
የቀደመው ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት የወደቀው ሥርዓቱ ሕዝቡን ሆኖ የመገኘት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል አቅም ማጣቱ ነው። ከሁሉም በላይ ሀገር እንደሀገር በሁለንተናዊ መልኩ ከትናንት ወደ ዛሬ ማሻገር የሚያስችል ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መነቃቃት መፍጠር አለመቻሉ ነው።
ከእዚህ ይልቅ ራስ ወዳድነት ፣ ዳተኝነት ፣ ዘረፋ እና አጋባሽነት የፖለቲካ ሥርዓቱ ዋንኛ መገለጫዎች ነበሩ። ሕዝብን እንደ ሕዝብ የመፈረጅ ፣ በሕዝቦች መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬን መዝራት ፣ ሀገርን የትናንት ባሪያ በማድረግ ከእዚህ የፖለቲካ ትርፍ ማስላት የሥርዓቱ ሌላኛው መገለጫ ነበር።
በልማት ስም የተካሄዱ የተለያዩ ወንጀሎች ዜጎችን ወደ ከፋ ድህነት ከመውሰድ ባለፈ ሕዝባችንን አሁን ድረስ ዋጋ እያስከፈለው ላለው የውጪ እዳ ዳርገውታል። ከሚታዩ ልማቶች በስተጀርባ የተፈጸሙ ውንብድናዎች የጥቂቶችን ካዝና ከመሙላት ባለፈ ፣ ለዛሬ የሰላም እጦት ተጨማሪ ምክንያት ስለመሆናቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው።
ሀገሪቱ እንደሀገር ለልማት ሥራዎች በሚል የወሰደቻቸው ዓለም አቀፍ ኮሜርሻል ብድሮች፣ ለታለመላቸው ዓላማ ባለመዋላቸው ፣ የልማት ሥራዎቹ ለአየር ባየር ደላሎች የደለበ የገቢ ምንጭ ሆነዋል። የተጠበቀውን አገልግሎት መስጠት ሳይችሉ ቀርተው፤ዛሬም የሀገር እና የሕዝብ ሸክም እንደሆኑ ነው።
በቀደመው ሥርዓት በተለይም በከተማ ልማት ስም ብዙ ዜጎች በግፍ ከእርሻቸው / ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለድህነት እና ለጠባቂነት ተዳርገዋል። ብዛት ያላቸው የግንባታ መሠረተ ድንጋዮች በደመቁ ሥነ- ሥርዓቶች ተጥለው ፣ እስከ በጀታቸው ሳይጀመሩ ታሪክ የሆኑ ፣ ተጀምረውም የመጠናቀቂያ ጊዜያቸው እንደናፈቃቸው እስከዛሬ የዘለቁ ጥቂት አይደሉም።
በቀደሙ ሥርዓተ መንግሥቶች በተለይም እንደ ሀገር ለከተሞች ልማት ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ዜጎች ለኑሮ በማያመቹ በፈራረሱ እና በመፈራረስ ላይ ባሉ፣ በተገቢው ቋንቋ ቤት ተብለው ሊገለጹ በማይችሉ ቤቶች ውስጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንዲኖሩ የተገደዱባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና ፣ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከተማ ከመሆኑዋ ጋር በተያያዘ ስሟን እና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን በሚመጥን መንገድ የከተማ ልማት ማካሄድ ሳትችል ዓመታትን አስቆጥራለች። ይህም ሁለንተናዊ በሆነው የከተሞች መመዘኛ ኋላቀር ከሚባሉ ከተሞች መካከል ተጠቃሽ አድርጓታል።
በከተማዋ መሀል አካባቢዎች የተገነቡ አብዛኞቹ ቤቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት በንጉሱ ዘመነ መንሥስት የተገነቡ ፣ በደርግ የከተማና ትርፍ ቤት አዋጅ የተወረሱ ናቸው ። ግንባታቸውም ቢሆን ገና ከጅምሩ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ እና የዘመኑን የከተማ ልማት እሳቤ በአግባቡ ያላሟላ ነበር።
እነዚህ ቤቶች አንድም በአግባቡ በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው አካል አለመኖሩ ፣ከእዛም ባለፈ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ቆርቆሯቸው እንኳን እንዳይቀየር ከተጣለው የሕግ ክልከላ አኳያ እርጅናቸው በራሱ አደባባይ ወጥቶ የሚያሳጣ ፣ ዜጎችንም በብዙ አንገት የሚያስደፋ ነበር።
ይህንን እውነታ ለመቀየር መንግሥት ላለፉት ስድስት ዓመታት ሰፊ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ በማድረግ ለውጥ እና የመለወጥ ተምሳሌት እንድትሆን ረጅም መንገድ ተጉዟል። በእዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ስኬት እያስመዘገበ ነው።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሪደር ልማት ፣ በከተማ ማደስ፣ በወንዝ ዳር እና አጠቃላይ በሆነው የከተማ ልማት በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደሀገር በቂ ትኩረት ላልተሰጠው የከተማ ልማት ትንሳኤ እየሆነ ነው። ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ ከመሆን ባለፈ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች በማሟላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን እድል እያሰፋ ነው።
በተለይም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ከተማ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ አሁን በከተማዋ እየተካሄደ ያለው ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ የከተማ ልማት የመዲናዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን በማሳደግ የሚኖረው ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ ነው።
ለእዚህም ትናንት በይፋ የተመረቀው የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እንደ ተጨማሪ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ልማቱ ለአረንጓዴ፣ ንፁህ እና ዘመናዊ የከተማ ማዕከላት ያለንን መሻት በተጨባጭ ማሳየት የሚያስችል ነው። በእዚህ ደረጃ የሚከወኑ የለውጥ ሥራዎች ፣ በብዙ ተግዳሮቶች የታጀቡ ናቸው። በልማቶቹ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችም ተለውጦ የመለወጥ የትውልዱ ፍላጎት ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም