
- 3ሺህ 694 ተቋማት በትምህርት ቤት ዙሪያ አዋኪ ድርጊቶችን በመፈጸም ርምጃ ተወሰደባቸው
አዲስ አበባ፡- ባለፉት 9 ወራት 9ሺህ 843 ግለሰቦች በሕገ-ወጥ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ ጉድለት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ 3ሺህ 694 ተቋማት በትምህርት ቤት ዙሪያ አዋኪ ድርጊቶችን በመፈጸም ርምጃ እንደተወሰደባቸው ተመልክቷል፡፡
በባለሥልጣኑ የስታንዳርዳይዜሽን አገልግሎት አሰጣጥ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ቀጸላ ባቀረቡት የ9 ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማ ሲካሄድ እንዳስታወቁት፤ 9ሺህ 843 ግለሰቦች በሕገ-ወጥ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ ጉድለት፣ 3ሺህ 195 ሕገ ወጥ ግንባታዎች በመፈጸማቸው፤ በ34ሺ 260 ሕገ ወጥ የጎዳና ንግድን በሚፈፅሙ አካላት ላይ ተቋሙ ህጋዊ ርምጃ ወስዷል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከ36 ጊዜ በላይ ክትትል በማድረግ የእሁድ ገበያ ላይ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ እንዳይነግዱ በጋራ የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎች ተሠርቷል፡፡ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጪ የበረንዳ ንግድ በሚነግዱ 7ሺህ 394 ደንብ ተላላፊዎች ላይ እና በ104ሺህ 998 ሕገወጥ ማስታወቂያዎች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡
በመንገዶች ማናቸውንም መሰናክሎች የሚያስቀ ምጡና በመንገድ ላይ የግንባታ ግብዓት ተረፈ ምርት የሚጥሉ አካላትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረገው ተግባራት ላይ ከአጋር ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት መቻሉን አመልክተው፤ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን የሚያግዱና የሚያስተጓጉሉ ፈቃድ የሌላቸው ድንኳን፣ ሸራ ቤትና መሰል ጉዳዮችን በጋራ በመለየት የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
የደንብ መተላለፎችን ፈፅመው ቅጣታቸውን በማይከፍሉ ደንብ ተላላፊዎች ላይ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ተጠያቂ በማድረግ ቅጣቱን እጥፍ እንዲከፍሉ በቅንጅት መሠራቱንም ጠቁመዋል፡፡
በኮሪዶር ልማቱ፣ በክፍት ወይም ዝግ የመናፈሻ ቦታዎች፣ የመንገድ አካፋዮች በመሳሰሉት ቦታዎች ዕጽዋት እንዳይረገጡ፣ እንዳይቆረጡ የቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት መቻሉን ጠቁመው፤ አዲስ በወጣው ደንብ ቁጥር 167/2017 ላይ ለ338ሺህ 411 የኅብረተሰብ ክፍሎች በደንቡ ላይ ግንዛቤ እንደተፈጠረም ተናግረዋል፡፡
በትራፊክ መብራቶች አካባቢ በልመና ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን እንዲሁም ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በጋራ በማንሳት ወደ ማገገሚያ ማዕከላት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ ለእድር አደረጃጀቶች በደንብ 150/2015 እና በተሻሻለው 167/2016 መመሪያ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ተሠርቷልም ብለዋል፡፡
በከተማዋ መሬት ባንክ ያልገቡ ክፍት ቦታዎችን ባንክ እንዲገቡ በማድረግ እና መረጃውን በማደራጀት 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ቦታን ለደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በሰነድ ማስረከብ መቻሉን የሚገልጹት አቶ ዳንኤል፤ ቦታውን ጠብቆ በማቆየትም የተሳካለት ሥራ መሥራት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ ባለፉት 9 ወራት ከኢንዱስትሪዎችና ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚመነጭ ዝቃጭ ፣ ተረፈ ምርት ፣ቆሻሻ በአግባቡ የማያስወግዱ ተቋማትን መከታተል ፣ መቆጣጠር እና መከላከል ሥራ ተሠርቷል፡፡ በተቋማት በግለሰቦች ላይ የወንዝ ዳርቻ አካባቢን በማበላሸት 229 ድርጅት እና 179 ግለሰቦች በድምሩ 75 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በቅጣት ተሰብስቧል፡፡
በደንብ ቁጥር 180/2017 ላይ ለ338ሺህ 411 የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ለ508 የፅዳት ሽርክና ማህበራት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቅንጅት መፍጠር መቻሉን ተናግረው፤ በትምህርት ቤት ዙሪያ ከሚፈቀደው ራዲየስ ውጪ አዋኪ ድርጊቶችን በሚፈፅሙ ተቋማት ላይ ቅንጅታዊ ርምጃ በመወሰዱ ለትምህርት ቤቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡ በእዚህም በትምህርት ቤት ዙሪያ አዋኪ ድርጊቶችን በፈጸሙ 3ሺህ 694 ተቋማት ላይ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም