የትራምፕ ያልተጠበቀ የእግር ኳስ የሰላም ተስፋ!

በእግር ኳስ ምክንያት የለየለት ጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራት በጥቂት የታሪክ አጋጣሚም ቢሆን ታይተዋል። ያምሆኖ በእግር ኳስ አማካኝነት የተገቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ ወደ ሰገባቸው የተመለሱ ሰይፎች በብዙ አጋጣሚዎች ታይተዋል። ለዚህም ነው እግር ኳስ የሰላም ምልክት ነው የሚባለው።

በእርግጥም እግር ኳስን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ሰላምን የመፍጠር፣ የተጣላን የማስታረቅ ትልቅ ኃይል አለው። ከሦስት ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ የዓለም ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን እግር ኳስ እንዲሁም አጠቃላይ ስፖርት ፈተና ገጥሞታል። የዓለምን እግር ኳስ የሚመራው ፊፋ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ሌሎች በርካታ የዓለምን ስፖርት የሚመሩ ተቋማት ሩሲያ ዩክሬንን ወራለች ብለው ከየትኛውም የውድድር መድረክ አግልለዋታል።

ይህ የዓለም አቀፍ ስፖርት ተቋማት ውሳኔ ከስፖርት መርህ አኳያ ተገቢ ባለመሆኑ የተቃወሙ በርካቶች ናቸው። “ስፖርትና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው” የሚለውን ወርቃማ መርህ የተጣረሰ መሆኑን በማንሳትም የሩሲያ ከዓለም ውድድሮች መገለል ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ሲሉ ዛሬም ድረስ ብዙዎች ይቃወማሉ። አሁንም ድረስ ግን ስፖርትን እንደ አንድ መፍትሄ ቆጥሮ የሁለቱን ሀገራት ጦርነት ለማቆምም ይሁን ለማብረድ ጥረት ያደረገ አካል የለም።

ከሰሞኑ ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተለየ ሃሳብ ይዘው ብቅ ብለዋል። የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን ጨብጠው ነጩ ቤተመንግሥት በገቡ በ24 ሰዓት ውስጥ የሁለቱን ሀገራት ጦርነት አስቆማለሁ ያሉት ትራምፕ ከመቶ ከቀናት በተሻገረ የሥልጣን ዘመናቸው ሃሳባቸው ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም። ጦርነቱን ለማስቆም ይህ ቀረህ የማይባል ርምጃ ሲወስዱ የቆዩት ትራምፕ ሰላም የማስፈን ውጥናቸው እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም። ተስፋ ግን አልቆረጡም። አሁንም በተለያየ መንገድ ሙከራቸውን ቀጥለዋል። ስፖርት የሁለቱን ሀገራት ጦርነት ያስቆማል ብለው ያስባሉ ብሎ ግን ማንም አልጠበቀም።

የ2026 የዓለም ዋንጫን ከካናዳና ሜክሲኮ ጋር በጣምራ የምታስተናግደው አሜሪካ ባለፈው ረቡዕ በዘመነ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፊፋን ባለሥልጣናት ጋር ተወያይታለች። በዚህ ውይይት ወቅት ነው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያልተጠበቀውን ሃሳብ የዘረገፉት። “የ2026 የዓለም ዋንጫ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ምክንያት ሊሆን ይችላል” ያሉት ትራምፕ የሩስያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ እንዳይሳተፍ የተጣለበትን እገዳ ማንሳት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እ.ኤ.አ. በየካቲት 2022 ከተጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የሩሲያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እና የሀገር ውስጥ ክለቦች በፊፋ እና በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር መታገዳቸው ይታወቃል። የሩሲያን ከእግር ኳስ መታገድ በሰሙበት ወቅት በእጅጉ የተገረሙት ዶናልድ ትራምፕ፣ እገዳውን ከሩሲያ ላይ ማንሳት ጦርነቱ እንዲቆም እንደ ማበረታቻ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

“አላውቅም የሩሲያ ከእግር ኳስ መታገድ ግን ተገቢ ነው?” በማለት ለፊፋውን ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ጥያቄ የሰነዘሩት ትራምፕ፣ የዓለም እግር ኳስ ከሚመሩት ጣሊያናዊ ቁርጥ ያለ መልስ ነበር የተሰጣቸው። “አዎን መታገዷ ትክክል ነው” ነው በማለት የመለሱት ኢንፋንቲኖ በሩሲያ ላይ የተጣለው የእግር ኳስ እገዳ በቅርቡ ሊያበቃ እንደሚችል ግን ያላቸውን ተስፋ ከመግለፅ አልተቆጠቡም። ለዚህም ጦርነቱ ቆሞ ሰላም ሊሰፍን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ትራምፕም የፊፋውን አለቃ መልስ ቀበል አድርገው “ ይቻላል፣ ሩሲያን ወደ እግር ኳስ መመለስ ጦርነቱን ለማቆም ጥሩ ማበረታቻ አይሆንም ትላለህ፣ ጦርነቱን እንዲያቆሙ እንፈልጋለን፣ በማይታመን ሁኔታ በየሳምንቱ በዚህ ጦርነት አምስት ሺህ ወጣቶች እየረገፉ ነው።” ብለዋል። ያም ሆኖ ሩሲያን ወደ እግር ኳሱ የመመለስና በዓለም ዋንጫው እንድትሳተፍ የመወሰን ሥልጣኑ የኢንፋንቲኖ በመሆኑ የፊፋው አለቃ እንዲያስቡበት ትራምፕ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You