የኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ተግባራት አርአያነታቸው የጐላ ነው !

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የታለበሱ ሕዝቦች ናቸው። በርሃብም ሆነ በድርቅ፤ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅቶች በመደጋገፍ እና በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን በማሳለፍ ይታወቃሉ። ሆኖም ዜጎች እርስ በእርሳቸው ከሚያደርጉት መረዳዳት በሻገር መንግሥት ዜጎችን በዘላቂነት የመደገፍ እና የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በሕገመንግሥቱ ጭምር ዕውቅና የተሰጠው ነው።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም የተሻለ የሚባል የማህበራዊ ፖሊሲ ይፋ አድርጋለች። ፖሊሲው በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድህነትን፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ተጋላጭነትንና መገለልን ለመቀነስ የሚያስችል እና ዜጎች በዘላቂነት ራሳቸውን መደገፍ የሚችሉበትን መንገድ የሚቀይስ ነው። ፖሊሲው ዜጎች ርዳታን ዘላቂ አድርገው መኖር እደዳያስቡ እና በዘላቂነትም አምራች ሆነው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መትረፍ እንዲችሉ እገዛዎችን የሚያደርግ ነው።

ፖሊሲው በዋናነት በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ለመከላከል፣ ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ የዜጎችን ሠርቶ የማግኘትና ጥሪት የመያዝ አቅምን ለማጎልበት፣ የሥራ እድልንና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የተዘጋጀና ለጥቃትና በደል ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሕግ ጥበቃና ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ ነው።

ይህን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ማህበራዊ ጥበቃ በማድረግ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛው ትልቁ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ሲሆን በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል እና በከተሞች የሚተገበር ነው።

ይህ የሴፍትኔት ፕሮግራም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ምርታማ ባልሆኑ እና ለተፈጥሮ እና የድርቅ አደጋዎች በተደጋጋሚ የሚጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ ሲሆን በሂደትም ዜጎች ከሴፍትኔት ተረጂነት ተላቀው በራሳቸው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። በብዙ ጥናቶች እንደተመላከተው ድህነት የገጠር ብቻ ሳይሆን የከተማም ችግር ነው። ከተማ ውስጥም የድሃ ድሃ የሚባሉ ማህበረሰቦች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን ኢትዮጵያ የዘረጋችውም የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያቅፍ እና ከከተማ ድህነት ራሳቸውን አላቀው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ነው።

መንግሥት የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን መሠረት በማድረግ ዜጎች በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ፤ በኑሮ ውድነት እና መሰል ችግሮች እንዳይጎዱ በየዓመቱ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ድጎማ እያደረገ ዝቅተኛው የህብረሰብ ክፍል በችግሮች እንዳይጠቃ የመጠበቅ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በሴፍትኔት ፕሮግራም ከሚደረጉ ቀጥተኛ ድጋፎች በተጨማሪ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የመንግሥት ሠራተኞች በኑሮ ውድነቱ እንዳይጎዱ በማሰብ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል። አርሶ አደሩም በማዳበርያ ዋጋ እንዳይጎዳ በማሰብ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድርጓል። በተመሳሳይ ለነዳጅ ከ84 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ዜጎችን የመጠበቅ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በተመሳሳይም አዲስ አበባ አስተዳደር በየዓመቱ ከ 12 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ለዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ከለላ በማድረግ ላይ ይገኛል። በየአመቱ ወደ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ግብዓት በነጻ እንዲያገኙ ይደረጋል። 850 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እያደረግን እንገኛለን። ይህ ትምህርት ቤት ምገባ ለተማሪ ወላጆች ትልቅ እፎይታ ከመፍጠሩም በሻገር ትውልድ የመገንቢያ አንዱ መንገድ ነው።

አቅመ ደካማ የሆኑ እናቶችን ለመደገፍ እየተደረገ ባለው ጥረት በሴፍትኔት ተደራጅተው ወደ 200 ሺ የሚጠጉ እናቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ሕይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ። አቅመ ደካሞች ለሆኑና በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለሚፈልጉ ሁሉ በራቸውን ክፍት አድርገው የሚጠብቁ 35 የምገባ ማዕከላት ተከፍተው በቀን ከ50 ሺ በላይ አቅም ደካሞችን እያገለገሉ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛው ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የማድረጉ ተግባርም ዚሁ ማህበራዊ ጥበቃ አንዱ አካል ነው። ለውጡ እውን ከሆነበት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮም በየዓመቱ ከ10 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በአጠቃላይ እንደ ሀገር እየተከናወኑ ያሉ የማህበራዊ ጥበቃ ተግባራት የአቅመ ደካሞችን ሸክም ከማቅለሉም ባሻገር እንደሀገርም መረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህልን የሚያሳድግ በመሆኑ አርአያነቱ ከፍ ያለ ነው።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You