ድርጅቱ ከብክለት የጸዳ አካባቢ እንዲኖር የሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚበረታታ ነው

አዲስ አበባ፡- ፊንቴክ ኢንቨስትመንት ከብክለት የፀዳ አካባቢ ለመፍጠር እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታ ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ::

አምባሳደሩ ድርጅቱ ባደረገው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ድርጅቱ እየሠራ ያለው ሥራ በተለይ የዓለማችን ዋነኛ ችግር የሆነው የአየር ብክለት ጫና ለመቀነስ ጊዜውን የጠበቀ ትልቅ ሥራ ነው፤ የቀድሞ አያቶቻችን የውጭ ወራሪ በመከላከል በጀግንነት ነፃ ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ፤ የአሁኑ ትውልድም ከድህነት ነፃ ለመውጣት እያደረገ ያለው ጥረት መቀጠል ያለበት ነው::

ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ ከመቀነስና ከአረንጓዴ ልማቱ ጋር ተዋዳጅ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ድርጅቱ ትልቅ ሥራ እየሠራ ስለሆነ የሚደነቅ መሆኑን አመልክተው፤ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል::

የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ የአብስራ ታደሰ በበኩላቸው፤ፊንቴክ ኢንቨስትመንት ቀደም ሲል በኦሮሚያ ባህል ማዕከል፣በስካይ ላይት ሆቴል እና በወዳጅነት ፓርክ 250 የኤሌክትሪክ መኪኖች ለደንበኞች ማስረከቡን አውስተው፤ አሁን ደግሞ 258 የኤሌክትሪክ መኪኖች ለማስረከብ ከጅቡቲ ወደ ገላንና ቃሊቲ ለማጓጓዝ ዝግጅቱን ጨርሷል ብለዋል::

መርሀ ግብሩ የ20ሺህ የኤሌክትሪክ መኪኖች የመገጣጠምና የማቅረብ ፕሮጀክት አካል ነው ያሉት ምክትል ሥራ አስፈፃሚው፤ ሀገራችን ወደ አረንጓዴ ማጓጓዣ ዘርፍ የምታደርገውን ሽግግርና የማህበረሰቦች የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማገዝ በግል ዘርፉ እየተወሰደ ያለው ጉልህ ተግባር ነው ብለዋል::

ድርጅቱ በቀጣይ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መኪኖች በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሳ፣ መቐለና ሌሎች የሽያጭ ጣቢያዎችን የተንቀሳቃሽ የጥገና ጣቢያዎችን እንዲሁም አረንጓዴ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You