
– በዘርፉ ከ4ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል
አዲስ አበባ፡- የሲዳማ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 176 ኪሎ ግራም ወርቅ በላይ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉን የክልሉ የማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አስታውቋል::ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩም ገለጸዋል::
የክልሉ የማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩኮ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት በወርቅ አምራች ማህበራትና በአዘዋዋሪዎች 176 ነጥብ ሁለት ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት ተችሏል::በዘጠኝ ወራት በወርቅ አምራች ማህበራት 10 ነጥብ ሁለት ኪሎ ግራም የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዘዋዋሪዎች ደግሞ 166 ኪሎ ግራም ወርቅ መገኘቱን ገልጸዋል::
አዘዋዋሪዎች ከአምራቾች እና ካገኙበት ቦታዎች ሁሉ ወርቅ በመግዛት ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡ ሕጋዊ ፍቃድ የተሰጣቸው ናቸው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አዘዋዋሪዎች ከባለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባታቸው አመልክተዋል::
ቀደም ባሉት ጊዜያት አዘዋዋሪዎች ዝቅተኛ መጠን ያለው ወርቅ የሚያቀርቡ መሆኑን አስታውሰው፤ በዘንድሮ ዓመት በተለየ መልኩ ከፍተኛ ወርቅ በማቅረባቸው ምክንያት ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ እንዲሰበሰብ ሆኗል ብለዋል::
በክልሉ ወርቅ የማምረት ፍቃድ የወሰዱ ማህበራት አብዛኛውን ባሕላዊ ወርቅ እንደሚያመርቱ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባሕላዊ የወርቅ አምራቾች ሆነው ከባለሀብቶች ጋር ተቀናጅተው የሽርክና ማህበር መስርተው በዘመናዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ መኖራቸውንም ጠቁመዋል::
የማዕድን ዘርፉ ለብዙዎች የሥራ እድል የሚፈጠር ዘርፍ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ በዘጠኝ ወራትም ለአራት ሺህ ሰማንያ ሦስት ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አመላክተዋል::
በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን ሀብቶች በማልማት ሥራ የተሰማሩ 162 ማህበራት እንዳሉ የሚጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ማህበራቱ ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸው ጠቁመዋል:: አብዛኛውም ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናት በማምረት ሥራ የተሰማሩ መሆናቸውን አመላክተዋል::
በክልሉ ሌሎች በርካታ ማዕድናት የሚመረቱ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዘጠኝ ወራት ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ቶን ታልክና ፊልድስፖር የተሰኙ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ለገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል::
በተጨማሪም ‹ሩታየል› የተሰኘ በከፊል የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድን የሚመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘጠኝ ወራት 65 ቶን ተመርቶ ለገበያ መቅረቡን ገልጸዋል::ማዕድኑን እስካሁን ድረስ በጥሬ ለውጭ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ እሴት ተጨምሮበት ጥቅም ላይ እንዲውል የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም አመላክተዋል::
በክልሉ በማዕድን ዘርፉ ዘጠኝ ወራት ከሮያሊቲ ክፍያ፣ በገቢ ግብርና መሰል ሌሎች ክፍያዎች 11 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 12 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወቁት::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም