አዲስ አበባ ፦ በዓሉ ከስጋት ነጻ ሆኖ እንዲከበር በሁሉም ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ ከተማ አስተዳደሩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ሞላ፤ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ለትንሳኤ በዓል የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የከተማዋ ነዋሪ ከአደጋ ስጋት ነጻ ሆኖ በዓሉን እንዲያከብር እንደ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ተከታታይ ቀናት በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በእዚህም መሠረት አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ለማስቆም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በቂ የዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ከኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ ከጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲና ሌሎችም ጋር በመሆን ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም እቅድ ተቀምጦ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የከተማዋ ነዋሪም ከተማ አስተዳደሩ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ከግምት በማስገባት ራሱም በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ከእዚህ ያለፈ ችግር ከተከሰተም ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሀመድ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱ ለመቆጣጠር በቂ ዝግጅት አድርጓል ይላሉ። ኮማንደሩ ባለፉት ቀናት የተደረጉ ዝግጅቶችን ሲያብራሩም፤ በከተማዋ አደጋ ይከሰትባቸዋል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች የትኞቹ እና ለምን አይነት አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል። በእዚህም በከተማዋ በሁሉም ወረዳዎች በቤት ለቤት ማንቂያ መልእክት፤ በበራሪ ወረቀቶች እንዲሁም የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት ኅብረተሰቡን የማንቃት ሥራ የተከናወነ ሲሆን፤ ከኅብረተሰቡም አበረታች ምላሽ ለማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።
እንደ ተቋምም ላለፉት ሃያ ቀናትም ለሁሉም ሠራተኛ ከአካል ብቃት ጀምሮ የተለያዩ ሥልጠናዎች ሲሰጡ ቆይተዋል። ለአደጋ መከላከል የምንጠቀምባቸውን ተሽከርካሪዎችና ቁሳቁሶች በመፈተሽ ለሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግም ተችሏል። የመረጃ መጠቆሚያና መቀበያ 939 ነጻ የስልክ መስመርም ከዛሬ ጀምሮ በልዩ ዝግጅት የሚሠራ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።
ይህም ሆኖ በምግብ ዝግጅት ከኤሌክትሪክ እንዲሁም የከሰል፤ ሻማና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ጥቅም ላይ ሲውሉ የሚፈጥሩት አደጋ ስለሚኖር ዜጎች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው አመልክተው፤ በተጨማሪ ከትራፊክ እንቅስቃሴም ጋር በተያያዘ አሽከርካሪዎች ጠጥተው ከማሽከርከር ሊታቀቡ የሚገባ ሲሆን፤ እግረኞችም ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይም የከተማዋ ነዋሪ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ጥንቃቄ በማድረግና አደጋ ከተከሰተም በፍጥነት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
«በዓሉን ስናከብርም ሆነ ከበዓል በኋላ በቆሻሻ አወጋገድ ረገድ ከተማዋን በሚመጥን መልኩ ልንንቀሳቀስ ይገባል» ያሉት ደግሞ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ፤ ኤጀንሲው ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ከተማ የማጽዳት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ይህም ሆኖ በበዓል ወቅት ከእርድና ከተረፈ ምግብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ቆሻሻዎች መኖራቸው ይታመናል። በመሆኑም ከማህበረሰቡ ይህንን በአግባቡ ለይቶ ማስወገድ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ቆሻሻ ለመሰብሰብ በበቂ ሁኔታ ልዩ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን፤ በአጋጣሚ የሚፈጠር ችግር ካለ በነጻ የስልክ መስመር 6199 ማሳወቅ የሚቻል መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም