
ዜና ሀተታ
የተሰጣቸውን ማንኛውንም ሥራ በጥንቃቄ እና በትኩረት እንደሚያከናውኑ በብዙዎች ይመሰከሩላቸዋል:: የጀመሩትን ሥራም ከዳር ሳያደርሱት ወደ ኋላ አይሉም:: ይህን ልዩ ባህሪያት የተላበሱት በአብዛኛው እንስቶች እንደሆነ ይገለጻል::
ለዚህ ማሳያ የሚሆነን የአፍሪካ ሴቶች እርስ በእርሳቸው ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት እና የጠንካራ ሥራ ውጤት የሆኑ ሥራዎቻቸውን ለገበያ ይዘው የሚቀርቡት ታላቅ የንግድ ትርኢት ላይ በቀጠሯቸው መሠረት ተገናኝተዋል:: ሥራዎቻቸውንም አሳይተዋል:: በቅርቡ ስድስተኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢትና ኮንፍረንስ አፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ተካሂዷል::
የንግድ ትርኢቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሴቶችን ያሳተፈ አህጉራዊ ውህደት ውጤታማ መሆኑ ጥርጥር የለውም ይላሉ:: የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግም የኮሜሳ አባል ሀገሮች የበለጠ ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል:: አምባሳደሯ በንግግራቸው አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል::
በሥራዋ በርካታ ጠንካራ ሴት ገበሬዎችን የምትወክለው እና ሥራዎቿን በተመለከተ ማህበራዊ ትስስር ገጹዋ ላይ በምታጋራቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች በርካታ ተከታዮችን ያፈራችው እና በቅርቡም የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነችው በረከት ገበሬዋ በኤግቢሽኑ ተግኝታለች:: በረከት ገበሬዋ የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነችው ወይዘሮ በረከት አደራ የማህበሩ አባል በነበረችበት ወቅት ይህ የንግድ ትርኢት ባሳለፍነው አመት በማዳጋስካር መካሄዱን አስታውሳ፤ በማጠቃለያው ኢትዮጵያ በቀጣይ እንድታዘጋጅ እድሉ ሲሰጣት ደስተኛ እንደነበረች ገልጻለች::
2ኛው የኮሜሳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ኮንፍረስ እንዲሁም 6ኛው የነጋዴ ሴቶችና ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት ላይ በርካታ የሀገሯ ሴቶችን እንዴት በዚህ መድረክ ማሳተፍ ይችላሉ የሚለውን ስታቅድ እንደነበር አስታውሳለች::
የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ኃላፊነቱን ከተረከበች በኋላም ይህንን አህጉር አቀፍ የሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሴቶችን ባህላቸውን፣ ሥራዎቻቸውንና አቅማቸውን እንዲያስተዋውቁ ተደርጓል በማለት ገልጻለች::
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አቅም ያነሳቸውን ሴቶችን በማበረታታት በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ወደ ኋላ የቀሩ ሴቶችን የሚያስፈልጋቸውን ድጋፎች በማድረግ በንግድ ትርኢቱ ሥራዎቻቸውን ይዘው እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል ነው ያለችው::
የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ ሴቶችን ከሌሎች ነጋዴዎች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል የፈጠረ ነው ስትል ገልጻለች:: ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ባዘጋጀችው በዚህ የሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር በስሩ ባሉ የክልል ማህበር የተውጣጡ ሴቶችን በመመልመል ባህላዊ ምግብና አልባሳትን ፣ የእደ-ጥበብ ውጤቶች ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ፣ ቡና አምራቾች ሥራዎቻቸውን ይዘው መቅረባቸውን ነው የገለጸችው::
የኮሜሳ የነጋዴ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ኮንፍረንስ በ21 የአባል ሀገራቱ ነጋዴዎችና ሥራ ፈጣሪዎች የልምድ ልውውጥ እና ከአፍሪካ ውስጥ እርስ በእርስ ግብይት የምናደርግበት ነው ስትል የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ በረከት ገልጻለች::
ማህበሩ ሕጋዊ የንግድ ፍቃድ ያላቸው ሴቶች ወደ ማህበሩ በመምጣት በሚኖሩባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች የነጋዴ ሴቶች ማህበርን መቀላቀል እንደሚችሉ ወይዘሮ በረከት ገልጻ፤ ማህበሩ ሥልጠና ለሚያስፈልጋቸው ሥልጠናዎችን በማመቻቸት እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ሴት ነጋዴዎች ራሳቸውን እንዲያበቁ እና ሥራቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚሠራ ገልጻለች::
ጸሀይ ብዙሀኔ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን በመወከል የጉራጌ ፣ ስልጤና እና ሀላባ ማህበረሰብ አልባሳት መገልገያ እቃዎች እንዲሁም በክልሉ በስፋት የሚገኙ እና የሚታወቁባቸው የባልትና ውጤቶች ይዛ ቀርባለች:: ጸሀይ ይህንን እድል በክልሎች በተቋቋሙ የሴት ነጋዴ ማህበር አማካኝነት በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት መገኘቷን ገልጻለች፡፡
ኹነቱ በኡትዮጵያ መዘጋጀቱ እንደ ሀገር መልካም ተሞክሮ ነው በማለት የምትገልጸው ጸሀይ፤ በዚህ ኹነት የመጀመሪያ ተሳታፊ ሆና በመቅረቧም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጻለች ::
ሴቶች በባህሪያቸው ትኩረት ሰጥተው አንድን ሥራ የሚያከናውኑ በመሆናቸው በሚሰማሩበት ማንኛውም ዘርፍ ስኬታማ መሆን ይችላሉ የምትለው ጸሀይ፤ መሰል የንግድ ትርኢቶች እና የሴቶችን አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች መድረኮች መስፋፋት እንደሚገባቸው ገልጻለች ::
በስድስተኛው የሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት ላይ ሙሉ ለሙሉ በእጅ የሚሠሩ የእደ-ጥበብ ውጤቶችን ይዛ የቀረበችው ዛምቢያዊቷ ወጣት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ ቢዝነሷን ለማሳደግ ጥሩ እድል እንደፈጠረላት ገልጻለች:: ወጣት ካሊንጋ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች ሲሆን በዛሚቢያ የሚገኘው የኮሜሳ አማካኝነት እድሉን እንዳገኘችም ትገልጻለች ::
ዲዛይነር ካሊንጋ በርካታ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎች የተገኙበት ይህ የንግድ ትርኢት አፍሪካውያን እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ እና በተሰማሩበት ዘርፍ ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ እድል የሚፈጥር ነው ስትል ገልጻለች ::
ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተናገደችው 6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢትና ኮንፍረንስ ከ21 አባል ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ ሴት ነጋዴዎች እንደተሳተፉበት ታውቋል::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም