በእስራኤል ቴል አቪቭ እና እየሩሳሌም አቅራቢያ ሰደድ እሳት ተከሰተ

በእስራኤል ቴል አቪቭ እና እየሩሳሌም አቅራቢያ በትናንትናው ዕለት ሰደድ እሳት መከሰቱን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል። የእስራኤል የእሳት አደጋ ባለሥልጣን ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፤ በሰደድ እሳቱ 13 ሰዎች ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 10 የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

በከባድ ሙቀት እና አውሎ ንፋስ ምክንያት እንደተነሳ የተገመተውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር፤ የእሳት አደጋ መከላከያ አውሮፕላን እና በርካታ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በማሰማራት የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር እየተሠራ እንደሆነም የታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ ያመለክታል።

ሰደድ እሳቱ በመጀመሪያ በእስራኤል ሞሻቭ ታኦዝ አካባቢ የተከሰተ ሲሆን፤ በተደረገው እሳቱን የመቆጣጠር ሥራ አመሻሽ ላይ በሰደድ እሳቱ ሳቢያ ተዘግተው የነበሩ አንዳንድ መንገዶች መከፈታቸውም ተገልጿል። ሰደድ እሳቱ በከተሞቹ አቅራቢያ የሚገኙ የደን ስፍራዎችን በከፊል ያወደመና አስፈሪ እንደሆነ ክስተቱን የተመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ሰደድ እሳቱን ለማጥፋትም በአየርና በምድር ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You