ጥንት ኢትዮጵያውያን ያለ ሕግ የኖሩበት ወቅት አልነበረም ማለት ይቻላል። ዛሬ ሕጎቻቸው ዳብረው፣ ፍትሕ ሰፍኖባቸው፣ መብታቸው ተከብሮላቸውና ነፃነታቸው ተጠብቆላቸው የምናያቸው ብዙዎቹ የዓለም አገራት በፅሁፍ የሰፈረ ሕግ ባልነበራቸው ዘመን በኢትዮጵያ በጽሑፍ የሰፈሩ፣ የህዝቡን መስተጋብር የሚያስተናግዱ፣ የነገሥታቱና የባላባቱን ሥልጣን ድንበር የሚከልሉ፣ በዳይን የሚወቅሱ፣ ተበዳይን የሚክሱ ሕግጋት ነበሩ።
በ16ኛው ምዕተ ዓመት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ «ህዝቤ ያለ ሕግ መኖር የለበትም» በማለት ዲያቆን ጴጥሮስን ወደ ግብጽ ልከው ያስመጡት የግብጽ ክርስቲያኖች (ኮፕቶች) ይተዳደሩበት የነበረው ፍትሐ ነገሥትን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል። ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እራሳቸው ጽፈውታል የሚባለው መጽሐፈ ምዕላድም አንዳንድ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር አንቀጾች እንደነበሩት ይጠቀሳል። ፍትሐ ነገሥቱ ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ ተተርጉሞ ቢያንስ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በዙፋን ችሎት (የንጉሡ ችሎት) በሥራ ላይ እየዋለ እስከ ዐፄ ምኒልክ ዘመን አገልግሏል።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ይተዳደሩባቸው የነበሩ ዛሬም ቅሪታቸው ያልጠፋ በኦሮሞው ገዳ፣ በአማራው ሸንጎ፣ በጉራጌ ቂጫ፣ በትግሬ ሽማግሌ ዓዲ፣ ወዘተ… በሌሎች ብሔረሰቦችም ዘንድ በተለያዩ ስሞች የሚታወቁ የባሕል ሕጎች የሰዎችን ግንኙነት ዳር ድንበር ከልለው ሕዝቡ ተቻችሎ እንዲኖር አድርገዋል።
የአሁኑ አገራችን የፍትህ ሥርዓት በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ ሕዝቡ ለሕግ የነበረው ከበሬታ እየተሸረሸረ መጥቷል፤ ሕግ ነፃነቱን አጥቷል፤ በፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር ወድቋል። ከቀይ ሽብር «ነፃ እርምጃ» ጀምሮ የዴሞክራሲ ጥያቄ በማቅረባቸው የተለያዩ ሥያሜዎች እየተሰጣቸው ፍትህ ዘንድ ሳይደርሱ ወይም ፍትህ ተነፍጓቸው ከማህበራዊ ሕይወታቸው፣ ከቤተሰባቸውና ከሥራቸው የተስተጓጎሉ በርካታ ወገኖቻችንን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም የፍትህ ጉዳይ የሕዝብ አመኔታ አጥቶ ለችግር ተዳርጎ ቆይቷል፡፡
የቀደመው የአገራችን የፍትህ ሥራ እንደ መንፈሣዊ ተግባር ተቆጥሮ ከዳኛው ነፍስ ጋር ትስስር ነበረው። ፍርደ ገምድል ዳኛ በቀጥታ ወደ ገሃነም እንደሚወርድ ይቆጠር ስለነበር «ፍረድ ለነፍስህ፣ ብላ ለከርስህ » ይል የነበረው ብሂል ዳኞች በገንዘብ ወይም በእጅ መንሻ እንዳይታለሉ ሕሊናቸውም ፈሪሃ እግዚአብሔርም ይገድባቸው ነበር።
የዕውነተኛ ፈራጅ አምሳል ተደርጋ የምትወሰደው ዓይኗን የተሸፈነችው እመቤት ሕግ ዛሬ በአንድ እጇ ሚዛን፣ በሌላው እጇ ሾተል ያነገተች ሳትሆን፤ ዓይኗን አፍጥጣ በያዘችው ሾተል መንታ መንታ ትቆርጣለች፡፡ አንዳንድ ከተከበረው የፍትህ ሥርዓት ያፈነገጡ፣ የገቡትን ያለ አድሎ የማገልገል መሃላ የዘነጉ በአንድ ፊት በምልጃና በጉቦ፤ በሌላ ፊት ፍትህን በማዛባት ሕዝብን አስለቅሰዋል፡፡
«ሰው ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ነው» የሚለው ዓለም ዓቀፋዊ መርህ ተሽሮ ሕግ ለፖለቲካ ዓላማ ውሎ ተቃዋሚን መመንጠሪያ መሣሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የሕዝብ አመኔታ ያጣው የፍትህ ተቋም እንደገና እንዲያንሰራራ ለማድረግ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ በሕዝብ ዘንድ የነበረውን የተበላሸ ገጽታ መለወጥ የሚፈልግ የፍትሕ ሥርዓትም ከለውጡ በኋላ ራሱን ችሎ መቆም መቻል ይኖርበታል፡፡
ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሷን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊንና ምክትላቸውን አቶ ሰለሞን አረዳን ለማሾም ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር፣ «ተሿሚዎቹ ፍትሕ ፍትሕ የሚሸት ተቋም እንደሚያደርጉት እተማመናለሁ፤» ብለው ነበር፡፡
ይህንን የፍትህ ሥርዓት ወደ ክብሩ ለመመለስ ነፃና ገለልተኛ መብቱን ማጎናፀፍ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱ ተሿሚዎች ከዚህ ቀደም ከሚታወቀው የፓርቲ ፖለቲካ ልማዳዊ አሠራር ውጪ የተሾሙ በመሆናቸው ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ ይህ ተስፋ እንዳይመክን ለፍትህ ሥርዓቱ መከበር ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡
እንደቀድሞው ሥርዓታችን ሁለት ባላጋራዎች መንገድ ላይ ቢገናኙ ተበደልኩ ባዩ ምንም ኃይል ሳይጠቀም «በሕግ አምላክ ቁም!» በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው (ተቆራኝተው) ያለ ፖሊስ አጃቢ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ እንደነበረው የዋህነታችን ባንመለስ እንኳ ካለፍርድ ከመታሰር፣ ተዘቅዝቆ ከመገረፍ፣ ጥፍር ከመነቀል፣ በቡድን ከመደፈር፣ ብልት በፒንሳ ከመጎተት የሚታደግ ነፃና ማንም የማይዘውረው የፍትህ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ በመሆኑ የፍትህ ባለሙያዎችና የተቋሙ የበላይ አመራሮች ታላቅ አደራ ስለተጣለባቸው ለውጥ የሚያሳይ ተግባር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ማንም የማይዘውረው የፍትህ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ነው!