
አዲስ አበባ፦ ሰሞነኛው የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ጭማሪ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የተከሰተ ጊዜያዊና በቅርቡም ሊፈታ የሚችል እንደሆነ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ገለጹ።
አቶ ሻፊ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በቅርቡ በሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ላይ እየታየ ያለው ጭማሪ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የመጣ ነው ብለዋል። አንደኛውና ዋናው ምክንያት በዓለም ገበያ በነበረው ከፍተኛ የቡና ፍላጎት ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት ለዓለም ገበያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ማቅረቧ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ምክንያት ወቅቱ አዲስ የቡና ምርት የገባበትና ለዓለም ገበያ እየተዘጋጀ ያለበት በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ አዲሱ ምርት ተዘጋጅቶ ደረጃ እስኪወጣለት ድረስ ጊዜ የሚፈልግ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ቡና በተለምዶ ደረጃው ዝቅ ይበል እንጂ ጥሩ ቡና ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ዝቅተኛ የተባለውም ሌላ ስም ስለታጣላት እንደሆነ አመላክተዋል። በአሁኑ ወቅትም ይኸው ዝቅተኛ የተባለውና ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውለው ቡና በዝግጅት ላይ እንደሚገኝና ወደ ገበያ ያልወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች በተጨማሪ የዓለም የገበያ ፍላጎትና ዋጋም በሀገር ውስጥ ገበያው ላይ ጫና ማሳደሩን ያልሸሸጉት አቶ ሻፊ፤ ጭማሪው ጊዜያዊና በቅርቡ ሊፈታ የሚችል ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት አዲሱ የቡና ምርት ተዘጋጅቶ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ አስፈላጊው የዝግጅት ሥራ እየተሠራ ያለበት ወቅት ነው። የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቅቆ ቡናው ለውጭ ገበያ ሲዘጋጅ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውለው ዝቅተኛ የተባለው ቡና ወደ ገበያ ይወጣል። በእዚህ ጊዜ የቡና ዋጋ ወደ ቦታው የሚመለስ ይሆናል ብለዋል።
ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውለው ቡና ለውጭ ገበያ ተዘጋጅቶ ካለቀ በኋላ የሚቀርብ በመሆኑ በደረጃው ዝቅተኛ ምርት ይባል እንጂ የተሻለና ጥራት ያለው ቡና መሆኑን አቶ ሻፊ ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ቡና ገዢ ሀገራት ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ወይም ተረፈ ምርቱን ጭምር የመግዛት ፍላጎት እያሳዩ ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅ፣ ተፈላጊና ተወዳዳሪ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ያለውን ተቀባይነት ማስቀጠል እንደሚገባ ያነሱት አቶ ሻፊ፤ በተለይም ዓለም አቀፍ ገበያው በሚፈልገው መንገድ ቡናን ማዘጋጀት የግድ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ቡናን በብዛትና በጥራት በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያለውን የቡና ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
ለእዚህም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና የምርት ጥራትን ማስጠበቅ አንደኛው ትኩረት ተሰጥቶት የተሠራ ሥራ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ የግብይት ዘርፉን ማዘመንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዋልታ ከሆነው ቡና ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት እንደምትችል አመልክተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም