትና በፍቅር ገልፀው ያስመሰክራሉ::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማለት ምንም ዓይነት ግዴታ ያልታከለበት፣ ከሰብዓዊ ማንነት የሚመነጭ እውነተኛ ስሜት ነው:: ከበርካቶች መሐል ተለይተው ስለሌሎች እስትንፋስ የሚኖሩ በጎ ፈቃደኞች ዓላማና ትልማቸው ሌሎችን በመርዳት ላይ ይታነጻል:: ይህን በማድረጋቸውም ከማንም የሚጠይቁት የገንዘብ፣ የምስጋናና የአክብሮት ክፍያ የለም:: የእነሱ ዋጋ የሚለካው ያጡትን ሲያገኙ፣ የተቸገሩት ምላሽን ሲቸሩ ብቻ ነው::

በዓለማችን ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በበርካታ ተግባራት ይገለጻሉ:: ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ችግሮች መላ እንዲበጅላቸው ለማስቻልም የበጎ ፈቃደኞች አስተዋፅዖ የድርሻውን ይወጣል:: በጦርነት፣ በችግር፣ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ ለነዚህ ወገኖች ቅስቀሳና ጥሪ አያሻም:: መልካም ልቦናቸው በበጎነት የታነጸ፣ ፈጣን አካላቸው ለሰፊ እገዛ የተዘጋጀ ነውና::

በጎ ፈቃደኝነትን ሁሉም ሰው አይቸረውም:: በጎነትን ለመዋረስ በተፈጥሮ መሰጠትን ይጠይቃል:: የራስን ጥቅም አሳልፎም ስለሌሎች ፍቅር መኖር ግድ ይላል:: በጎ ፈቃደኞች በሚከውኑት መልካም ምግባር በገንዘብ የሚተመን ዋጋ የላቸውም:: የእነሱ የምንግዜም ክፍያ ከድርጊታቸው ጀርባ የሚያገኙት የሕሊና እርካታ ብቻ ይሆናል::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከማኅበራዊ መስተጋብር ባለፈ ስለ ሰላም የሚኖረው ዋጋ ከፍ ያለ ነው:: ከውስጥ ሰላማዊ ማንነት የሚመነጨው ስሜት አካባቢና ሀገርን ብሎም መላውን ዓለም ለመታደግ ኃይል አለው:: በጎ ፈቃደኞች ስለሌሎች የሚከፍሉት መልካምነት ሕይወትን በብዙ ይለውጣል፣ ዕንባን ያብሳል፣ ታሪክን ቀይሮ የምስጋና በረከት ይሆናል::

በመላው ዓለም የሚገኙ ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች ሁሌም ጊዜና ጉልበታቸውን፣ ገንዘብና ዕውቀታቸውን የሚጠቀሙት በጎ ተግባራትን በመከወን ነው:: አቅም ላጡ ምርኩዝ በመሆን ይደግፋሉ:: ትምህርትን ለሚሹ ዕውቀታቸውን ያጋራሉ:: ከዚህም ባለፈ ረሀብና ጦርነት፣ ስደትና አደጋ በደረሱባቸው ስፍራዎች ተገኝተው ከመልካምነታቸው ያካፍላሉ:: ይህን በጎነት ሲከውኑ ግን ክፍያቸው የተለመደው የሕሊና እርካታ እንጂ በገንዘብ የሚቆጠር ደመወዝ አይደለም::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመተባበር፣ የመተጋገዝ መገለጫ ነው:: አንዱ ሲወድቅ ሌላው እያነሳ መተባበሩ አብሮነትን በግልጽ ይተገብራል:: በዚህ ኅብረት መሐል ፍቅርና አንድነት ለሰው ልጆች ማንነት ወሳኝ እውነታዎች መሆናቸውን የሚያመላክት ሐቅ ይገለጣል:: በበጎ ፈቃደኞች መልካምነት በርካቶች ሕይወታቸው ተቀይሯል:: ዕንባቸው ታብሶ ፈገግታቸው ተመልሷል::

በሀገራችን በተለያዩ አጋጣሚዎች በደረሱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል:: እንዲህ በሆነ ጊዜ ሰብዓዊ ማንነታቸውን አዳምጠው በስፍራው የተገኙ በርካቶች ችግሮችን ለመታደግ ተረባርበዋል:: በራሳቸው ይሁንታ ተገፍተው ባበረከቱት በጎ አስተዋፅዖም ትርጉም ያለው ተግባራት ከውነው የወገኖቻቸውን ሕይወት ታድገዋል::

እነሆ! ሰኔ ግም ሊል ቀናት ቀርተውታል:: መጪውን የክረምት ወራት ተከትሎ ከበርካቶች የሚጠበቀው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጥቂት የማይባል ኃላፊነትን የሚጠይቅ ይሆናል:: በዚህ ወቅት ተማሪዎች ከትምህርት ቆይታ የሚያርፉበት፣ አእምሯቸውን ለዕረፍት የሚያዘጋጁበት ነው:: አብዛኞቹ ግን ይህን ጊዜ ለዋዛ ፈዘዛ አይጠቀሙትም:: መልካምነታቸው ከበጎ ተግባር አውሎ ትርጉም ያለው ተግባርን ይከውኑበታል::

የበጎ ፈቃደኞች ልብ ሁሌም ቢሆን ማረፊያው ከመልካምነት ጥግ ነው:: ለእነሱ የክረምቱ ዝናብና ጭቃ የጥንካሬቸው ማሳያ፣ የብርታታቸው ልክ እንደሆነ ይቀጥላል:: በዚህ ወቅት በበጎነት ልቦና የትራፊክ ሂደቱን ያሳልጣሉ:: የአቅመ ደካሞችን ቤት ይሠራሉ:: የተቸገሩ ወገኖቻቸውን ደግፈው ኃይልና ትከሻ ይሆናሉ::

ይህ ጊዜ በጎ ልብ ላላቸው ሁሉ ድርጊታቸው በመልካም እሴት የሚገለጽበት ነው:: በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በደም ልገሳ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት እገዛና በሌሎችም ተግባራት የሚሰማሩ ወጣቶች የድካማቸውን ፍሬ የሚያዩት ውለው ሳያድሩ ይሆናል:: ለዚህ ሁሉ በጎነታቸው ደግሞ ሽልማታቸው የንዋይ ጥቅም አይደለም:: እርካታቸው የተለመደው የሕሊና ደስታና የአእምሮ ሰላም ብቻ ነው::

በተለያዩ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎች በሚማሩበት አካባቢ ማኅበረሰቡን በማገልገል በርካታ ቁምነገሮችን ይተገብራሉ:: ይህን በማድረጋቸው በብዙ የጎደሉት ተሟልተው ክፍተቶች ይደፈናሉ:: የማኅበረሰቡ አቅም ጎልብቶ የጎበጡት ይቃናሉ:: አብዛኞቹ ይህን በማድረጋቸው የጠቀሙት ራሳቸውን እንደሆነ የሚናገሩት በሙሉ መተማመን ነው:: እርካታው በውስጣቸው ዘልቆ ሲያልፍ ይሰማቸዋል::

በሁሉም ዘንድ ውጤታማ የማኅበረሰብ አገልግሎት ይኖር ዘንድ የእርስ በርስ ግንኙነትን ውጤታማ ማድረግ ያሻል:: በሀገራችን ከጥቂት ዓመታት በፊት በሥልጠና መታገዝ የጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ለዚህ መፍትሔ እንደሆነ ዘልቋል:: ወጣቶች ለአገልግሎቱ በየቦታው ሲዘዋወሩ ባህልና አኗኗርን እንዲጋሩ አስችሏቸዋል:: የልምድ ልውውጥን በመቅሰምም በገንዘብ የሚተመነውን ዋጋ በበጎነት መክፈል ችለዋል::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማንነት አጥር አይወሰንም:: ማንኛውም ሰው በሚገኝበት ዕድሜና የኑሮ ደረጃ የአቅሙን በማበርከት በጎነቱን ማሳየት ይችላል:: ሰዎች ከሚችሉትና ካላቸው አቅም ጉልበት፣ ዕውቀትና ገንዘብ ቀንሰው ለሌሎች መድረስ ከቻሉ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ::

ችግሮች ባሉበት ሁሉ የመልካሞች በጎነት መገለጽ ባይችል የዓለማችን ሚዛን ወደአንዱ እንዳጋደለ ይቀጥል ነበር:: ክፉ አጋጣሚዎች ለበጎነት ማሳያ የመሆናቸው እውነት ደግሞ ቀይ መስቀልን የመሰሉ የሰብዓዊ ተቋማት እንዲወለዱ ምክንያት ሆኗል::

ዛሬ ለዓለማችን አንገብጋቢ ችግሮች ቀዳሚ የሰብዓዊነት ጋሻ የሆነው ቀይ መስቀል ለመመስረቱ መነሻ የሆነው አስከፊው ጦርነትና የሰብዓዊ ስሜቶች እውነታ ነበር:: የሰው ልጅ በራሱ እጆች የሚፈጥራቸው ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ክፉ ታሪኮችን የሚሽርባቸው መፍትሔዎችም ከራሱ አይርቁም:: ይህም መልካም ልቦና ባላቸው ወገኖች ድንበር አልባው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕውን እንዲሆን አስችሏል::

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በመልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You