በሚያንማር አዲስ ርዕደ መሬት ሊከሰት ይችላል ብሎ በቲክቶክ ላይ የተናገረው ኮከብ ቆጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉ ተነገረ። ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ገጥሟት በነበረው ሀገር ውጥ የሚገኘው ቲክቶከሩ ኮከብ ቆጣሪ ርዕደ መሬት ይከሰታል ብሎ የሠራው ቪዲዮ በርካታ ሰዎችን አስደንግጧል።
ጆን ሞ የተባለው ይህ ግለሰብ ቪዲዮውን በቲክቶክ ላይ የለቀቀው በሚያንማር በርዕደ መሬት መለኪያ 7 ነጥብ 7 መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተ በሁለተኛው ሳምንቱ ነበር። ቀደም ሲል በደረሰው የመሬት ነውጥ ከ 3 ሺህ 500 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ጥንታዊ ቤተ መቅደሶችም ፈራርሰዋል።”ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ሕዝብን በማስደንገጥ” ተከሶ ቲክቶከሩ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጿል።
ግለሰቡ በቲክቶክ ላይ በሚቀጥለው ግንቦት ወር ቀኑን ጠቅሶ ሌላ ርዕደ መሬት “በሁሉም የሚያንማር ከተሞች ይከሰታል” ሲል ነበር ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ የተናገረው። የመሬት መንቀጥቀጥን ለመተንበይ በርካታ ከግምት የሚገቡ ነገሮች በመኖራቸው የአደጋውን መከሰት በእርግጠኛነት ለማወቅ እንደማይቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ በሚያንማር ጠመሬት ነውጥ ይከሰታል ብሎ የተነበየው ቲክቶከሩ ያሠራጨው ቪዲዮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን አግኝቷል። “ርዕደ መሬቱ ሲነሳ ዋጋ የምትሰጧቸውን እቃዎች ይዛችሁ መሸሽ አለባችሁ። ትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥም እንዳትቀመጡ” ሲል ቲክቶከሩ ተከታዮቹን አስጠንቅቋል። ያንጎን ከተማ የምትኖር ሴት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገረችው ጎረቤቶቿ ቲክቶከሩን አምነውታል። ቤት ውስጥ አንቀመጥም ብለውም በፍርሃት ከቤታቸው ወጥተዋል።
አሁን የግለሰቡ የቲክቶክ ገጹ ቢታገድም፣ ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች የነበሩት ሲሆን፣ በኮከብ ቆጠራ የወደፊቱን እንደሚተነብይ ይናገራል። ግለሰቡ በማዕከላዊ ሚያንማር ሳጋንግ በሚገኘው መኖሪያው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል። ማንዳሊ እና ሳጋንግ ከዚህ ቀደም በተነሳው ርዕደ መሬት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የመሬት መንቀጥቀጡ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በሚገኙ አካባቢዎች ንዝረቱ በመድረሱ እስከ ጎረቤት ሀገር ታይላድ ድረስ ጉዳት ደርሷል። በታይላንድ ዋና ከተማዋ ባንኮክ በመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት ምክንያት ሕንጻዎች ፈራርሰዋል ለብዙዎች ሞት ምክንያትም ሆኗል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም