
ዜና ትንታኔ
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ጥቅሟን የሚጎዳ የንግድ ድርድር የሚያደርጉ ሀገራትን አስጠንቅቃለች። የሀገሪቱ መንግሥት ማስጠንቀቂያውን የሰጠው በርካታ ሀገራት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጣሉባቸው የታሪፍ ጭማሪ እንዲስተካከልላቸው ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ንግግር መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ “መለማመጥና ማባበል ሰላምን ሊያመጣ አይችልም። ከታሪፍ ጫና ነፃ ለመሆን ሲባል የሚደረግ ራስ ወዳድና የሌላውን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር፣ ለሁሉም ወገኖች ውድቀትን ያስከትላል” ብሏል።
ቻይና ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ ጉዳይ የመፍታት ነፃነታቸውን እንደምታከብር ገልጻ፤ የቻይናን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራትን የሚፈፅሙ ሁሉንም አካላትን ግን በጥብቅ እንደምትቃወም በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል። ከእዚህ በተጨማሪም ቻይና ጥቅሟን ለሚጎዱ ርምጃዎች ሁሉ የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥም አስጠንቅቃለች።
“ብሉምበርግ ኒውስ” (Bloomberg News) ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው ዘገባ፤ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ሀገራት የታሪፍ ጫናው እንዲቀልላቸው ከቻይና ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲቀንሱ ጫና እያደረገ እንደሆነ ጠቁሟል። የአሜሪካ ባለሥልጣናት የፕሬዚዳንት ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ጫና የፈጠረባቸው ሀገራት ከቻይና የሚያስገቡትን ምርት እንዲቀንሱና ከሀገሪቱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካላቸው ሀገራት በሚገዟቸው ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታሪፍ እንዲጥሉ ሀገራቱን ለማግባባት እቅድ እንዳላቸው “ብሉምበርግ” ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች እንደሰማ ገልጿል።
በርካታ ሀገራት ስለታሪፍ ጭማሪው ውሳኔ ለመደራደርና ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየጣሩ እንደሚገኝ ተገልጿል። የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት ከ70 በላይ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ጥያቄ እንዳቀረቡ ተናግረዋል። ለአብነት ያህልም የጃፓን ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አቅንተው ስለታሪፉ ጉዳይ ውይይት ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ደቡብ ኮሪያም ተመሳሳይ ውይይት ለመጀመር በእዚህ ሳምንት ተወካዮቿን ወደ አሜሪካ እንደምትልክ ታውቋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሳምንታት በፊት ይፋ ያደረጉትና መላውን ዓለም ያስገረመው የታሪፍ ጭማሪ ከበርካታ ሀገራት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። በአንዳንድ ሀገራት ላይ የተጣለው የታሪፍ ጭማሪ ከፍተኛ የሚባል ነው። ፕሬዚዳንቱ ይህ ውሳኔያቸው በብዙ ሀገራት ላይ እንዳይተገበር ለ90 ቀናት ያራዘሙት ቢሆንም ከቻይና ጋር የገቡበትን ውዝግብ ግን አፋፍመውታል። ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ የ145 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን፤ ቻይና በበኩሏ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ125 በመቶ ታሪፍ ጥላለች።
ሁለቱ የዓለም ባለግዙፍ ምጣኔ ባለቤቶች እንዲህ ያለ የንግድ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል። ፍጥጫቸውም የመቀዛቀዝ ምልክት የሚያሳይ አይመስልም። ቻይና ለአሜሪካ ከፍተኛ ምርት በመላክ በቀዳሚነት ተቀምጣለች። የአሜሪካ ገበያ ለቻይና ምርት ትልቅ ስፍራ አለው።
በፒተርሰን ኢንስቲትዩት የአሜሪካ- ቻይና የንግድ ጉዳዮች ጥናት ባለሙያ ሜሪ ላቭሊ እንደሚያስረዱት፤ ቻይና የወጪ ንግዷ የሚያሽቆለቁል ከሆነ ወሳኝ የሆነው የገቢ ምንጯ መጎዳቱ የማይቀር ነው። ለቻይና ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ መመንደግ የወጪ ንግዷ ለረጅም ጊዜ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ሀገሪቱ ምንም እንኳ የቴክኖሎጂ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍንና የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመጨመር የገቢ አቅሟን ለማስፋፋት እየሞከረች ቢሆንም፣ የወጪ ንግዷ አሁንም መሠረታዊ የገቢ ምንጯ ነው።
ስለሆነም ቻይና አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን መፈለጓ የሚጠበቅ ርምጃ ነው። ለእዚህም ሳይሆን አይቀርም የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ባለፈው ሳምት በሦስት የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት (ቬትናም፣ ፊሊፒንስና ካምቦዲያ) ጉብኝት ያደረጉት። የፕሬዚዳንት ሺ የደቡብ ምስራቅ እስያ ጉብኝት ቻይና በቀጣናው ያላትን የበላይነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ውሳኔን ተከትሎ ለወጪ ምርቶቿ አማራጭ የገበያ መዳረሻና ዘላቂ የንግድ አጋሮችን ለመፈለግ የምታደርገው እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ ተወስዷል።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ የ438 ቢሊዮን ዶላር ምርት ከቻይና ያስገባች ሲሆን፣ ቻይና ደግሞ 143 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአሜሪካ ሸምታለች። በእዚህም አሜሪካ ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ የ295 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ገጥሟታል። አሜሪካ ከቻይና የምታስገባቸውን ምርቶች በአጭር ጊዜ ከየትኞቹ ሀገራት በሚገኙ ምርቶች እንደምትተካቸው ግልጽ አይደለም።
የሁለቱ ኃያላን ፍጥጫ ሀገራቱ እርስ በርሳቸው ከሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባሻገር፣ በሌሎች ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። አዲሱ የቻይና ማስጠንቀቂያም ይህ እንደሚሆን ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከቻይናና ከአሜሪካ ጋር የንግድ ትስስር ያላቸው ሌሎች የዓለም ሀገራት በሁለቱ ኃያላን ጥቅምና ፍላጎት መካከል ላይ ለመቆምና አስቸጋሪ ምርጫን ለመምረጥ ሊገደዱ እንደሚችሉ እየተገለጸ ይገኛል።
አሜሪካ በሀገራቱ ላይ የጣለችውን የታሪፍ ጭማሪ ለማላላት ሀገራቱ ከቻይና ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲቀንሱ ስታስገድድ፤ ቻይና ደግሞ ይህ ድርጊት ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ በመሆኑ በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ከአሜሪካ ጋር የሚቆምሩ ሀገራትን ለመቅጣት የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዷ አይቀርም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በርካታ የዓለም ሀገራትን አጣብቂኝ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።
“መዝገበ ቃላት ውስጥ ካሉ ቃላት መካከል በጣም የምወደውና ደስ የሚያሰኘኝ ‹ታሪፍ (Tariff) የሚለው ቃል ነው” ብለው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ የታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካን አምራች ኢንዱስትሪ ለመጠበቅና ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል ብለው ያምናሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ግን፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው ይፋ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ለዋጋ ንረት፣ ለምጣኔ ሀብት መዳከምና ለዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት ያስከትላሉ። የታሪፍ ጭማሪው ለአሜሪካውያን ሸማቾች የምርቶች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል፤ በሌሎች ሀገራትም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይፈጥራል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም