
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኤርትራና ደቡብ ሱዳን የሚገኙትን ጨምሮ አስር ኤምባሲዎችን ለመዝጋት ማቀዱ ተገለጸ።ከኤምባሲዎቹ በተጨማሪ 17 ቆንስላዎቹንም ለመዝጋት ማቀዷን ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል። ከሚዘጉት ኤምባሲዎች 6ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
አሜሪካ በኤርትራ የሚገኘው ኤምባሲዋን ጨምራ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ጽሕፈት ቤቶቿን ልትዘጋ መሆኑን ሮይተርስ የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰነድን ጠቅሶ ዘገበ።
የትራምፕ አስተዳደር አብዛኞቹ በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ ቢያንስ 27 የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችን የሚዘጋ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ኤርትራ አንዷ ናት።በውሳኔው መሠረት ይዘጋሉ የተባሉት አስሩ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በኤርትራ፣ በግሪናዳ፣ በሌሶቶ፣ በማዕካላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሉክዘንበርግ፣ በሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ በጋምቢያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በማልታ እና በማልዲቭስ የሚገኙ መሆናቸውን ሮይተርስ የተመለከተው ሰነድ ያመለክታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲዘጉ ባቀዳቸው ኤምባሲዎች ይከናወኑ የነበሩ ሥራዎችን በአጎራባች ሀገራት ኤምባሲዎች ለማከናወን ማቀዱንም ዘገባው ጠቁሟል።የኤምባሲዎቹና ቆንስላዎቹ መዘጋት የትራምፕ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥትን በጀት ለመቀነስ እየወሰደ ያለው ርምጃ አካል ነው ተብሏል።
አሜሪካ ለመዝጋት ካቀደቻቸው አስር ኤምባሲዎች መካከል ስድስቱ በአፍሪካ የሚገኙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በሶማሊያ ሞቃዲሾ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ፣ ካልሆነ ደግሞ ሠራተኞቹ በከፍተኛ ቁጥር እንዲቀነሱ ሃሳብ መቅረቡን ዘገባው አመላክቷል።
አሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኤርትራ የሚገኘውን ኤምባሲውን ለመዝጋት የያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በርቀት ወይም በሦስተኛ ወገን እንዲሆን ያደርጋል።
በተጨማሪም ከሚዘጉት 17 የአሜሪካ ቆንስላዎች መካከል ከ12 የሚበልጡት በአውሮፓ የሚገኙ ናቸው። ቀሪዎቹ በደቡብ ኮሪያ ቡሳን፣ በደቡብ አፍሪካ ደርባን፣ በኢንዶኔዢያ ሜዳን እና በካሜሩን ዱዋላ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።
ከሚዘጉት ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ባሻገር ኤምባሲ እና በርካታ ቆንስላዎችን በመያዝ ግዙፍ የዲፕሎማቲክ ሥራ በሚከናወንባቸው እንደ ጃፓን እና ካናዳ ያሉትን ተልዕኮዎች በማዋሃድ መጠናቸውን የመቀነስም ሃሳብ አለ።በተጨማሪም ሰነዱ ከፍተኛ ወጪ በማስወጣት ውድ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ የተመደበባቸው ናቸው ያላቸውን በሞቃዲሾ ሶማሊያ እና በኢራቅ ያሉ የዲፕሎማቲክ አባላትን መጠን የመቀነስ ሃሳብ መቅረቡን አመልክቷል።
ትራምፕ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከተመለሱ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ መስኮች ከሀገሪቱ ፍላጎት ጋር አይጣጣሙም ያላቸውን ተቋማት በመዝጋት እና ርዳታዎችን በማቋረጥ ላይ ይገኛል። በእዚህም የትራምፕ የቅርብ ሰው በሆኑት ማርኮ ሩቢዮ የሚመራው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጀት እስከ ግማሽ የሚደርሰው እንደሚቀነስ ሮይተርስ የተመለከተውን የመሥሪያ ቤቱን ሰነድ ጠቅሶ አመልክቷል።
በእዚህም ሳቢያ በበርካታ ሀገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችን የመዝጋት ሃሳብ እንዳለ ተገልጿል። ይዘጋሉ ከተባሉት የአሜሪካ የዲፕሎማቲክ ተቋማት መካከል አስሩ ኤምባሲዎች ሲሆኑ የቀሩት ቆንስላዎች መሆናቸው ታውቋል።
የአሜሪካ መንግሥት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚያወጣው ገንዘብ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለመቀነስ አቅዶ የበጀት ጥያቄውን ለሀገሪቱ ምክር ቤት ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው። የሮይተርስ የዜና ወኪል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት በተያዘው ዕቅድ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።
ሮይተርስ የተመለከተው የበጀት መጠየቂያ ሰነድ እንደሚያሳየው፤ በጀቱ በአሁኑ ወቅት ካለው 54 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወደ 28 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። በተጨማሪም ለውጭ ርዳታ በአሜሪካ የዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ (ዩኤስ ኤአይዲ) በኩል ይቀርብ የነበረው 38 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 16 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር እንዲካተት የተወሰነበት ግዙፉ የዓለማችን የርዳታ ተቋማ ዩኤስኤአይዲ በዓለም ዙሪያ የነበሩትን ከአምስት ሺህ በላይ ፕሮግራሞቹን በመዝጋት በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን ማሰናበቱ ይታወቃል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም