“ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የባሕር በር የማግኘት መብት አላት” -አምባሳደር ግሬጎር ሹስተርቺትስ

አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት አምባሳደር ግሬጎር ሹስተርቺትስ ገለጹ።

የኢንስብሩክ ዩኒቨርሲቲ የአውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ እና የአውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ሕጎች የክብር ፕሮፌሰር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የባሕር በር ኮንቬንሽን መሠረት የባሕር ዳርቻ ካላቸው ጎረቤት ሀገራት ጋር በመስማማት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የባሕር በር የማግኘት መብት አላት።

አምባሳደር ግሬጎር ሹስተርቺትስ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ “የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር ዳርቻ ማግኘት የሚችሉበት ዕድል ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንደጠቀሱት፤ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መርህ በሚካሄድ ድርድር የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት ዓለም አቀፍ ሕጎች የሚያረጋግጡት እውነት ቢሆንም ይህ መብት ተፈጻሚነት የሚኖረው የባሕር ዳርቻ ካለው ሀገር ጋር በሚደረግ ስምምነት ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የባሕር በር ሕግ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢው ያለውን የባሕር በር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት መደንገጉን ጠቁመው፣ የባሕር ኮንቬንሽን አንቀጽ 25 ወደብ የሌላቸው ሀገሮች ወደ ባሕር የመግባት መብት እንዳላቸው ይገልጻል። ይህ መብት የባሕር በር ባለው ሀገር እና የባሕር በር በሌለው ሀገር መካከል ስምምነት ላይ ከተደረሰ ሊፈጸም እንደሚችልም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከብዙ ሀገራት ጋር ስምምነት መፍጠር የሚያስችል ልዩ አማራጮች አሏት፣ ነገር ግን ዕድሉን ለመጠቀም መንገዶችን መፈለግ እና ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን መምረጥ ይኖርባታል ያሉት አምባሳደሩ፤ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው እንቅስቃሴ የአካባቢውን ፍላጎት ባገናዘበ እና በፍትሃዊነት መርሆች ላይ በተመሠረተ መንገድ መሆን አለበት ሲሉም አመልክተዋል።

“እኔ የባሕር በር ያለኝ ሀገር ብሆን ኖሮ ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት የባሕር መዳረሻን እሰጣት ነበር ምክንያቱም የንግድ ልውውጥ፣ ሰፊ የሥራ እድል፣ የቱሪስት ፍሰት፣ ምግብ ቤት እና ሌሎች እድሎችን ስለሚያመጣ በኢኮኖሚ በጣም ጠቃሚ ነው” ያሉት አምባሳደሩ፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ዕድሉን በመመልከት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አብሮ ለማደግ ይሠራሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You