እስራኤል በሁቲዎች ላይ የአጸፋ ርምጃ ወሰደች

እስራኤል እሁድ ለተፈጸመባት ጥቃት በሁቲዎች ላይ የአጸፋ ርምጃ ወሰደች፡፡ የየመን ሁቲዎች በዴቪድ ቤን ጎሪዮን አየር ማረፊያ ላይ ለፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃት አጸፋ የመን ውስጥ የሚገኙ የቡድኑ ዒላማዎች መምታቱን የእስራኤል ጦር አስታወቀ። የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ጥቃት የተፈጸማባቸው ስፍራዎች በየመን ሁዳይዳህ ወደብ ላይ እና በከተማዋ በሚገኝ የሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ ሲሆን እነዚህም “የሁቲ ኃይሎች የአቅርቦት ማዕከል” ናቸው ብሏል።

ሁቲዎች እሁድ ዕለት በእስራኤል የአየር ማረፊያ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ፣ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ለማስፋፋት ላወጣችው ዕቅድ ምላሽ አየር ማረፊያዎቿን ዒላማ በማድረግ “አጠቃላይ የአየር እንቅስቃሴዎቿን እናቅባለን” ብለዋል። የአየር ጥቃቱን “የአሜሪካ እና የእስራኤል የጋራ ወረራ” ነው ያለው በኢራን የሚደገፈው ሁቲ እስራኤል ሰኞ ዕለት በፈጸመችው ጥቃት 21 ሰዎች ቆስለዋል ብሏል። አሜሪካ ግን በጥቃቱ ተሳትፎ እንደሌላት አስተባብላለች።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል የተፈጸመው ጥቃት “በወደብ ላይ የቆሙ መርከቦችን ለመከላከል የተወሰደ ግልጽ ርምጃ” ነው ብሏል። ጥቃት የተፈጸመበት የሲሚንቶ ፋብሪካ የቡድኑ “ወሳኝ የገንዘብ ምንጭ” መሆኑን እና ከመሬት በታች መተላለፊያዎችን እንዲሁም መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚያገለግል ነው። በተጨማሪም ወደቡም “ከኢራን የሚመጡ የጦር መሣሪያዎች መተላለፊያ ነው” በሚል ዒላማ ሆኗል።

ጥቃት የተፈጸመበት ወደብ የመን ካሏት የባሕር በሮች መካከል ሁለተኛው ትልቁ ሲሆን፣ ወደ ሀገሪቱ ከሚገባው ምግብ 80 በመቶ በዚሁ ወደብ በኩል ነው። የተለያዩ በወደብ ከተማዋ የሚኖሩ ምንጮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ከ 10 በላይ ጥቃቶች በሁዳይዳህ ወደብ እና በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ተመትተዋል፤ ሌሎች አራት ጥቃቶች ደግሞ የሲሚንቶ ፋብሪካውን ዒላማ አድርገዋል።

በሁቲ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኒስ አል-አስባሂ፣ ቢያንስ 21 ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሁቲዎች ጥቃቱ የተፈጸመው በአሜሪካ እና በእስራኤል የጋራ ጥምረት ነው ሲሉ ከሰዋል። ነገር ግን አንድ አሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን ለፈረንሳይ ኤና ወኪል ኤኤፍፒ ኃይሎቻቸው “እስራኤል [ሰኞ] በፈጸመችው የአየር ጥቃት አልተሳተፉም” በማለት አስተባብለዋል።

ባለፈው እሁድ ሁቲዎች ተኩሰው ከቴል አቪቭ አቅራቢያ ቤን ጎሪዮን አየር ማረፊያ ወደ ዋነኛው የመንገደኞች ማስተናገጃ በሚወስደው መግቢያ መንገድ ላይ ወድቆ ነበር። በፍንዳታው አራት ሰዎች መቁሰላቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ መደበቂያ ቦታ ሲያመሩ ቆስለዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጥቃቱን ተከትሎ የአጸፋ ርምጃ እንደሚወስዱ “ከዚህ በፊትም ጥቃት ፈጽመናል፣ ወደፊትም ጥቃት መፈጸማችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ሁቲዎች በእስራኤል አየር ማረፊያ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት በተመለከተ ኢራን እጇ እንደሌለበት ቡድኑ “ጥቃቱን በራሷ ውሳኔ ያደረሰው ነው” ብላለች። አሜሪካ በየመን ሁቲዎች ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃቶችን ስትፈጽም ቆይታለች። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በሁቲ ኃይሎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላም ጥቃቱ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በሰሜን ምዕራብ የመን ውስጥ በሚገኘው የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማ ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን ሁቲዎች አስታውቀው ነበር ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You