
አዲስ አበባ፡- ጠንካራና የላቀ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ከሳይበር ጥቃት ሊታደገው የሚችልና 24 ሰዓት የማይተኛ ሠራዊት አለው ሲሉ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስታወቁ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የትኛውም ኢትዮጵያን ማጥቃት የሚፈልግ አካል የመጀመሪያ የጥቃት ዒላማውን ማድረግ የሚፈልገው የሀገሪቷ ገንዘብና የመንግሥት ሀብት የሚያንቀሳቅሰውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ይሁንና ጠንካራና የላቀ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሳይበር ጥቃት ሊታደገው የሚችልና 24 ሰዓት የማይተኛ ሠራዊት እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል።
ይህ ሠራዊት የሚሠራው በፈረቃ ሲሆን፤ በሲስተማችን ላይ ከውጭ የሚመጣውን የሳይበር ጥቃት የሚከላከለው በቁርጠኝነት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በየቀኑ ሲስተማችንን ለማውረድ የሚመጡት ጥቃቶች በትንሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የሆነ የፖለቲካ ችግር የተፈጠረ ጊዜ ደግሞ ይህ ቁጥር አምስትና ስድስት እጥፍ ይሆናል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ እኛ የምናስባቸውና ጥቃት ሊሰነዝሩብን ይችላሉ ከሚባሉ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በፍጹም ከማይጠበቁ ሀገራት ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሙከራቸውም 24 ሰዓት በሙሉ እንደሆነ ጠቁመው፤ ይሁንና የተዘረጋው ሲስተም በአግባቡ የሚከላከል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሥርዓቱን አልፎ ጥቃቱ ቢሰነዘር እንኳ የመከላከያ ዘዴው ጥብቅ በመሆኑ ሥርዓቱን ሰብሮ ለመግባት የሚፈልግ የትኛውም አጥቂ አልፎ መሔድ የማይችለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አቤ ገለጻ፤ የሳይበር ደኅንነት በብዙ ባለድርሻዎች ከፍተኛ ክትትል የሚደረግ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክም፤ ባንኮች በቴክኖሎጂው የላቁ እንዲሆኑ እንቅስቃሴ የጀመረው ከዛሬ 16 ዓመታት በፊት ነው፡፡ የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ጀምሮ የፋይናንስ ደኅንነቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራ የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከኢንሳ፣ ከብሔራዊ ባንክና ከባንኮች ጋር የባንኮችን ደኅንነት ለመጠበቅ በጋራ እየተሠራ ነው፡፡
ባንኮች ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁ በራሳቸው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በተቆጣጣሪ አካልም ጭምር ቁጥጥር የሚደረግበት መሆኑን አመልክተው፤ ብሔራዊ ባንክም በራሱ መስፈርት ባንኮች ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲጠብቁ በየጊዜው ክትትል ያደርጋል፡፡ ኢንሳ ደግሞ የሀገራችን የሴኪዩሪቲ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ክትትል ያደርጋል፡፡ ሁሉም ባንኮች በተቻላቸው አቅም የሌላ የውጭ አካል ገብቶ ሲስተማቸውን በርብሮ የፈለገውን እንዳያደርግ ተገቢ የሆኑ የመከላከያ ሥርዓቶች እንዲኖራቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳይበር ደኅንነቱ ላይ ኢንቨስት ያደረገው ከአስር ዓመት በፊት መሆኑን አውስተው፤ ኢንቨስት ያደረገውም በጣም ጠንካራ ቴክኖሎጂን ነው ብለዋል፡፡
አሁን ሁሉም የተደራጀ የሴኪዩሪቲ ሥርዓት አለው፡፡ አንዱ ሌላውን ያግዛል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴኪዩሪቲ ማዕከሉ ላይ ችግር ካየ ፈጥኖ ለሁሉም ያሳወቃል፡፡ ችግሩን የሚከላከለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሳይሆን ኢትዮ ቴሌኮምም ኢንሳም በጋራ በመሆን እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
አቶ አቤ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ማንም የእኛን ሲስተም ሰብሮ የገባ የለም፡፡ መከላከያ ሥርዓት ከተደረገ መከላከል እንደሚቻል በተግባር ያየንበት ነው፡፡ ይህ የመከላከል ሥርዓቱ አንዴ ተደርጎ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፤ በየቀኑ ዘመኑ የፈበረካቸው አዳዲስ እውቀትን መሠረት በማድረግ የሚካሄድ ነው፡፡ ችግሩን ለመከላከል በሰው ብቻ ሳይሆን በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመጣ ጥቃትን ጭምር መቋቋም የሚችል ከእዚያ በላይ የጠነከረ ሥርዓት ማድረግን ይጠይቃልና በእዚህ ረገድ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የሳይበር ሴኩሪቲ መከላከያ የባንካችን ትልቁ ኢንቨስት የሚደረግበት ሥርዓት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አንዳንዴ የውስጥ ሠራተኛ በስሕተትም ከውጭው ጋር ተባብሮ ችግር ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ የምንከተለው ፖሊሲ ዜሮ ትረስት ነው፡፡ በእዚህ ጉዳይ አቶ አቤም አይታመንም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ40 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም