እንስቶች በማይደፍሩት ዘርፍ የነገሠችው -ንግሥት

ዜና ሀተታ

ወይዘሮ ንግሥት ተስፋዬ ትባላለች። አሰላ በሚገኘው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ ናት።ዲፕሎማዋን ለመማር ስትወዳደር በጄኔራል ሜታል ፋብሪኬሽን’ ትምህርት ክፍል ተመደበች። በስልጠና ሂደት ሙያውን ስለወደደችው ትምህርቷን ቀጥላ ከኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪዋን ማግኘቷን ትገልጻለች።

ይህም ብዙዎች በተለይም ሴቶች የማይደፍሩትን የብየዳ ሙያ እንድትጠበብበት፣ ለተማሪዎቿም ክህሎት እንንድታስጨብጥ እድል ፈጥሮልኛል ትላለች። በዚህም አላበቃም፤ ከሚያዚያ 6 እስከ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ብየዳ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ተወዳድራ ሁለተኛ በመውጣት ሀገሯን አኩርታለች።

በሀገራችን ለሙያተኞች በሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት ምክንያት ብዙ ተግዳሮት እንዳጋጠማት የምታስታውሰው ወይዘሮ ንግሥት፤ የእሷ ሙያውን መውደድ የእናቷም ድጋፍ ጫናዎችን ተቋቁማ በዘርፉ ላይ ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን እንዳስቻላት ትጠቅሳለች።

የብየዳ ሙያ ከቤታችን በርና መስኮት እስከ አቬሽንና ጠፈር ድረስ ጥቅም ላይ የሚውል፣ ከፍ ያለ ጥበብን የሚጠይቅ ሳይንስ ነው የምትለው ሙያተኛዋ፤ ለሙያው ባለው የተሳሳተ አመለካከት እና ጉልበትንም የሚጠይቅ መሆኑ ብዙ ሴቶች አይደፍሩትም ነው ያለችው።

ሴቶች የተለየ ጥበብ ያለና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም የመፍትሔ ሀሳብ ማምጣት የሚያስችል ተፈጥሮ ስላለን የትኛውም ሙያ ላይ ብንሰማራ ውጤታማ መሆን እንችላለን ትላለች።ወደፊት በዘርፉ የግሌን ሥራ መሥራት፣ ከሀገር ውጭ ወጥቶ ተጨማሪ ክህሎት ለመጨበጥና ውድድር ላይም ለመሳትፍ ህልም እንዳላት የምትገልጸው ወይዘሮ ንግሥት፤ ኢትዮጵያ ካለችበት የእድገት ሁኔታና ካሉ ዓለም አቀፍ እድሎች አንጻር ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ስትል ትገልጻለች።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የምስክር ወረቀት እየሰጠች ነው።በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን የብየዳ ስልጠና ወስደው ሀገራቸውን በመገንባት ሂደት እንዲሳተፉ ብሎም እየተፈጠሩ ያሉ ዓለም አቀፍ እድሎችን ተጠቅመው እንዲሠሩ ምክሯን ለግሳለች።

በሀገራችን የሚስተዋለው የሙያተኞችን የእጅ ሥራ ውጤት እየተጠቀሙ ሙያተኞችን ዝቅ አድርጎ ማየትና ያልሆነ ስያሜ መስጠትም ሊታረም እንደሚገባ መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You