የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ!

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የታለበሱ ሕዝቦች ናቸው። በርሃብም ሆነ በድርቅ፣በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅቶች በመደጋገፍ እና በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን በማሳለፍ ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያውያን ዘር ፣ ቀለምና ፣ሃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፣የተራበን ማብላት፣የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በራሳቸው ይቅርና ባሕር አቋርጦ፣ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው ፣ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው።

ይህ የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ቤት ማደስ በእዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።

ሰሞኑን በፋሲካ በዓል እንደተደረገው ሁሉ የበዓላት ወቅቶች ሲመጡ በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ በማድረግ አቅመ ደካሞች በዓላትን ተደስተው እንዲያሳልፉ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን እሴቶች ማስቀጠያዎች ለመሆን በቅተዋል። በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው።

ለወትሮ በማጣት ምክንያት በበዓላት ወቅት ቤታቸውን ከርችመው የሚውሉ ዜጎች ዛሬ በማዕድ ማጋራት በዓላትን በደስታ ማሳለፍ ችለዋል። በበዓላት የሃዘን ድባብ የሚያጠቃቸው ቤቶች ዛሬ በደስታ ተለውጠዋል። በእነዚህ ዜጎች ዘንድ በዓላት የፈገግታ ምንጭ ሆነዋል። ማዕድ ማጋራት ተሳስቦ የመኖር ኢትዮጵያዊነትን ያጠናከረ እና የእኛነታችን አንዱ መገለጫ እየሆነ ያለ ተግባር ነው።

አቅመ ደካሞችን ከመመገብ ጋር በተያያዘ ሌላው ሳይነሳ የማይታለፈው የምገባ ማዕከላት ጉዳይ ነው። አቅመ ደካሞች ለሆኑና በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለሚፈልጉ ሁሉ በራቸውን ክፍት አድርገው የሚጠብቁ 20 የምገባ ማዕከላት ተከፍተው በቀን ከ35 ሺ በላይ አቅመ ደካሞችን እያገለገሉ ነው።

ከእዚሁ ጎን ለጎንም በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛው ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው።

ለውጡ እውን ከሆነበት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከታዩ በጎ ተግባራት ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የሚደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው። በእዚህ ፕሮግራም ውስጥ በተለይም አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ ሊፈርሱ የደረሱ ደሳሳ ጉጆዎች ቀና እንዲሉ ተደርገዋል። በእዚህም የበርካታ አቅመ ደካሞች እንባ ታብሷል።

መንግሥት በሚከተለው ዜጋ ተኮር ፖሊሲ ምክንያት ዜጎች የተሻለ መጠለያ እንዲያገኙ በተያዘው ዕቅድ በየዓመቱ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የአቅመ ደካማ ቤቶች እየታደሱ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ዜጎች በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ ከማስቻሉም በላይ የከተማዋን ገጽታ ከስር መሠረቱ እየቀየረው ይገኛል። አሁን አሁን ደግሞ በክረምት ብቻ የነበረው ቤት ማደስ ክረምትን ተሻግሮ በበጋም መተግበር ጀምሯል። በእዚህም ምክንያት የበጎ ፈቃድ ሥራው ዓመቱን ሙሉ እየተተገበረ ይገኛል።

በእዚህ በጎ ተግባር ውስጥም መንግሥት የራሱን ሀብት ፈሰስ ከማድረጉም ባሻገር ባለሀብቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል። ሰሞኑንም የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ይኸው በጎ ተግባር ጎልቶ ታይቷል።

የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት በቦሌ ክፍለ ከተማ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነባ ባለ 4 ወለል ሕንፃ ለ446 አቅመ ደካሞችና የልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤት ቁልፍ የተረከቡ ሲሆን፤ ከለውጡ ወዲህም ከ39 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል። ይህን መሰል በጎ ተግባራት የአቅመ ደካሞችን ሸክም ከማቅለሉም ባሻገር እንደ ሀገርም የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህልን ለማዳበር ስለሚጠቅሙ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You