
እስራኤል ሶሪያ ውስጥ የአየር ጥቃቶችን መፈፀሟን ቀጥላለች። ትናንት በዋና ከተማዋ ደማስቆና አካባቢው የተፈፀመውን ጥቃት የእስራኤልና የሶሪያ መገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል። በደማስቆና አካባቢው ከተፈፀሙት ጥቃቶች በተጨማሪ በዕለቱ ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚርቀው ሃማ አካባቢም ሌሎች ጥቃቶች ተፈፅመዋል።
የእስራኤል ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን የሀገሪቱ ጦር ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እና ከመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ ባገኘው ይሁንታ የጥቃት ኢላማዎችን ለይቶ መምታቱን ገልጿል። የእስራኤል ጦር ሶሪያ ውስጥ በወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን እና ፀረ-አውሮፕላን መሣሪያዎችንና ከምድር ወደ ሰማይ የሚወነጨፉ ሚሳኢሎችን ማውደሙን አስታውቋል።
ይህ ጥቃት የተፈፀመው እስራኤል ደማስቆ ውስጥ በፕሬዚዳንታዊው ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ተመሳሳይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ የሶሪያ የሽግግር መንግሥት ጥቃቱን ካወገዘ ከሰዓታት በኋላ ነው። የፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን አል-ሻራ መንግሥት የእስራኤል ጥቃቶች አደገኛና ውጥረትን የሚያባብሱ እንደሆኑ ገልፆ፣ እስራኤል ጥቃቶችን እንድታቆም አሳስቧል።
የአልጀዚራው ዘጋቢ ኢምራን ካሃን ከደማስቆ ባሰራጨው ዘገባ፣ እስራኤል ኢላማ ያደረገቻቸው የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሺር አል-አሳድ ጦር ይጠቀምባቸው የነበሩ ወታደራዊ ይዞታዎችን እንደሆነ ገልጿል። እስራኤል ከዚህ ቀደም መሰል ጥቃቶችን እንደፈፀመች የገለፀው ካሃን፣ ‹‹እስራኤል ይህን የምታደርገው እስከአፍንጫዋ የታጠቀች ጎረቤት ሶሪያን ማየት ስለማትፈልግ ነው›› ብሏል።
የሶሪያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የእስራኤልን ጥቃት በፅኑ ኮንኗል። ድርጊቱ ሶሪያ እንዳትረጋጋና የፀጥታ ኃይሏም እንዳይጠናከር የማድረግ ግዴለሽ እንቅስቃሴ እንደሆነ ገልጿል። ‹‹ሶሪያ በሉዓላዊነቷና በጸጥታዋ አትደራደርም። ሁሉንም አማራጮች ተጠቅማ የሕዝቧን መብት ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት አጠራክራ ትቀጥላለች›› ብሏል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተለይም የዓረቡ ዓለም፣ ሀገሪቱን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርቧል።
ኳታር የእስራኤልን ጥቃቶች ‹‹የሶሪያን ሉዓላዊነትና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሰ ግልጽና ሀፍተረቢስ ወረራ›› በማለት አውግዛለች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ እስራኤል በሊባኖስ፣ በሶሪያና በጋዛ የምትፈፅማቸው ጥቃቶች ቀጣናውን ወደማያባራ ቀውስና ብጥብጥ የሚከቱ አደገኛ ድርጊቶች እንደሆኑ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ሶሪያ ውስጥ የምትፈፅመው ጥቃት በአካባቢው ሌላ ውጥረት እንዳይፈጥር ተሰግቷል። እስራኤል ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮም ሶሪያ ውስጥ የተመረጡ ጥቃቶችን ስትፈፅም ቀይታለች። በተለይም የበሺር አል-አሳድ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የጦር መሣሪያ ለደህንነቴ ስጋት ይሆናሉ ባለቻቸው ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ በሚል ምክንያት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈፅማለች።
ሰሞኑን የሶሪያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከደማስቆ ደቡባዊ አቅጣጫ ከሚኖሩት የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ፍጥጫ አገርሽቷል። የሶሪያ መንግሥት ኃይሎች ከድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ በርካታ የማኅበረሰቡ አባላት የተገደሉ ሲሆን ይህ ደግሞ እስራኤልን አስቆጥቷል።
እስራኤልም ደማስቆ ውስጥ በሶሪያ ፕሬዚደንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የፈፀመችው ጥቃት የሶሪያ መንግሥት ኃይሎች በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ለፈፀሙት ግድያ ምላሽ እንደሆነ ገልፃለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የሶሪያ ኃይሎች ከደማስቆ ደቡባዊ አቅጣጫ እንዲሰማሩ እና በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ስጋት የሚደቅን ክስተት እንዲፈጠር አንፈቅድም›› ብለዋል።
የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት የሺአ እስልምና ተከታዮች ሲሆኑ በሶሪያ፣ በእስራኤልና በሊባኖስ ይኖራሉ። እስራኤል የማኅበረሰቡን አባላት እንደአጋሯ የምትቆጥራቸው ሲሆን፣ ብዙ ድሩዞች የእስራኤል ጦር አባላት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የሶሪያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና አጋሮቻቸው ጃራማናና ሳህናያ በተባሉ ከደማስቆ ደቡባዊ አቅጣጫ በሚገኙ አካባቢዎች እንዲሁም በስዌዳ ከተማ ‹‹ሃይማኖታዊ›› በተባለ ጉዳይ ምክንያት ከድሩዝ ታጣቂዎች ጋር በፈጠሩት ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ በኋላ ነው የእስራኤል ባለሥልጣናት የሶሪያ መንግሥት የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላትን ከጥቃት የማይጠብቅ ከሆነ፣ ሀገራቸው ርምጃ እንደምትወስድ ያስጠነቀቁት። የመከላከያ ሚኒስትሩ ካትዝ ‹‹እስራኤል ተመጣጣኝ ርምጃ ትወስዳለች›› ሲሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒትሩ ጌዲዮን ሳር ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶሪያ የሚገኙ ህዳጣን ማኅበረሰቦችን ከጥቃት ለመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሶሪያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል-ሻዕባኒ በየትኛውም ምክንያት የሚደረግ የውጭ ጣልቃ ገብነት አለመረጋጋትን ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ገልጸዋል።
የድሩዝ ማኅበረሰብ መንፈሳዊ መሪ ሸህ ሂክመት አል-ሂጂሪ ለጥቃቱ መንግሥትን ተጠያቂ አድርገዋል። በጃራማናና ሳህናያ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በጥብቅ አውግዘው፣ ጥቃቶቹን ‹‹የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች›› ብለዋቸዋል። መንፈሳዊ መሪው ባወጡት መግለጫ ‹‹ይህ ታስቦበት የተፈፀመ የጅምላ ግድያ ግልጽና ሁሉም ያየው ድርጊት ነው። ራሱን መንግሥ ብሎ በሚጠራው አካል ላይ እምነት የለንም። ጽንፈኛ ቡድኖችን አሰማርቶ የራሱን ሕዝብ የሚገድል አካል መንግሥት ሊባል አይችልም›› ብለዋል።
የአልጀዚራው ኢምራን ካሃን እስራኤል በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ለተፈፀመው ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ እንደሰጠች ብትገልፅም የማኅበረሰቡ መሪዎች ግን በዚህ ደስተኛ እንዳልሆኑ ዘግቧል። ‹‹እስራኤል ለድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ያላትን አጋርነት ለመግለፅ ጥቃት ብትፈፅምም የማኅበረሰቡ መሪዎች ግን እስራኤል ጥበቃ እንድታደርግላቸው እንደማይፈልጉ ገልጸዋል›› ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በሶሪያ መንግሥትና በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ተወካዮች መካከል ከተካሄዱ ጠንካራ ድርድሮች በኋላ የመንግሥት ኃይሎች ከአካባቢዎቹ መውጣታቸውንና ውጥረቶችም መርገባቸውን ካሃን ገልጿል።
እስራኤል የበሺ አል-አሳድን መንግሥት የገለበጡትን ኃይሎች ያሰባሰበውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት በበጎ አትመለከተውም። ቀደም ሲል እስራኤል የአልሻራን መንግሥት ‹‹ከኢድሊብ ተነስቶ ደማስቆን በኃይል የተቆጣጠረው የሸብር ቡድን›› ብላ ሰይማው ነበር።
እስራኤል አንድ ጊዜ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተከማቸው የጦር መሣሪያ ለደህንነቴ ስጋት በሆኑ ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሶሪያ መንግሥት አጋሮቼ የሆኑትን የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላትን ከጥቃት ሊታደግ አልቻለም በሚሉ ሰበቦች ሶሪያ ውስጥ በተከታታይ የምትፈፅማቸው ጥቃቶች፣ ዓይነተ ብዙ ፍላጎት ባላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሽኩቻ ምክንያት አስተማማኝ መሆን ለተሳነው የሶሪያ ሰላምና ፀጥታዋ ሌላ ስጋት እንዳይሆን የብዙዎች ስጋት ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም