ሳይንስ ችግር ፈቺ የምርምና የፈጠራ ሥራዎች ማዕከል ነው። መነሻቸው የተፈጠረና ያጋጠመ ችግር፤ መድረሻቸውም የችግሩ ማቅለያና መፍቻ መፍትሄ የሆኑት የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ከዘመን ጋር እየዘመኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ችግር ፈቺነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ መሄድ የሰው ልጅ የአዕምሮ ምጥቀትና የዕድገት ደረጃ ማሳያዎች ናቸው። በእነዚህ የፈጠራና የምርምር ሥራዎች በመገረም ደጋግመን ተደንቀናል ብለናል።
ዛሬ ላይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች የዓለምን አጠቃላይ ገፅታ በመቀየር ለሰው ልጆች ህይወት መቅለልና የአኗኗር ሥርዓት መልካም አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች መበራከትና የምርምር ሥራዎች መስፋፋት ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው እንደ ሀገር ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በመሠራት ላይ ያለው፤ የተፈለገውን ያህል ባይሆንም በመስኩ ውጤት መመዝገቡ አልቀረም። በተለያዩ መስኮች የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችም ላይ መታየት ጀምረዋል።
ወጣት ተመራማሪዎች ከዚህም ከዚያም መመልከታችን ሀገራችን በዘርፉ ወደፊት የምትደርስበት ደረጃ መልካም እንደሚሆን መተንበይ ያስችላሉ። ወጣቶች በግል ተነሳሽነት የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች በማበርከት ላይ ይገኛሉ። የዛሬ የሳይንስ አምዳችን የሚያስተዋውቀን ወጣት ገና 18 ዓመቱ ነው። ይህ የአስራ ስምንት ዓመት ብላቴና ከዕድሜው በመቅደም በተቸረው ብሩህ አዕምሮ ከስምንት ያላነሱ የፈጠራና የምርምር ሥራዎችን አበርክቷል።
ወጣት ፈትሂ አዲል ይባላል። በግል ፍላጎቱ ያለ ሙያዊና ቁሳቁሳዊ ድጋፍ በምርምርና በፈጠራ ሥራ ላይ ያለውን ፈተና ተቋቁሞ የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የምርምር ሥራዎችን በመሥራትና ለማህበረሰቡ በማበርከት የዜግነት ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል። ገና የ11ኛ ክፍል ተማሪና የ18 ዓመቱ ወጣት ፈትሂ በምርምርና በፈጠራ ሥራዎቹ ስኬታማና ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር የተካነ ወጣት ባለሙያ መሆኑ የፈጠራ ውጤቶቹ ምስክር ናቸው።
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ፈትሂ በልጅነቱ የተለያዩ የወዳደቁ ዕቃዎችን በማንሳት እና
በመገጣጠም ወደ ሌላ ቅርፅ በመቀየርና የተበላሹ መገልገያ መሣሪያዎችን በመጠገን ድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ያደረገው የነበረውን ልምምድ ወደ ፈጠራ ሥራ አሳድጎ ዛሬ ላይ ከስምንት ያላነሱ የፈጠራ ሥራዎችን ማበርከት ችሏል። “የልጅነት ህልሜ በአንድ መስክ የተለየ ተጽዕኖ መፍጠር ነበር” የሚለው ወጣት ፈትሂ ዛሬ ላይ በጥረቱ ከውጤት አድረሶ ተግባራዊ ያደረጋቸው የፈጠራ ሥራዎቹ ለነገ ትልቅ ደረጃ ደራሽነቱ አመላካቾች ናቸው።
የፈጠራ ሥራው ምንነት
መፍጠርን የተካነው ባለብዙ የፈጠራ ሥራ ባለቤቱ ፈትሂ እስካሁን የሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች ዘመናዊ ፀረ አረም መርጫ፣ የመስኖ ውሃ ማውጫ፣ የቤት ማሞቂያ፣ የልብስ መስፊያ መኪና፤ ኤፍ ኤም ትራንስሚተር፤ ሶሎኖይድ ኢነርጂ፤ ካር ቦርድ፤ ድሮውን፤ ፍሪ ኤሌክትሪክ እንጂን፣ የምንጣፍ ማጠቢያ ናቸው። የፈጠራ ባለሙያው ፈጠራዎቹን በአካባቢው የተመለከታቸውን የተለያዩ ችግሮች መነሻ በማድረግ እንደሚሠራቸው ይናገራል።
በተለይም፤ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ጠቀሜታውን ለማስፋት በቴክኖሎጂ ውጤቶች መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደመሆኑ የወጣቱ ባለሙያ የፈጠራ ውጤት የሆኑ የግብርና ቴክኖሎጂ ማዘመኛ መሣሪያዎች ወይም የፈጠራ ሥራዎች ፋይዳቸው ከፍ ያለ ለመሆኑ ማሳያ ነው።
ለፈጠራ ሥራው ያነሳሳው ምክንያት፡–
የፈጠራ ሥራዎች መነሻ የሚሆን ችግር ነውና ወጣት ፈትሂ በአካባቢው የተመለከታቸው ማህበራዊ ችግሮች መነሻ የሆኑት። በተለይም ባለበት የሐረሪ ክልል ውስጥ አብዝቶ በሚመለከተው ኋላ ቀር የግብርና ሥራ መነሻነትና ለገበሬዎች ቀላል የእርሻ መሣሪያዎች ያለመኖሩ ለፈጠራ ሥራው መነሻ ያደረገው ነው።
የተመለከተውን ችግር መነሻ አድርጎ መመራመርና ደጋግሞ መሞከር የሚያዘወትረው ፈትሂ እስካሁን ድረስ የፈጠራቸውን ሥራዎች ወደፊት በተሻለ መልኩ አገልግሎት ላይ ለማዋል ማስተካከያዎችን ማድረግና አዳዲስ መሣሪያዎች ማከል ተዛማጅ ነገሮችንም መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።
በፈጠራ ሥራው የተገኘ እውቅናና ሽልማት
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ፈትሂ የምርምር ሥራው ከተለያዩ ተቋማት እውቅናና ብዙ ሽልማቶችን አስገኝቶለታል። ከትምህርት ቤት ጀምሮ በፈጠራና በምርምር ሥራው እውቅናና ሽልማት በማግኘት ጥረቱና ሞራሉ የፈጠራ ባለሙያ ሥራው በሀገር አቀፍ ደረጃ እንኳን እስካሁን ድረስ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጃቸው የፈጠራ ሥራ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ሁለት ጊዜ የወርቅና አንድ ጊዜ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሜዳሊያ ሽልማቱን ደጋግሞ የወሰደው ወጣቱ የፈጣራ ባለሙያ ይህም ለፈጠራ ሥራው ትልቅ ማበረታቻ እንደሆነውና በዘርፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዳደረገው ይናገራል። በክልል በዞንና በወረዳ ደረጃ ያገኛቸው ሽልማቶችም ለሥራዎቹ ምሥጋናና ማበረታቻዎቹ ናቸው።
የፈጠራ ሥራው አሁን ያለበት ደረጃ
አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ተግባራዊ ሆነው ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርሱ ማድረግና ጥቅም ላይ ማዋል ወሳኙ ጉዳይ ነው። ነገር ግን የፈጠራና የምርምር ሥራዎች በተመራማሪው የገንዘብና የቁሳቁስ አቅም ውስንነት የተነሳ ብዙ ጊዜ ወደማህበረሰቡ ሳይደርሱ ይቀራሉ። የወጣት ፈትሂ የፈጠራ ሥራዎች ተግባራዊነታቸው ተፈትሾ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጡ ቢታመንባቸውም፤ ወጣቱ ያለበት የገንዘብና የቁሳቁስ እጥረት ሥራዎቹ በብዛት ተመርተው ለህብረተሰቡ እንዳይደርሱ እንቅፋት ሆኗል።
አሁን ላይ በተመራማሪው የሚሠሩት ውስን የፈጠራ ሥራዎቹ በፋብሪካ ደረጃ ተዘጋጅተው ለህብረተሰቡ በስፋት የሚቀርብበት ዕድል ቢመቻች አንድም፤ የፈጠራ ሥራውን ማበረታታትና ጥቅም ላይ ማዋል ሲሆን፤ በዘርፉ ተሰማርቶ ሥራውን ለመሥራት ላለመ ሰፊ የገበያ ዕድል ማግኛም መንገድ መሆኑ እሙን ነው።
የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ፣ የፈጠራ ሥራቸውን ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ ምቹ በማድረግና ሥራዎቹ ይበልጥ ተሻሽለው ከፍ ያለ ጠቀሜታ ማበርከት እንዲችሉ ማድረግ ደግሞ ሊሠራበት የሚገባ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ በብሩህ አዕምሮው ሐሳብ ይገልፃል።
በፈጠራ ሥራው የገጠመው ፈተና
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ከዘርፉ አዲስነትና ካለው አካባቢያዊ ሁኔታ አንፃር የምርምር ሥራውን ከውጤት ለማድረስ እጅግ የበዛ ፈተናና ተስፋ አስቆራጭ ገጠመኞች እንደነበሩበት ይገልፃል። ለምርምር ሥራ የተሻለ ውጤት ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ወጣት ፈትሂ በምርምር ሥራው ከዚህ ደረጃ ለመድረስ መንገዱ ምቹ ሆኖ አልጠበቀውም። በፈጠራ ሥራው የገጠመውን ፈተና በመጋፈጥ ያለመው ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል።
ለምርምር ሥራ ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ሁኔታና ልምድ አለመኖር፣ በሀገር ደረጃ ለፈጠራ ሥራ የሚሰጠው ትኩረት የጠነከረ አለመሆንና ለምርምር ሥራ የሚሰጠው ድጋፍ ማነስ የፈጠራ ሥራ ውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ አሳዳሪ ምክንያት እነደሆኑ ከራሱ ልምድ መነሻነት ያስረዳል። በተለይ በወጣትነታቸው ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች የሚሠሩ ባለሙያዎች የሚገጥማቸውን ችግር በመፍታት ለፈጠራ ሥራቸው ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ይጠቁማል።
ለጀማሪ ባለሙያዎች የፈትሂ መልዕክት
በፈጠራና በምርምር ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው ትዕግስት በተሞላበት መልኩ ሥራውን ማከናወንና የሚገጥሙትን ፈተናዎች ከተስፋ መቁረጥና በራቀ መንፈስ ሊጋፈጥ እንደሚገባ ይመክራል። በዘርፉ አዲስ ሆነው ለሚቀላቀሉ የፈጠራ ወጣት ባለሙያዎች ለምርምር ሥራቸው መልካም ውጤት በመመኘት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ እና ካለሙት ግብ ለመድረስ መትጋት ይኖርባቸዋል።
በአዲስ የፈጠራ ሥራ ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች ከሌላ አካል ድጋፍ ከመጠበቅና ከመጠየቅ ይልቅ በአካባቢያቸው ላይ ያተኮረ የምርምር ሥራ መሥራት በሚያስችሉ ቁሳቁሶች በመጠቀም ሥራቸውን አጠንክረው ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም ወጣቱ ይመክራል።
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ችግሮችን ለመፍታት የፈጠራና የምርምር ሥራዎች ወሳኝ እንደሆኑና መንግሥትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም ይናገራል። በተለይ፤ የምርምር ሥራዎች በተሻለ መልኩ ተጠንተውና ትኩረት ተሰጥቷቸው ለህብረተሰቡ ጥቅም መስጠት እንዲችሉ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፤ የሚለው ወጣቱ ተመራማሪ ለዘርፉ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ይጠቁማል።
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ፈትሂ ከዚህ የፈጠራ ሥራው በተጨማሪ ሌሎች የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅዶች እንዳሉትም ይናገራል። በተለይም በግብርና ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመፍጠርና በዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ፍላጎቱ መሆኑን ይናገራል። “ወደፊት እጅግ የበዙ ዕቅዶች አሉኝ ለሀገሬ ኢትዮጵያ ጥሩ ነገር ማበርከት እፈልጋለሁ” ለሚለው ፈትሂ ስኬት ተመኘን። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2011
ተገኝ ብሩ