
ጊኒር– የምሥራቅ ባሌ ዞን ከ42 ሺህ ሔክታር በላይ መሬትን በበጋ ስንዴን በመስኖ የለማ ምርት ተሰብስቦ እየተጠናቀቀ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ እስማኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን ስንዴ አምራች እንደሆነ ይታወቃል፤ በተለየ ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ኢንሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ የዞኑ የስንዴ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልፀዋል።
ምስራቅ ባሌ ዞን በስንዴ ምርት የሚታወቅ አካባቢ መሆኑንና የበጋ መስኖ ስንዴ ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ በተለየ በስንዴ የሚሸፈነውን ማሳ በሔክታር በማሳደግ እና መስኖን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ፤ ዞኑ ለኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርት ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ለምታደርገው የስንዴ ኤስፖርትም ትልቅ አበርክቶ ካላቸው አምራች አካባቢዎች አንዱ ነው።
‹‹ምሥራቅ ባሌ ዞን በልማት በኩል የልማት አርበኛ ተብሎ የሚጠራ ዞን ነው›› የሚሉት አቶ መሐመድ ፤‹‹ስንዴም በኩታ ገጠም የሚለማበት እና በዓመት ሦስት ጊዜ የሚመረትበት አካባቢ ነው›› እንደሆነ ገልጸዋል።
ምንም እንኳን ሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ስንዴ አምራች መሆናቸውን የሚገልፁት ምክትል አስተዳዳሪው፤ በተለየ ግን የዞኑ ሁለት ወረዳዎች ስንዴ በስፋት የሚመረትበት አካባቢዎች ናቸው። ዞኑ ባለፉት ዓመታት ስንዴ ምርት ለኤክስፖርትም ሲደረግ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ዞኑ ቆላማና ውሃ አጠር አካባቢ ስለሆነ የመስኖ ልማት ወደ ኋላ የቀረ ነበር የሚሉት አቶ መሐመድ፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ኢንሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ ግን ያለውን የውሃ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የመስኖ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
አሁን ላይ ውሃ ያለበት የዞኑ አካባቢ በተለያየ ዘዴ፣ ማለትም በፓምፕ፣ በባህላዊ የመስኖ ዘዴ እና በአነስተኛ የመስኖ ልማትን በመጠቀም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ነው የሚሉት አቶ መሐመድ። የበጋ መስኖ ስንዴ ኢንሼቲቭ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከዓመት ወደ ዓመት በመስኖ ስንዴ የሚሸፈነው ማሳ ብዛት እና ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ እንደመጣ ነው የገለጹት።
እንደ ኃላፊው አገላለጸ፤ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም ዞኑ ከ42 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ መሸፈን ተችሏል።ይህ በበጋ ስንዴ የተሸፈነው ሰብል አሁን ላይ ምርቱ ተስበስቦ ወደ መጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት የተጀመረው ታሕሳስ ወር ጀምሮ መሆኑን የገለፁት አቶ መሐመድ፤ በፓምፕ፣ በአነስተኛ መስኖ እና በባህላዊ የመስኖ ዘዴ በመጠቀም 42 ሺህ ሔክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን አውስተዋል።
ምርታማነቱም ከዓመት ወደ ዓመት እድገት እያሳየ መሆኑን እና ዘንድሮም በአማካይ ከሔክታር 35 ኩንታል ምርት የተገኘ መሆኑንና ምርቱም በጥሩ ሁኔታ ተስብሶ እያተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀዋል።
ምሥራቅ ባሌ ዞን በክረምት፣ በበልግ እና በበጋ መስኖ ልማት በዓመት ከ300 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በስንዴ እንደሚለማ የነገሩን ምክትል ዋና አስተዳዳሪው፤ ለመጪው የመኸር ምርት ወቅትም ከ190 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በስንዴ ለመሸፈን ዝግጅት ተጀምሯል። ለ2017/18 የመኸር ወቅት ዝግጅት ከዚህ ወር ጀምሮ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ መገባቱን አቶ መሐመድ አመልክተዋል።
ዳርጌ ካሕሳይ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም