
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እያሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ማዕቀብ ለመጣል ያሰቡት ተባብሶ በቀጠለው ደም አፋሳሹ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ደስተኛ ባለመሆናቸው እና ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረጉ ሙከራዎች እስካሁን ውጤት ባለማስገኘታቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሬዚዳንቱ በካቢኔያቸው ስብሰባ ላይ፣ ‹‹ፑቲን ብዙ ሰው እየገደለ ነው። ብዙዎቹ የእርሱ ወታደሮችና የዩክሬን ኃይሎች ናቸው›› ብለዋል። በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ስለመጣል ጉዳይ ተጠይቀው፣ ‹‹ጠንከር አድርጌ እያሰብኩበት ነው›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። ስለእቅዳቸው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
ትራምፕ ስለማዕቀብ ሃሳባቸው የተናገሩበት ጊዜ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በብሪታኒያ ፓርላማ ተገኝተው አውሮፓ ዩክሬንን ፈፅሞ እንደማይዘነጋት ከተናገሩት ንግግር ጋር ተገጣጥሟል። ፈረንሳይና ዩናይትድ ኪንግደም ከአጋሮቻቸው ጋር በመተባበር ዩክሬንን ለመደገፍ እንደሚሠሩ ማክሮን ተናግረዋል። ‹‹ጠንካራና ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ እንታገላለን። ዩክሬን ውስጥ አደጋ ላይ የወደቁት የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች እኛንም የሚመለከቱ ናቸው›› ብለዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው፣ ሩሲያ ተጨማሪ ድርድሮችን ለማድረግ ዩክሬን ድርድር የሚካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ እንድታሳውቅ እየጠበቀች እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን እንደምትልክ ትራምፕ አስታውቀዋል። ለዩክሬን ከሚላኩት መሣሪያዎች ውስጥ ዋናዎቹ የአየር መከላከያ መሣሪያዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል። ‹‹ተጨማሪ መሣሪያዎችን እንልካለን። ዩክሬኖች ራሳቸውን መከላከል አለባቸው›› ብለዋል።
የመከላከያ መሥሪያ ቤቱ ፔንታጐንም አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ መሣሪያዎችን እንደምትልክ አረጋግጧል። የፔንታጐን ቃል አቀባይ ሾን ፓርነል በሰጡት መግለጫ፣ ዩክሬናውያን ራሳቸውን መከላከል መቻላቸውን ለማረጋገጥ አሜሪካ ተጨማሪ የመከላከያ መሣሪያዎችን እንደምትልክ ገልፀዋል። ጦርነቱ ቆሞ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ጥረቷን እንደምትቀጥልም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ወደ ሌሎች ሀገራት የምትልካቸው የጦር መሣሪያ አቅርቦቶች የአሜሪካን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም ፓርነል ገልፀዋል።
ከቀናት በፊት አሜሪካ ለዩክሬን ከምትሰጣቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን ማቋረጧን አስታውቃ ነበር። ውሳኔው የተወሰነው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ ለሌሎች ሀገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ መገምገሙን ተከትሎ የአሜሪካን ጥቅም ለማስቀደም እንደሆነ ዋይት ሐውስ መግለጹ ይታወሳል።
ርምጃው የተወሰደው የአሜሪካ ወታደራዊ መሣሪያዎች ክምችት እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ መሆኑን ተዘግቦ ነበር። ይህ ውሳኔ የተላለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ቭላድሚር ዘሌንስኪ ጋር ከሁለት ሳምንታት በፊት በኔዘርላንድስ በተካሄደው የ‹ኔቶ› ጉባኤ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነው። በወቅቱ ትራምፕ አሜሪካ ተጨማሪ ፀረ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን ትሰጥ እንደሆን ተጠይቀው ‹‹አንዳንዶቹን ማቅረብ እንችል እንደሆነ የምናየው ይሆናል›› ማለታቸው ይታወሳል። ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት መወሰኑ ዩክሬንንና አጋሮቿን ክፉኛ አስጨንቆ ነበር።
ሩሲያም በዩክሬን ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች። ባለፉት ሳምንታት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ከፈፀመቻቸው ጥቃቶች ሁሉ ትልልቅ ናቸው የተባሉ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች። በጥቃቶቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሊስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማለች።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ያስገባት መሠረታዊ ችግር ካልተወገደ ጦርነቱን እንደማታቆም ተናግረዋል። ፑቲን ከቀናት በፊት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ ሞስኮ ከኪዬቭ ጋር ወደ ጦርነት ያስገቧት መሠረታዊ ምክንያቶች ሳይወገዱ እና የጦርነቱ መሠረታዊ መነሻ እልባት ሳያገኝ ጦርነቱ እንደማይቆም ነግረዋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ ዝግጁ መሆናቸውን እና ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርጋቸውን ውይይቶች ለመቀጠል ፈቃደኛ ብትሆንም፣ ማንኛውም የሰላም ድርድር መደረግ ያለበት ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው በሩሲያና ዩክሬን መካከል እንደሆነ ገልፀውላቸዋል።
‹‹ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ›› ተብሎ ተሰይሞ የነበረውና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት፤ ዛሬም ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል። ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩት ጥረቶች ሁሉ ትርጉም ያለው ውጤት ማስገኘት አልቻሉም። ሁለቱም ሀገራት የሚፈፅሟቸውን ጥቃቶች በየፊናቸው አጠናክረው ቀጥለዋል። ሩሲያ ተኩስ ለማቆም ያስችላል ባለችው ዝርዝር እቅድ ውስጥ የተካተቱት ቅድመ ሁኔታዎቿም በዩክሬንና በምዕራባውያን አጋሮቿ ተቀባይነት ያገኛሉ ተብሎ አይታሰብም። ለዚህም ነው ብዙ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ሩሲያና ዩክሬን የመስማማት ተስፋ አላቸው? ዘላቂ የተኩስ አቁም ብሎም የሰላም ስምምነትስ ይፈራረሙ ይሆን…?›› ብለው አበክረው የሚጠይቁት።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም