
“የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2025” ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፦ የፋይናንስ ዘርፉ ሕጋዊ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ተደራሽነቱን ሊያሰፋና አቅሙን ሊያሳድግ ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም ትናንት መካሄድ የጀመረው “የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2025” ዛሬ ይጠናቀቃል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ “የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2025” መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የዋጋ ንረት፣ የተከማቸ ብድር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና መሰል ችግሮች ነበሩበት። መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም ቀላል፣ ግልፅና ቅንጅታዊ የአሠራር ሥርዓት መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገኘውን ስኬት ይበልጥ ለማሳደግ የፋይናንስ ዘርፉ ሕጋዊ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ተደራሽነቱን ሊያሰፋና ያለውን አቅም ሊያሳድግ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት አንፃር የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን ይበልጥ ማጠናከርና ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ከዓለም ባንክ ድጋፍ እንድታገኝ ያስቻለ መሆኑን ተናግረው፤ በማሻሻያው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚመጥን አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር መሠረት መጣል ተችሏል ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ ድርሻ እንዲያድግ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጉልህ ሚና ማበርከቱን የገለጹት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ለተገኘው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት ለውጤታማነቱ ጉልህ ሚና ማበርከቱን ገልጸዋል።
የፋይናንስ ፎረሙ ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት በዘርፉ ያከናወነቻቸውን ሥራዎችንና በዚህም የተገኙ ውጤቶችን ያስገነዝባል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ይህም በዘርፉ ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎችን እና ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት እንዴት ማሳካት እንደሚቻል አቅጣጫ ይጠቁማል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት የብድር መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ለአስተዳደር አዳጋች እንደነበር እና በሕጋዊ የውጭ ምንዛሬ ገበያውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሬ መጠን የተራራቀ እንደነበር ተናግረዋል።
ይህንንም ለማስተካከል ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ተደርጓል። ይህም የዋጋ ንረት በፊት ከነበረበት 35 በመቶ አካባቢ ወደ 13 ነጥብ ስድስት በመቶ ዝቅ እያለ እንዲመጣ ማድረጉን አስረድተዋል።
በማሻሻያው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ እንደተቋቋመ እና በባንኮች መካከል ዲጂታል የገበያ ሥርዓት እንዲኖር መደረጉን የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ፤ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ድጋፍና ዕውቅና ማግኘቱን ጠቁመዋል።
ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አብዛኛው ሥራ አሁን በጠንካራ ሁኔታ ላይ እንዳለ ገልጸው፤ ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ፋይናንስ ዘርፉ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲወዳደር አሁንም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የዘርፉ ተዋናዮች ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተጣጥመው የራሳቸውን ዐሻራ ማሳረፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም