ከ 142 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምርቶች ማስወገዱን ባለሥልጣኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ግምታዊ ዋጋቸው ከ 142 ሚሊዮን በላይ የሚያወጡ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ የተበላሹ ምግቦች እና ጤና ነክ ምርቶችን ማስወገዱን የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይህን ያስታወቀው ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ከማዕከል ጀምሮ ቅርንጫፍ እና ክላስተር ከሚገኙ አመራሮችና ዳይሬክቶሬቶች፣ አጠቃላይ ሠራተኞች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ስለተከናወኑ የሥራ አፈጻጸሞች በገመገመበት ወቅት ነው።

ባለሥልጣኑ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ስላከናወናቸው የሥራ አፈጻጸሞች በተመለከተ ሰነድ ያቀረቡት የባለሥልጣኑ እቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት አቶ አስመላሽ ደርጋሶ እንደተናገሩት፤ ግምታዊ ዋጋቸው 51 ሚሊዮን 348 ሺህ 613 ብር የሚያወጡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች ተወግደዋል። እንዲሁም 91 ሚሊዮን 440 ሺህ 759 ብር የሚያወጡ የተበላሹ ምግብና ጤና ነክ ምርቶች በአጠቃላይ ከ142 ሚሊዮን ብር በላይ ምርቶች መወገዳቸውን ገልጸዋል።

የተወገዱትም 23 ሺህ 515 ኪሎ ግራም መድኃኒት፣ 241 ሺህ 804 ኪሎ ግራም ምግብና ጤና ነክ ምርቶች እንዲሁም 71 ሺህ 522 ሊትር መጠጥና ፈሳሽ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም በሰው ተኮር ተግባራት የተከናወኑ ሥራዎች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከማዕከል እስከ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮችና ፈጻሚዎችን በማሳተፍ ከ20 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን አውስተው፤ ባለሀብቶችን በማስተባበር ለአንድ ሺህ 500 የማህበረሰብ ክፍሎች ሁለት ሚሊዮን 535 ሺህ 320 ብር የሚያወጣ የማዕድ ማጋራት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

12 ቤቶች ፈርሰው በአዲስ መልክ ተሠርተው ለነዋሪዎቹ ርክክብ መደረጉን፣ ለአንድ ሺህ 250 ወንድ እና ለ 1 ሺህ 825 ሴት በድምሩ 3 ሺህ 075 ዜጎች የነፃ ህክምና እንዲያገኙ ከጤና ተቋማት ባለንብረቶች ጋር በመቀናጀት መሠራቱን አውስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከህከምና ስህተትና የባለሙያ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ከቀረቡ አቤቱታዎች ለ28ቱ የተለያዩ ውሳኔዎች መስጠት መቻሉን ፣ ለ21 ሺህ 620 ተቋማት እና ለ11 ሺህ 933 ጤና ባለሙያዎች ብቃት መሰጠቱን፣ በ47ሺህ 308 ተቋማት ላይ ቁጥጥር በማድረግ በአንድ ሺህ 136 ተቋማት ላይ የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸውን እንዲሁም ለጤና ባለሙያዎች ፈቃድ ለመስጠት የሰነድ ማጣራት ሲደረግ 71 ሀሰተኛ መረጃ መገኘታቸውን በዚህም የተለያዩ አስተዳደራዊ ርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን አንዱ ግን በሕግ የተያዘ መሆኑን አቶ አስመላሽ ደርጋሶ አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ ከ 12 ባለድርሻ አካላት ጋር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ስላከናወናቸው የቅንጅት ሥራዎች አፈጻጸሞች የባለሥልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ድጋፍና ክትትል ምዘና ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ጣዕመ ሰነድ አቅርበዋል። በዚህም በቅንጅታዊ ሥራ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፤ የተለያዩ መመዘኛዎች በመስጠት ለሰባት ተቋማት በጣም ከፍተኛ እንዲሁም ለአምስት ተቋማት ከፍተኛ የአፈጻጸም ደረጃ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረቡ ሰነዶችን መሠረት በማድረግ ሃሳብና አስተያየት እንዲሁም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችም ምላሽ ሰጥተዋል። እንዲሁም የቀረቡ ሃሳቦችና አስተያየቶችን በመቀበል በቀጣይ ለሚሠሩ ተግባራት እንደግብዓት እንደሚጠቀሙበት ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You