ሀገራዊው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካል የሆነው 200 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር የመትከል መርሀ ግብር በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ትናንት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አንዱ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ ወረዳ ነው። በለቡ ወረዳ አንድ በሚገኘው ሰፊ የመንገድ አካፋይ ችግኝ ለመትከል በወጣው ህዝብ ዘንድ ይታይ የነበረው ስሜት እጅግ ይደንቃል። ችግኞች በተሽከርካሪ ተጭነው ሲመጡ አውርዶ ለመትከል የሚደረገው መሯሯጥ ቁጭት ይፈጥራል።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ጀርመን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ስትራ ችግኝ ተክላ አታውቅም።ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ መትከሏን ትገልጻለች።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ለቡ ወረዳ አንድ አካባቢ ችግኝ ስትተክል ያገኘናት ወጣት ስትራ፣ ሀምሌ 22 ችግኝ ይተከላል ተብሎ በሚዲያዎች ሲተዋወቅ ሰምታ በጉጉት ስትጠባበቅ መቆየቷን ትናገራለች። የችግኝ ተከላው እጅግ ደስ የሚል ስሜት እንደፈጠረባትም ትገልጻለች።’’
አምስት ችግኝ እተክላለሁ ብላ ከቤቷ እንደወጣች የምትናገረው ወጣት ስትራ፤ ድባቡ እጅግ ደስ የሚልና ለመትከል የሚያነሳሳ ሆኖ እንዳገኘችው ጠቅሳ፤ በዚህም አስር ችግኞችን እንደተከለች ትናገራለች። ሰፈሯ ችግኝ ከተከለችበት አካባቢ ሩቅ መሆኑን ጠቅሳ፤ አልፎ አልፎ እየመጣች ውሃ ለማጠጣትና ለመንከባከብ እንደወሰነች ትገልጻለች።
ወጣት ስትራ እንደምትለው፤ ዛፍ ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አኳያ እስከ ዛሬ ችግኝ ባለመትከሏ ትቆጫለች። ችግኝ መትከልና መንከባከብ የመንግስትን ቅስቀሳ ተከትሎ የሚሰራ ስራ ሊሆን አይገባም የምትለው ወጣቷ፤ ሀገሪቷ ካላት አነስተኛ የደን ሽፋን አንጻር በአመት አንድ ቀን በሚደረግ የዘመቻ ስራ ብቻ በደን ላይ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ነው የምትናገረው። የአረንጓዴ ልማትን ሁሉም ሰው እንደ እለት ተለት ተግባሩ ሊመለከተው እንደሚገባ ጠቅሳ፤ ከቀጣይ አመት ጀምሮ በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ ያለቀስቃሽ የመሳተፍ እቅድ እንዳላት ትገልጻለች።
የካ ክፍለ ከተማ መገናኛ አካባቢ ነዋሪው ወጣት ኤፍሬም አሰፋ 15 ችግኞችን እንደተከለ ይናገራል። ከመስከረም በኋላ መጥቶ ለመንከባከብ መዘጋጀቱን ይገልጻል። ችግኝ ተከላ ባህል ሊሆን ይገባል የሚለውን የወጣት ስትራ ሃሳብ በማጠናከር ፣‹‹ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ባህል እንዲሆን ብርቱ ስራ ይጠይቃል›› ይላል። ሁሉም ሰው ለታዳጊዎች ስለችግኝ ግንዛቤ ሊፈጥር እንደሚገባ፣ ለልጆች ስለ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ማስተማር ከተቻለ ባህል መሆኑ እንደማይቀርም ያብራራል።
ሀገራዊውን ጥሪ በመቀበል በችግኝ ተከላው ለመሳተፍ እንደወጡ የሚናገሩት አቶ ግርማ ቀጠለ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ነዋሪ ናቸው። ችግኝ ተከላው በዘመቻ መሆኑ ሁሉም ዜጎች በአንድነት እንዲተክሉ መደረጉ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የተለያዩ ፋይዳዎች እንዳሉት ይናገራሉ።የችግኝ ተከላው ከዘመቻ ጎን ለጎን የዕለተ ዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ ሀገራዊውን ጥሪ በመቀበል በርካታ ዜጎች በችግኝ ተከላው እየተሳተፉ ናቸው። መንግስትም ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ አድርጎበታል። ይህ መሆኑ ብቻ ግን ሀገሪቷን አረንጓዴ ለማድረግ ዋስትና አይሆንም። በዘለቄታነት መንከባከብ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝብ መልዕክት ለህብረተሰቡ በየጊዜው ሊተላለፍ ይገባል። ሚዲያዎች ሲተከሉ ብቻ ሳይሆን የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ጠቃሜታና ምንነትን በሚገባ ሊያስገንዝቡ የሚችሉ ትምህርቶችን ለህብረተሰቡ በተከታታይ ሊያቀርቡ ይገባል።
ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች የተለየ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው በሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎች እጅግ የሚያስደስቱ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ግርማ፤ እነዚህ መረጃዎች ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ መዋል እንደሌለባቸውም ያመለክታሉ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የችግኝ ተከላ አስተባባሪ ኮሚቴ አቶ አሳሱ እንዳለ እንደሚሉት፤በክፍለ ከተማው 261 ሺህ ጉድጓድና ችግኝ ተዘጋጅተዋል። በወረዳው በመንግስት ከቀረበው ውጪ በግለሰቦች 11 ሺ ችግኞች ቀርበዋል።
ክፍለ ከተማው ካቀደው ውጪ የህብረተሰቡ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ አሳሱ፤ የችግኝ ተከላው በህብረተሰቡ ዘንድ የተለየ መነሳሳት የታየበት መሆኑን ይገልጻሉ።ማህበረሰቡ ለተከላው ከተጠበቀው በላይ መውጣቱን፣ ቢያንስ 36ሺህ ገደማ ህዝብ እንደወጣም ያብራራሉ።
ህዝቡ ይህን ልምድ እንዲያደርገውና ችግኝ ተከላና እንክብካቤን ባህሉ እንዲያደርግ ክፍለ ከተማው ድጋፉንና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
ክፍለ ከተማው
ከችግኝ ተከላ ባሻገር
እንክብካቤ ላይ ትኩረት
አድርጎ ለመስራት ማቀዱን
ይገልጻሉ። ህብረተሰቡ በግሉ
ወስዶ በአካባቢው የተከለውን በግሉ እንዲንከባከብና በጋራ
የተተከሉ ችግኞችን በአካባቢው የሚገኙ ኮንዶሚኒየም ሳይቶች
ተከፋፍለው በመያዝ የእንክብካቤና የጥበቃ ስራውን እንዲሰሩ
ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን
አቶ አሳሱ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011
መላኩ ኤሮሴ