ሕንድ እና ፓኪስታን “ተኩስ አቁሙን በመጣስ” እርስ በርስ ተወነጃጀሉ

ሕንድ እና ፓኪስታን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን ከገለፁ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን “በመጣስ” ወነጀሉ። በሕንድ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ካሽሚር ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቪክራም ሚስሪ ” ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ተደጋጋሚ ጥሰት ተፈጽሟል” ብለዋል።

የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ “በተወሰኑ ስፍራዎች በሕንድ የተፈጸሙ ጥሰቶች እያሉም ቢሆን. . . ለተኩስ አቁሙ ትግበራ ቁርጠኞች ነን” ብለዋል። ባለፉት አራት ቀናት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ግጭት ባለፉት አስርት ዓመታት በመካከላቸው ከታየው ወታደራዊ ፍጥጫ ሁሉ የከፋ ነበር ተብሏል።

ሕንድ ባለፈው ወር በፓልጋም ለደረሰው ጥቃት ምላሽ በሚል በፓኪስታን እና ፓኪስታን በምታስተዳድረው ካሽሚር ግዛት ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን፣ ሚሳኤሎች እና ሌሎች ተተኳሾች የታገዘ ድብደባ አድርጋለች። ፓኪስታን የ26 ሂንዱዎችን ሕይወት በቀጠፈው ጥቃት ላይ እጄ የለበትም ብላ ብታስተባብልም ሕንድ ግን በመንግሥት በሚደገፉ አማፂያን የተፈጸመ ነው ስትል ትሞግታለች።

ለአራት ቀን ከቆየው ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት በኋላ ፓኪስታን እና ሕንድ ሙሉ እና ወድያውኑ ተፈጻሚ የሚሆን የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል። ሁለቱ ሀገራት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል። አክለውም በአሜሪካ ሸምጋይነት በሁለቱ ኒውክሌር ታጣቂ ሀገራት መካከል ተኩስ ለማቆም ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

የፓኪስታኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢሻቅ ዳር ሀገራቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን አረጋግጠዋል። ሚንስትሩ ለሀገራቸው የመገናኛ ብዙኃን በዲፕሎማቲክ ጥረቱ ውስጥ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊን ጨምሮ “በርካታ ሀገራት” መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

የሕንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቪክራም ሚስሪም በበኩላቸው “በምድር፣ በአየር እና በባሕር” ሀገራቸው የምትወስደውን ርምጃ ለማቆም መስማማቷን አረጋግጠዋል። ጨምረውም ተኩስ አቁሙ በሰዓታት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ብለው ነበር። ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ ከጥቂት ሰዓት በኋላ በሕንድ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ግዛት የሚገኙ ነዋሪዎች ፍንዳታዎችን መስማታቸውን እና በሰማይ ላይ ፍንጥቅጣቂዎችን ማየታቸውን ተናግረዋል።

የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቪክራም ሚስሪ “ላለፉት ጥቂት ሰዓታት ከደረስነው ስምምነት በተቃራኒ ተደጋጋሚ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ይህ አስቀድሞ የተስማማንበትን የጣሰ ነው” ብለዋል። ሚስሪ የሕንድ መከላከያ ኃይል “ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ” ትዕዛዝ መተላለፉን ተናግረዋል። አክለውም “ፓኪስታን ስለተፈጸመው ጥሰት ማብራርያ እንድትሰጥ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው “ፓኪስታን ቀደም ብሎ በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል ለተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ቁርጠኛ መሆኗን መግለጽ እፈልጋለሁ። ምንም እንኳ በተወሰኑ አካባቢዎች በሕንድ የተኩስ አቁሙ ቢጣስም የጦር ኃይላችን ጉዳዩን በኃላፊነት እና በመታቀብ ተቆጣጥሮታል።

“የተኩስ አቁምን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስፈጸም ማንኛቸውም የሚኖሩ ጉዳዮች በተገቢው ደረጃ በመግባባት ሊፈቱ ይገባል ብለን እናምናለን። የተሰማሩ ጦር ኃይሎችም ቢሆኑ ከማንኛውም ነገር መታቀብ አለባቸው” ብለዋል።

ካሽሚር በሕንድ እና በፓኪስታን የይገባኛል ጥያቄ የሚቀርብባት ግዛት ስትሆን ነገር ግን ሁለቱም ሀገራት ከብሪታንያ ነጻነታቸውን ካገኙበት እአአ 1947 ጀምሮ በከፊል ብቻ እያስተዳደሯት ይገኛል። የይገባኛል ጥያቄው ለሁለቱ ኒውክሌር ለታጠቁ ሀገራት ምንጊዜም የፍጥጫ ምክንያት ሲሆን ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ያህል ወደ ጦርነት ገብተዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ያረጋገጡት የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሁለቱ ሀገራት ” ተኩስ ለማቆም እና ወታደራዊ ተግባራትን ለመግታት” መስማማታቸውን ተናግረዋል። “ሕንድ በሁሉም መልኩ እና መገለጫዎች በሽብርተኝነት ላይ ያለማቋረጥ ጠንካራ እና የማያወላዳ አቋሟን ቀጥላለች። ይህንንም አጠናክራ ትቀጥላለች” ብለዋል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የተኩስ አቁም ስምምነት “ለሁሉም ሰው ጥቅም” ሲባል መደረሱን ተናግረዋል። የተኩስ አቁም ይፋ መደረጉን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ሕንድ እና ፓኪስታን በገለልተኛ ቦታ በሰፊው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለመጀመር ተስማምተዋል ብለዋል። እርሳቸው እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ከሕንድ እና የፓኪስታን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሀገራቱን ጠቅላይ ሚንስትሮች ናሬንድራ ሞዲ እና ሼህባዝ ሻሪፍን ጨምሮ ለ48 ሰዓታት ያህል ንግግር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ግጭቱን ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ” በደስታ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል። የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሰር ኬር ስታርመር ብሪታንያ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ላሚ በኩል ከሁለቱም ወገኖች ጋር “ለተወሰኑ ቀናት” በውይይት ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ሰር ኪር “ዛሬ የተኩስ አቁም ስምምቱን ተደርሶ በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ካሉ በኋላ “አሁን የሚኖረው ተግባር ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ነው” ማለታቸው ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You