
አዲስ አበባ፡- ሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ንጉስ ልጅ እያሱ ታስረውበት የነበረው ታሪካዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።
የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ባሕልና ቅርስ ጥበቃ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኢብራህም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በምሥራቅ ሐረርጌ ጉራዋ ወረዳ የሚገኘው ንጉስ ልጅ እያሱ ታስረውበት የነበረው ታሪካዊው ቤተ መንግሥት ዕድሳት ሳይደረግለት ረጅም ዓመታት በመቆየቱ አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል። የእዚህ ታሪካዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሊጀመር ነው ብለዋል።
ይህ ታሪካዊው እስር ቤት 5 ሺህ ካሬ መሬት ላይ ያረፈ እንደሆነ ገልጸው፤ የ93 ዓመት ገደማ እድሜ ያስቆጠረና በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተገነባ እንደሆነ ተናግረዋል።
ግንባታውም በ1923 ተጀምሮ 1925 ዓ.ም የተጠናቀቀ መሆኑን አውስተው፤ መስከረም 5 ቀን 1925 ዓ.ም በቀዳማዊ ንጉስ ኃይለስላሴ ተመርቆ የማረሚያ ቤቱ አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ተናግረዋል።
የሕንፃው ግንባታ ዘመናዊነትን የተላበሰ ሲሆን፤ ዲዛይኑ በአርማናዊት ዜጋ አማሊያ እንደተዘጋጀ ታሪኩን ዋቢ አድርገው ኃላፊዋ ገልጸዋል።
ንጉስ ልጅ እያሱ ከ1913-1916 ኢትዮጵያን ስያስተዳድሩ ከቆዩ በኋላ በሀገር ውስጥ ባንዳና በውጭ ጫና ሥልጣናቸውን ተነጥቀው ጉራዋ በሚገኘው እስር ቤት ሲሰቃዩ እንደነበር ታሪክ ያትታል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ንጉስ ልጅ ኢያሱ ሥልጣናቸውን ተነጥቀው በአዲስ አበባ ፣ በፊቼና ታርካዊው ምሥራቅ ሐራርጌ ጉራዋ በሚገኘው በእዚሁ እስር ቤት ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ 1928 ማታ ከእስር ቤቱ አስወጥተዋቸው በ40 ዓመት እድሜአቸው መገደላቸውና እስካሁን የተቀበሩበት ቦታ የማይታወቅና ጥናት እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ ሰዓዳ ገልጸዋል።
በእስር ቤቱ ባሳለፉት ቆይታ እግራቸው ታስሮበት የነበረ 100 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሰንሰለትና ከብረት የተሠራ መቀመጫቸው አሁን ድረስ በቦታው ይገኛል ያሉት ኃላፊዋ፤ ሲጠበቁበት የነበረ ጠብመንጃና የቤቱ ቁሳቁሶች ተዘርፈው በግለሰቦች እጅ እንደገቡና ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕንፃው ተጠግኖ የገቢ ምንጭ መሆን ሲገባው ዕድሳትና ጥበቃ ስላልተደረገለት አደጋ ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።
በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ቋሚ የሥነ ጥበብና የኪነ ሕንፃ ቅርስ ጥገና ባለሙያ አቶ ገብረማርያም አናኒያ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጡን ማብራሪያ፤ ታሪካዊ ቅርሱን የሚመለከታቸው ኮሚቴዎችን በማዋቀር የጉዳት ደረጃውን ተመልክተው ለእድሳት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በእዚሁ መሠረት ዕድሳቱን ለማድረግ ዝግጅት መጠናቁን የገለጹት ባለሙያው፤ ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ዝግጅቶቹ ተጠናቀው ወደ ዕድሳት ሥራው ይገባል ብለዋል።
የእድሳቱን በጀት በባለሥልጣኑ የሚሸፈን መሆኑን ገልጸው፤ ዕድሳቱም ስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።
በጨረታ ሂደት ላይ ስለሆነ በጀቱን መግለፅ ይከብዳል ያሉት አቶ ገብረማርያም፤ እድሳቱ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሙያዊ ጥገና ይደረግለታል ብለዋል።
እድሳቱ ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት እስኪሆን ድረስም በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች አደጋ እንዳይደርስበት ከዞኑ ጋር በመሆን ክትትልና ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑንም ተናግረዋል።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ገፀ በረከት ያጌጠችው ምሥራቅ ሐረርጌ የሐሮማያ ሀይቅ፣ የባቢሌ ዝሆን፤ ትክል ድንጋይ፣ የቁንድዶ ፈረስ የሚገኙበት ዞን ነው።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ ያጌጠችው ቱሪዝም ዘርፍ ጥበቃና ገቢ ጋር በተያያዘ ብዙ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎች እንዳሏት ነው ዞኑ የሚገልጸው። የዞኑ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቱሪስት መስህቦች ጥበቃ ጋር በተያያዘ ሐሮማያ ሀይቅን ወደ ነበረበት በመመለስ በቁንድዶ ፈረስና ባቢሌ ዝሆን መጠለያን ማመቻቸት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ እንደቆየ ነው የተገለጸው።መጠለያዎቹን ከማመቻቸት ጋር ተያይዞ በተሠራው ሥራ ሐሮማያ ሀይቅ በመጠንና ጥልቀት እየገዘፈ የቁንድዶ ፈረሶችም ሆነ የባቢሌ ዝሆን ቁጥር በመጨመር ላይ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
ዋሲሁን ተክሌ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም