አሜሪካ በሁቲ አማፂያን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ልታቆም ነው

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በየመን የሁቲ አማፂያን ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ ልታቆም መሆኑን ገለፁ። ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት የሁቲ አማፂያን “ጥቃት መፈፀም በማቆማቸው” መሆኑን ተናግረዋል። ኦማን በበኩሏ በኢራን በሚደገፉት አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ላለመፈጸም መስማማታቸውን አስታውቃለች።

ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በዋሺንግተን በተገናኙበት ወቅት “[ሁቲዎች] መዋጋት አይፍልጉም፤ እኛ ደግሞ ያንን እናከብራለን፤ እናም የአየር ድብደባ ማካሄዳችንን እናቆማለን፤ ስለዚህ እነሱም ጥቃት ማድረሳቸውን አቁመዋል” ብለዋል።

የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለቱም ወገኖች አንደኛቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት ላለመሰንዘር መስማማታቸውን ገልጸዋል።”በባሕሩ ላይ በሰላም የመቅዘፍ ነጻነትን ለማረጋገጥ እና የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ፍሰት የተሳለጠ እንዲሆን” ስምምነት መደረጉን የዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ተከትሎ የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ለጥፏል።

ሁቲዎች እስካሁን ድረስ ተደረሰ ስለተባለው ስምምነት ያሉት ነገር የለም። በመጋቢት ወር አሜሪካ በሁቲዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላ፣ በየመን 1,000 ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የመከላከያ ኃይሉ አስታውቋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከኦቫል ኦፊስ እንደተናገሩት “ሁቲዎች ከአሁን በኋላ መርከቦች ላይ አይተኩሱም” “ሁቲዎች እንዳስታወቁት፣ ወይንም ቢያንስ ለእኛ እንደገለፁልን፣ ከአሁን በኋላ አይዋጉም. . . ነገር ግን የበለጠ ጠቃሚው ነገር ቃላቸውን አምነን መቀበላችን ነው።”የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አል ቡሳይዲ ውጥረቶች እንዲረግቡ ሀገራቸው ማሸማገሏን ተናግረዋል።

“ወደፊት ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት አይፈጽሙም፤ በቀይ ባሕርም ሆነ በባብ አል መንደብ የአሜሪካ መርከቦችን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች በነጻነት እንዲቀዝፉ እንዲሁም የተሳለጠ ፍሰትን ለማረጋገጥ ተስማምተዋል” ብለዋል።

ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመሩት እ.አ.አ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በፍልስጤማውያን ላይ መክፈቱን ተከትሎ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በሚል እንደሆነ አውስቶ ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You