የማሊ ወታደራዊ መሪዎች በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አገዱ

የማሊ ወታደራዊ መሪዎች በሀገሪቱ ያሉ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አገዱ። “በመላው ሀገሪቱ ያሉ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ስብስብ እና ፖለቲካዊ ባሕሪ ያላቸው ድርጅቶች በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ” እንዲሆኑ ከወታደራዊው ቡድን (ሁንታ) ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ወጥቶ በሀገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን የተነበበው መግለጫ አስታውቋል።

መግለጫው እኤአ በ2020 እና 2021 በማሊ በተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በጨበጡት ወታደራዊው መሪ አሲሚ ጎይታ የተፈረመ ሲሆን፣ ወታደራዊ መሪው ምርጫ ተካሂዶ ሥልጣን እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ቢያንስ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በመንበራቸው ላይ ይቆያሉ ተብሏል። ይህ የወታደራዊው ቡድን ውሳኔ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገባ ሲጠይቁ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞን እንደሚቀሰቀስ ይጠበቃል።

ካለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ወዲህ የወታደራዊው መንግሥት ባለሥልጣናት በሀገሪቱ በሚካሄዱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ርምጃ እየወሰዱ ነው። ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው የዴሞክራሲ ጥያቄ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በኋላ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፖሊስ መሆናቸውን በገለጹ በታጠቁ ግለሰቦች ታፍነው ተወስደዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የማሊ ባለሥልጣናት ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።

ወታደራዊው መንግሥት ባዘጋጀው ባለፈው ወር በተጠራው እና ዋነኛ የሀገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባልሆኑበት ጉባዔ ላይ የወታደራዊው ቡድን መሪ ጄኔራል አሲሚ ጎይታ እስከ እኤአ 2030 ድረስ በፕሬዚዳንትነት እንዲቀጥሉ ሃሳብ ቀርቧል።

እኤአ በ2022 በሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ እንደሚካሂድ ቃል ገብቶ ከነበረው ወታደራዊ መንግሥት በኩል የቀረበው ይህ ሃሳብ ከተቃዋሚ መሪዎች እና ከሠብዓዊ መብት ቡድኖች በኩል ውዝግዘት ገጥሞታል። አሁን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለማገድ የወጣውን አዋጅ የማሊ ዜጎች ችላ ሳይሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔ በጣሱ ላይ ምን ዓይነት ርምጃ እንደሚወሰድ ግን የተባለ ነገር የለም ተብሏል።

አዋጁ ጨምሮም በፖለቲካዊ ወይም አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ ተሠማርተው ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች “ከለፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ሥራቸውን ማከናወን መቀጠል” እንሚችሉ ገልጿል። ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማገድ ውሳኔ የመጣው በመንግሥት አዘጋጅነት ከተካሄደው ሀገራዊ ጉባዔ በኋላ የቀረበውን የመሪውን የሥልጣን ዘመን የማራዘም ሃሳብ ከቀረበ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።

በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ቡድን ባለፈው ሳምንት የሀገሪቱን የሽግግር አስተዳደር በመቃወም ተቃውሞ ለማሰማት ጥሪ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለውን ዕገዳ ተከትሎ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፎ ነበር። የተቃዋሚ ቡድን መሪዎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከእንቅስቃሴ ውጪ የማድረጉን የወታደራዊ መሪዎቹን ውሳኔ አውግዘውታል።

ሙሳ ማራ የተባሉት የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እና የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር በወታደራዊው መንግሥት የተላለፈው ዕገዳ “ባለፈው ዓመት በተጀመረው የእርቅ ጥረት ላይ የተፈጸመ ትልቅ ጥቃት ነው” ሲሉ ገልጸውታል። አንድ የማሊ ጉዳይ ተንታኝ እንዳሉት ወታደራዊ መሪዎቹ ይህንን ርምጃ የወሰዱት “ከሀገሪቱ ነጻነት አንስቶ በአመራር ላይ ያሉትን እና አሁን ድረስ ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው የሚባሉትን ቀደምት ልሂቃንን ከመንግሥት ውስጥ ለማስወጣትት ነው።”

የወታደራዊ መንግሥቱ መሪ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙት ከቡርኪናፋሶ እና ከኒጀር ወታደሮች ጋር የትብብር ኅብረት በመመሥረት ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቀነስ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል። የማሊ ወታደራዊ መሪዎች በመፈንቅለ መንግሥት የያዙትን ሥልጣን ምርጫ በማካሄድ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመለሱ በመጠየቁ ምክንያት ጄነራል ጎይታ ማሊን ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ማኅበር ኤኮዋስ አስወጥተዋታል።

በተመሳሳይ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀርም ከማኅበሩ ራሳቸውን አግልለዋል። ይህንንም ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ሦስቱ ተጎራባች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ትብብር መሥርተው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You