
አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት ኢትዮጵያ ከወርቅ ሁለት ነጥብ 057 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ከ29ሺህ 396 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡም ተገልጿል፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዮስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት ከ29ሺህ 396 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ፣ ሁለት ነጥብ 57 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
ከክልል ለብሔራዊ ባንክ የቀረበ የወርቅ መጠን ሲታይ በዋናነት፤ ከትግራይ ክልል 12ሺህ 210፣ ከኦሮሚያ ስድስት ሺህ 910፣ ከጋምቤላ አራት ሺህ 590፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ሦስት ሺህ 689 ኪሎ ግራም ወርቅ መቅረቡን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት፤ የመንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንክ እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲጠብቅ በማድረጉ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን እንዲጨምር በማድረግ ለውጤቱ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በባሕላዊ እና አነስተኛ ወርቅ ምርት ለተሰማሩ አምራቾች ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው ማበረታቻ የአምራቾችን የማምረት ፍላጎት አነቃቅቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም የወርቅ ሕገ ወጥ ንግድ እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ምርታማነትን የሚያሳድጉ የማምረቻ መሳሪያዎች የሚጠቀሙ አምራቾች ቁጥር መበራከት፤ በቅድም ምርት ላይ ለሚገኙ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉ፤ ለወርቅ አምራቾች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱ እና ዘርፉን የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ምግባቱ ለምርቱ እድገት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ምርታማነትን ለመጨመር እና ማዕድን የወጣባቸው ቦታዎች እንዲያገግሙ ከማድረግ አኳያም በልዩና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው የሚያመርቱ የወርቅ አምራቾችን በማስተባበር ተረፈ ምርታቸውን በአቅራቢያቸው ላሉ ትላልቅ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች እንዲያቀርቡ የማድረግ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል።
የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑ ዘርፎች መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፍ መሆኑን በማውሳት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋራ በመሆን፤መንግሥት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀራረብ እና በመናበብ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ሚሊዮን እንደተናገሩት፤ በሌሎች ማዕድናት አመርቂ የሆነ ውጤት እየተመዘበ የሚገኝ ሲሆን፤ ግብይቱን ዘመናዊ ከማድረግ አኳያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማዕድን ልማት ኢንስቲትዩት እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በመፈራረም በጋራ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በዋናነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ከወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ከማዕድን ልማት ኢንስቲትዩት፣ ከጅኦሎጂካል ኢንስቲትዩት እና ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም