ብሩህ አእምሮ ያለው ትውልድ ለመገንባት ሕጻናት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በሥነ ምግባር የታነጸና በእውቀት የበለጸገ ትውልድ ለመገንባት ሕጻናት ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የኬንያ ሞንባሳ ግዛት አስተዳዳሪ አብድልስዋማድ ሸሪፍ እና ሉካቸው በአዲስ አበባ ከተማ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም የልምድ ልውውጥ ከትናንት ጀምሮ ለአራት ቀናት እያደረጉ ይገኛል፡፡በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ የመጪውን ትውልድ ሁኔታ የሚወስኑት የዛሬ ሕጻናት ናቸው፡፡ ከእዚህ አኳያም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥነ ምግባር የታነጸና በእውቀት የበለጸገ ትውልድ ለመገንባት ለሕጻናት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ በተለያየ መልኩ የሚነሱ የልማት፣ የማህበራዊ ፍትህ እና ሌሎች ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትና ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ፈርጀ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ የሚደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ በዛሬ ሕጻናት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ሕጻናት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራም ዛሬ የሚታዩ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ወደፊት እየተፈቱ የማይሄዱበት እድል አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ እንደተናገሩት፤ ችግር ብቻ ሳይሆን ሀገርን መገንባት የሚችሉ አዕምሮዎች እና ብቃቶችን ማግኘት የሚቻለው ሕጻናት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም ሕጻናት ላይ ኢንቨስት በማድረግ እንደ ከተማ ለሕጻናት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን ለሕጻናት እድገት ምቹና ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ ሥርዓት በጣም ወሳኝ ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ ሥርዓት መዘርጋት እንዲያስችል በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ከተማ የተሠራው ሥራ መሠረታዊ የሆነ የዳሰሳ ጥናት ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሕጻናት የእድገት ደረጃ በምን ደረጃ እንደሚገኝ በተሠራው መሠረታው የዳሰሳ ጥናትም ሁለት ነገሮችን ለመረዳት መቻሉን ጠቁመው፤ ጥናቱን መሠረት በማድረግ ተሻጋሪ እና አካታች የሆኑ እቅዶች መነደፋቸውን አመልክተዋል፡፡ሥራዎቹን ማስፈጸም የሚችሉ አመራሮች እና ጽሕፈት ቤቶች እንዲኖሩ የማድረግ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ከሕጻናት አስተዳደግ አንጻር ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት፤ ሕጻናትን እና ወላጆችን የሚያማክሩ አምስት ሺህ አሰልጣኞች በማሰልጠን ወደ ሥራ ለማሰማራት ተችሏል፡፡

በኬንያ የሞንባሳ ግዛት አስተዳዳሪ አብድልስዋማድ ሸሪፍ በበኩላቸው፤ በከንቲባው ተቀርጸው እየተተገበሩ ያሉ በርካታ መርሃ ግብሮች የሚደነቁ እና ማስተማሪያ የሚሆኑ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ከተግባር ተሞክሮ የበለጠ አስተማሪ የለም ያሉት አስተዳዳሪው፤ በሚኖራቸው ቆይታ በሁሉም ዘርፍ ትልቅ ልምድ እንደሚያገኙ እምነታቸውን በመግለጽ፤ ለተደረገላቸው የልምድ ልውውጥ ገለጻ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You