
የዓለማችን ቱጃርና የማይክሮሶፍት መሥራች የሆነው ቢል ጌትስ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ጠቅላላ ሀብቱን ለሌሎች ለመስጠት ማቀዱን አስታወቀ። ጌትስ የሀብቱን 99 በመቶ ወይንም 200 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በርዳታ ድርጅቱ በኩል ለመስጠት ማቀዱን ነው ይፋ ያደረገው።
ቢል ጌትስ ሀብቱን ለሌሎች የሚያከፋፍለው በፋውንዴሽኑ በኩል መሆኑን ገልጾ፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2045 ሥራ እንደሚያቆም ተናግሯል። “ስሞት ሰዎች ስለ እኔ ብዙ ነገር ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን እርግጠኛ የምሆነው ‘ከእነ ሀብቱ ሞተ’ የሚለው ከወሬያቸው መካከል እንደማይሆን ነው” ሲል ሐሙስ ዕለት በብሎጉ ላይ ጽፏል።
የ69 ዓመቱ ጌትስ በስሙ ያቋቋመው ፋውንዴሽን እስካሁን ድረስ 100 ቢሊዮን ዶላር ለጤና እና ለልማት ፕሮጀክቶች መስጠቱን ገልጾ፣ በቀጣይ ሁለት አስርት ዓመታት እስከ 200 ቢሊዮን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ተንብይዋል። ቢል ጌትስ በብሎጉ ላይ ታዋቂው አንድሪው ካርኒጌ በ1889 የሀብት ወንጌል ሲል በሰየመው ጽሑፉ ላይ ቱጃሮች ሀብታቸውን ለማኅበረሰቡ መልሰው የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው ማለቱን ጠቅሷል።
ጌትስ “ሀብታም እንደሆነ የሚሞት ሰው እርሱ ክብሩን ጥሏል” ሲል ካርኒጌ የጻፈውን ጠቅሷል። ጌትስ በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በኩል ሀብቱን መስጠቱን እንደሚያቀላጥፍ ቃል ገብቷል። ከዚህ በፊት እርሱ እና የቀድሞ ባለቤቱ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ሕይወታቸው ካለፈ በኋላም ለበርካታ አስርተ ዓመታት የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እየሠራ እንዲዘልቅ ፍላጎት ነበራቸው። ይህ የውሳኔ ለውጥ እንዴት እንደመጣ ሐሙስ ዕለት ቢቢሲ ኒውስ አወር ሲጠይቀው በሚቀጥሉት 20 ዓመት ውስጥ የወደፊቱን ተግዳሮቶች በተሻለ ሁኔታ መፍታት የሚችሉ ሌሎች ሀብታም ሰዎች ይኖራሉ ሲል መልሷል። እንዲሁም “ለነገሮች ቅድሚያ የመስጠት ጉዳይ ነው” ብሏል።
“ዘላለማዊ ለመሆን ካልሞከርን በስተቀር ብዙ ተጨማሪ ወጪ ልናወጣ እንችላለን። እና ወጪው ከእሴቶቼ ጋር የተጣጣሙ እንደሚሆኑ አውቃለሁ።” ቢል ጌትስ የሀብቱን 99 በመቶ ቢሰጥም ቢሊየነር ሆኖ እንደሚቀጥል የብሉምበርግ ዘገባ ያሳያል። የማይክሮሶፍት መሥራቹ ቢል ጌትስ የዓለማችን አምስተኛው ሀብታም ነው።
ጌትስ በብሎጉ ላይ ባሰፈረው ረዥም ጽሑፍ ሀብቱን በጊዜ ሰሌዳ ዘርዝሮ ያስቀመጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተጣራ የሀብት መጠኑ 108 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ያሳያል። ይህንን የሀብቱን መጠን እአአ በ2045 ዜሮ ለማድረስ ማቀዱንም በዚሁ ጽሑፉ ላይ አስፍሯል።
ቢል ጌትስ ከጓደኛው ፖል አለን ጋር በጋራ በመሆን በእአአ በ1975 ማይክሮሶፍትን የመሠረቱ ሲሆን በኮምፒውተር ሶፍትዌር የዓለምን ገበያ መቆጣጠር ችሏል። ጌትስ ቀስ በቀስ በድርጅቱ ውስጥ ካለው ተሳትፎ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በ2000 ከአመራርነቱ በ2014 ደግሞ ከሊቀመንበርነቱ ለቋል። ቱጃሩ ቢልጌትስ ገንዘቡን ለሌሎች ለማከፋፈል የተነሳሳው ከባለሃብቱ ዋረን በፊት እና ሌሎች በጎ አድራጊዎች በመመልከት መሆኑን ተናግሯል። ይሁን እንጂ ተቺዎቹ ቢል ጌትስ ፋውንዴሽኑን ግብርን ላለመክፈል እንደ መሸሸጊያ ይጠቀምበታል ሲሉ ይተቹታል።
ጌትስ በብሎጉ ላይ በጻፈው ረዥም ጽሑፍ ፋውንዴሽኑ ሦስት ዓላማዎችን ዘርዝሯል። መከላከል የሚቻሉ እና እናቶችን እና ሕጻናትን ገዳይ የሆኑ በሽታዎችን ማጥፋት፣ ወባን እና ኩፍኝን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ማጥፋት፣ እንዲሁም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት ማውጣት ናቸው። ጌትስ አሜሪካ፣ ዩኬ እንዲሁም ፈረንሳይ ለውጭ ርዳታ የሚያውሉትን በጀት መቀነሳቸውን ተችቷል።
“የዓለማችን ሀብታም ሀገራት ለድሃ ሕዝቦች ይቆሙ እንደሆን ግልጽ አይደለም” ሲል ጽፏል። “ነገር ግን አንድ ነገር እርግጠኛ የምንሆነው፣ ጌትስ ፋውንዴሽን በሁሉም ሥራዎቹ ሀገራትን እና ሕዝቦች ከድህነት እንዲወጡ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል “ዶናልድ ትራምፕ የመንግሥት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ በሚል የመሠረቱትን መሥሪያ ቤት እንዲመራ የሾሙትን ባለሀብቱን ኤለን መስክ የአሜሪካን ርዳታ በማቋረጥ ሕጻናትን እየገደለ ነው ሲል መተቸቱን በተመለከተ ተጠይቆ “የርዳታ ማቋረጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናትን ነው የሚገድለው፣” ብሏል።
“የዓለማችን ቱጃር ሰው ይህንን ያደርጋል ብለህ አትጠብቅም” ሲል አክሏል። ጌትስ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበረው ቆይታ ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ሰርጥ “ለሃማስ” ኮንዶም ለመግዛት የሚውል ነው በሚል ለሆስፒታል ይሰጥ የነበረ የርዳታ ገንዘብ ስለማቋረጣቸው በማንሳት ተናግሯል። መስክ በኋላ ላይ ዶናልድ ትራምፕ ያሉት ስህተት መሆኑን ጠቅሶ “ስህተት እንሠራለን” ቢልም ርዳታው ግን ሳይቀጥል ቀርቷል። “ያንን ርዳታ በማቋረጡ [መስክ] በኤች አይቪ የተጠቁ ሕጻናትን ሄዶ ቢያይ እመኛለሁ።” ሲል ጌትስ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናግሯል።
በአንድ ወቅት ጌትስ እና የቴስላ ባለቤት ኤለን መስክ የዓለማችን የቱጃሮች ሚና መሆን ያለበት ሌሎችን ለማገዝ ገንዘብ መስጠት መሆኑን ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጋጭተዋል። ጌትስ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ ታዳጊ ሀገራት በጤና ዘርፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም